1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ የስደተኞች ጣቢያ እንደ ሰደድ እሳት የሚፈራው ኮቪድ 19 

ዓርብ፣ ሚያዝያ 9 2012

እንደ ተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን  UNHCR ከሆነ አፍሪካ ውስጥ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ወይም ተፈናቃዮች ይገኛሉ። ስለሆነም በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ቢከሰት እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት የመሰራጨት አቅም እንዳለው ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

https://p.dw.com/p/3atV5
Uganda Junge Frauen transportieren Kanister mit Wasser auf ihrem Kopf
ምስል Imago Images/photothek//T. Koehler

በስደተኞች ጣቢያ እንደ ሰደድ እሳት የሚፈራው ኮቪድ 19 

በአፍሪካ በሚገኙ በርካታ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እና ድሃ ሰፈሮች ያለው የኑሮ ሁኔታ ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋትም በፊት በጣም ከባድ የሚባል ነው። የ 25 ዓመቷ ስቴላ ንዳፖሎ ስደተኛ ናት። ስቴላ ከቤተሰቦቿ ጋር ከኮንጎ ወደ ጎረቤት ሀገር ዮጋንዳ ከተሰደደች ጥቂት አመታት ተቆጠሩ። ወጣቷ ከእናቷ እና ከአራት ወንድምና እህቶቿ ጋር በአንድ የስደተኛ ጣቢያ ውስጥ ይኖራሉ። በኮሮና ቀውስ ምክንያት ያለንበት ሁኔታ ተባብሷል ትላለች ስቴላ።« የትም መሄድ አትችልም። ምንም የቆጠብከው ወይም ቤትህ ውስጥ ያስቀመጥከው ምግብ  የለህም።በአሁኑ ሰዓት  እኛን አብዛኞቹን ስደተኞች እዚህ ዮጋንዳ ውስጥ እየጎዳን ያለው ርሃብ ነው። ያለ ትምህርት መቆየት ይቻላል፣ ያለ ትራንስፖርት አገልግሎት መቆየት ይቻላል። መሰረታዊ ነገር የሆነው ምግብ ሳይኖረን ግን መቆየት አንችልም።»
ዩጋንዳ ከህዝብ ብዛቷ አንጻር እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ የተቀበለች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት። እንደ ተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን  UNHCR 1,2 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች በሀገሪቷ ይኖራሉ። አብዛኞቹም ስደተኞች የመጡት ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፣  ከሩዋንዳ ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከሶማሊያ ነው። ምንም እንኳን ስደተኞቹ በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ በቀረበ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቢሆንም እንዲቆዩ የሚደረጉት በ10 ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች ግን መጠለያውን እየለቀቁ ለመዲናዋ ካምፓላ ቅርብ የሆነ መንደር ውስጥ ለመኖር ይሞክራሉ። የስቴላ ቤተሰብም በመዲና ካምፓላ  ጎዳና ላይ እየነገዱ ለመኖር ከሚጥሩት ስደተኞች መካከል አንዱ ነው። አሁን ላይ ግን የሀገሪቱ መንግሥት ኮሮናን ለመከላከል በንግድ ተቋማት ላይ በጣለው ገደብ የተነሳ ስቴላ እና ቤተሰቦቿ በንግድ መተዳደር አልቻሉም። ስለሆነም ወጣቷ ወይ በርሃብ ወይም ኮቪድ 19 ህይወታችን ያልፋል የሚል ስጋት አላት። 
ከድሆች ሰፈር ባሻገር በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ያለው ሁኔታ ከዚህ የከፋ ነው ሲሉ ሜዲኮ ኢንተርናሽናል የተባለው የእርዳታ ድርጅት ባልደረባ ራሞና ሌንዝ ለDW ያስረዳሉ።
« ኬንያ ውስጥ በዳዳብ እና ኩኩማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይገኛሉ። ወይም ቢዲቢዲ ዮጋንዳ ውስጥ ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከለላ ጠይቀው ይገኛሉ። ይህ እጅግ ግዙፍ ቁጥር ነው። ብዙ ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖርበት ቦታ እንደመሆኑ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የማይችሉበት ሁኔታ ነው ያለው። እጅ ቶሎ ቶሎ መታጠብን ተግባዊ ማድረግ የማይችሉ ናቸው። የህክምና እርዳታ የማግኘት ዕድል የሌላቸው ናቸው። በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ወረርሽኙ እንዳይከሰት በተቻለ አቅም እየተሞከረ ነው ምክንያቱም አንዴ ከተከሰተ መጨረሻው እጅግ አስከፊ እንደሚሆን ግልፅ ነው። »
«ከጊዜ ጋር ትግል ይዘናል» የሚሉት ደግሞ በአፍሪካ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ፓትሪክ ዩሴፍ ናቸው። “ለሰዎች እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ ኮቪድ 19 በስደተኞች መካከል እንዳይከሰት የተቻለውን ሁሉ ማድረግ አለብን ይላሉ። « ቡርኪና ፋሶን በምሳሌነት ብንወስድ በሀገሪቱ ባለው ግጭት የተነሳ ከ 1,5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከህክምና ርዳታ ርቀው ይገኛሉ። ሶማሊያን የወሰድን እንደው የህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት 15 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። በርግጥ ድሮም ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጠችው አፍሪቃ እንደዚህ አይነት ወረርሽኝን መጋፈጥ ትልቅ ፈተና ይሆናል። »
በማሊ ባማኮም ይሆን በናይጄሪያ ከቦኮ ሀራም አማፂ ቡድን ሸሽተው እና ተፈናቅለው የሚገኙ አፍሪቃውያን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት። እስካሁን በነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች ኮሮና ስለመከሰቱ በይፋ የተገለፀ ነገር ባይኖርም በሰሜናዊ ናይጄሪያ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ተህዋሲው መገኘቱ በመረጋጡ ስጋቱ እጅግ ከፍተኛ ሆኗል።

Ramona Lenz | Referentin für Flucht und Migration von Medico International
የ ሜዲኮ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ራሞና ሌንዝምስል Privat
Uganda Kampala | Stella Nbapolo & Familie
ስቴላ ከቤተሰቦቿ ጋር ከኮንጎ ወደ ጎረቤት ሀገር ዮጋንዳ ከተሰደደች ጥቂት አመታት ተቆጠሩ።ምስል privat

አንቶኒዮ ሳስኪያስ/ ልደት አበበ