1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በስደተኞች ቀውስ ላይ የመከረው የአውሮጳ ኅብረት

ዓርብ፣ መስከረም 18 2016

ከፍተኛ የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ያሳሰባቸው የአውሮጳ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ስብሰባ ተቀምጠዋል ። ፍልሰቱ ግን ይጨምር እንጂ ሲቀንስ ዐልታየም ። እስካሁን ከ250 ሺ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ መግባታቸው ይነገራል ። በዚሁ ጉዳይ የአውሮጳ ኅብረት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ብራስልስ ተሰብስበዋል ።

https://p.dw.com/p/4WxSL
ሕገወጥ ስደተኞች በላምፔዱዛ፤ ጣሊያን፦ ፎቶ ከማኅደር
ሕገወጥ ስደተኞች በላምፔዱዛ፤ ጣሊያን ። ከሳምንት በፊት በጣሊያን ደሴት ላምፔዱዛ በ24 ሰአት ብቻ ከሰባት ሺ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ መግባታቸው ተዘግቧል ። ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Cecilia Fabiano/AP Photo/picture alliance

ፍልሰቱ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ ዐልታየም

ከፍተኛ የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ያሳሰባቸው የአውሮጳ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ስብሰባ ተቀምጠዋል ።ፍልሰቱ ግን ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ ዐልታየም ። እስካሁን  ከ250 ሺ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ መግባታቸው ይነገራል ። ከሳምንት በፊት በጣሊያን ደሴት ላምፔዱዛ በ24 ሰአት ብቻ ከሰባት ሺ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ መግባታቸው ተዘግቧል ። በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺ በላይ ተገን ጠያቂዎች አውሮጳ ውስጥ ለጥገኝነት ያመለከቱ መሆኑን የኅብረቱ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል ። በተለይ የሕገወጥ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ቁጥር  ለአውሮጳ ኅብረት ተጨማሪ ተግዳሮት ሆኗል ። 

የአውሮጳ ኅብረት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት እዚህ ብራስልስ ባካሄዱት ስብሰባ፤ በአደገናኛ ሁኔታ በብዛት የሚድትራኒያን ባህር አቁርጠው ወደ አውሮፓ እየገቡ ስላሉ ስደተኞች ጉዳይና፤ በአህጉሩ እየተስፋፋ ስላለው የአደንዛዣ እጽ ዝውውር በስፋት ተወያይተው ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። ሚኒስትሮቹ በአደንዛዥ ዕጽ ጉዳይ የመከሩት ከላቲን አሜሪካ 14 አገሮች ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር የነበር ሲሆን፤ የዚህን ዕጽ ዝውውር ለመግታትና ተያያዥ ወነጅሎችንም ለመክላከል በጋራና በተቀናጀ ሁኔታ ለመስራት የተስማሙ መሆኑ ተገልጿል።

የኮሚሽኑ የፍትህና የውስጥ አስተዳደር ኮሚሽነር  ወይዘሮ ይልቫ ጆሃንሶን ከወቅቱ የህብረቱ ፕሬዝደንሲ የስፔን ያገር ውስጥ ሚኒስተር ሚስተር ፌርናንዶ ማርላስክ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኮኬይን የሚባለው አደንዛዥ ዕጽ ዛሬ የሚበቅለው በላቲን አሜሪክ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም ጭምር ሁኗል በማለት በህብረቱ አገሮች ከሚፈጸሙት ወንጀሎችና ግድያዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም ከዚህ እጽ ዝውውር ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሚኒስትሮቹ በሁኑ ወቅት የህብረቱና አባል አገራቱ ዋና የፖለቲክ አጀንዳ በሆነው የስደተኖች ጉዳይ ከአሳሪ ስምምነት ባይደርሱም በተለይ የቀውስ ግዜ እርምጃዎችን በሚመለከት ግን ከስምምነት እንደተደረሱና ይህም በቀጣይ  የህብረቱን የጋራ የስደተኖች ፖሊስ ለማጽደቅ ጭምር ሊረዳ እንደሚችል ተገልጿል።

ላምፔዱዛ ደሴት፤ ጣሊያን
ወደ አውሮጳ ሕገወጥ መንገድ ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራ የሚደረግባት የጣላዪane ደሴት ላምፔዱዛ ። እዚህች ደሴት ላይ ሳይደርሱ ሕይወታቸውን እባሕር ውስጥ ያጡ ስደተኞች ቁጥር በርካታ ነው ። ምስል Cecilia Fabiano/AP Photo/picture alliance

ከሳምንት በፊት በጣሊያን ደሴት ላምፔዱዛ በ24 ሰአት ብቻ ከሰባት ሺ በላይ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ መግባታቸውን ተክትሎ፤ የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ቮንዴርለየን ባለ አስር ነጥብ የድርጊት እቅድን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በስፔን ፕሬዝደንሲ የቀረበውና አሁን ተቀባይነት አግንቷል የተባለው ሰነድ፤ መንግስታት የስደተኖች ቀውስ ሲገጥማቸው በተወሰነ ድረጃ የራሳቸውን ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስልጣን የሚሰጥ ነው ተብሏል።

