1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለተጠቁት የሰብአዊ ዕርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት

ቅዳሜ፣ የካቲት 12 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ እልባት ለመስጠትና ለተጎጂዎች እርዳታ እንዲደርስ የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል። በየብስ እና በአየር አመራጭ እርዳታዎች በጦርነቱ ለተጠቁት እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

https://p.dw.com/p/47I2V
Äthiopien Kebede Desisa
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳትን ለማድረስ እያደረገ ያለው ጥረት ምንድነው ?

 

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ እልባት ለመስጠትና ለተጎጂዎች እርዳታ እንዲደርስ የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ በየብስ እና በአየር አመራጭ እርዳታዎች በጦርነቱ ለተጠቁት እንዲደርስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአፋር በኩል የህወሓት ኃይሎች የከፈቱትን ጦርነት የፌዴራል መንግስት በሚገባ አልተከላከለም መባሉንም ሚኒስትር ዴኤታው አስተባብለዋል፡፡

ለጦርነቱ ዘላቂ እልባት ግን የፌዴራል መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ነው የተባለው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ቢሮ በሳምንቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ምንም እንኳ በነዳጅ እጥረት ማከፋፈል ባይቻልም ተጨማሪ የመድኃኒት ቁሳቁሶች በአየር ትግራይ ክልል መቀሌ መድረሳቸውን አመልክቷል፡፡ ይሁንና በዚሁ ክልል 11 ሺ ነብሰጡር እናቶች እና 60 ሺ ህፃናት ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውን የሰብዓዊ ድርጅቱ