ስነዱ የሰባዊ መብቶችን በተለይም ልዩ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የሴቶችንና ህጻንትን መብቶች ይጥሳል በሚል ተቃውሞ ተነስቶበት የነበር ቢሆንም፤ በተለይ ጀርመንተቃዉሞዋን ካነሳች በኋላ ግን  በአብላጫ ድምጽ ተቀባይነት  እንደሚያገኝ ሁለቱም ባለስልጣኖች አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ጆሀንሰን በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት  ወደ ህብረቱ በገፍ  የሚገቡት ስደተኞች ከፍተኛ ጫና የፈጠሩ መሆኑን በማውሳት፤ ሚኒስትሮቹ ከዚህ ውሳኔ የደርሰበትን ምክኒያት አብራርተዋል፤ “  እስካሁን  ከ250 ሺ በላይ ስደተኖች በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ገበተዋል። ዋናው መዳረሻም ጣሊያን በተለይም ላምፔዱዛ ነው  በማለት ይህንን ሁኔታ  በጥልቀት እንደተወያዩበትና ጫናውንም እንድተገንዘቡት አስረድተዋል ። ወይዘሮ ጆሀንሰን አክለውም፤ “ በተመሳሳይ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺ በላይ ተገን ጠያቂዎች ያመለክቱ ሲሆን ይህም ያለው ተግዳሮት ሕገወጥ ስደተኖችን ከመክላከል የዘለለ መሆኑን ያሳያል ሲሉ፤ በአውሮፓ ህብረት ስደተኝነት ለመጠየቅ አስበው በህጋዊ መንገድ የሚመጡትን ሰዎች በሚመለከትም ከሦስተኛ አገሮች ጋር መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ላምፔዱዛ ፤ ጣሊያን
ከባሕር አደጋ የተረፉ ስደተኞች ላምፔዱዛ ደሴት፤ ጣሊያን ደርሰው ። በርካቶች በዚህ አደገኛ ጉዞ እባሕር ውስጥ ሕይወታቸውን ያጣሉ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Yara Nardi/REUTERS

ህብረቱ ደንበሩን በሕገወጥ መንገድ ጥሰው የሚገቡ ስደተኞችን ለመክላከልና የሰው አዘዋዋሪ ወንጀሎኞችንም ለመቆጣጠር፤  እስካሁን ከቱርክና ሊቢያ ጋር ስምምነት እንዳደረገ የሚታወቅ ሲሆን፤ በቅርቡም የ100 ሚሊዮን ኢሮ ርድታን የያዘ ተመሳሳይ ውል ከቱኒዚያ ጋር ተፈራርሟል፤ በቀጣይም ከግብጽ ጋር እንደዚሁ ከስምምነት ይደረሳል እየተብለ ነው።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ግን ኅብረቱ ለስደተኞች መስደድ ምክንያቶች ከሆኑ አምባገነን መሪዎች ጋር ጭምር  በመስማማት አለማቀፍ የሰብአዊና ስደተኞች መብቶችን እየጣሰ ነው በማለት  ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። ዲደብሊው ኮሚሽነር ይልቫ ጆሀንሰንን ህብረቱ  በስደተኖች ጉዳይ ክሶስተኛ አገሮች ጋር ለመስራት ያስቀመጠው መስፈርት ካለ በማለት ቱኒዚያን ጠቅሶ ላነሳው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “

ከቱኒዝያ  ጋር የገባነው ውል በአምስት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው። አንደኛ በቱኒዝያ ያሉ ስደተኖችን ወደ አገሮቻቸው የምንመልሰው በመንግስታቱ ድርጅት የፈላሲያን ጽሕፈት ቤት (IOM) በኩል ነው። ሁለተኛ ቱኒዚያን በአደገኛ ሁኒታ ጉዞ የሚጀምሩ ስደተኖችን ለመክላከል የሚረዱ የቅኝትና የነፍስ አድን መሳሪያ መርዳት፤ ሦስተኛ የስደተኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙትን ቱኒዚያውያን በፍጥነት እንዲመለሱ ማድረግና መስራት የሚችሉና ችሎታ ያላቸው ቱኒዚያውያን ወደ ህብረቱ በሕጋዊ መንግድ ሊገቡ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የተመረት መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ህብረቱና አባል አገራቱ  በአሁኑ ወቅት በስደተኞ ላይ የሚወስዷቸው ርምጃዎች ዓለማቀፍ የሰባዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጻረሩ እንደሆነ ነው በስፋት የሚነገረው። ይህም በብዙዎቹ አባል አገሮችና ባውሮፓ ደረጃ ምርጫ የሚካሄድበት ግዜ የተቃረበ በመሆኑና ብሄረተኞችና ጸረ ስደተኖች ፓርቲዎች አጀንዳውን ለምርጫ ቅስቀሳ እንዳይጠቀሙበት በመስጋት ጭምር እንደሆነ ነው የሚገመተው ።

ገበያው ንጉሤ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር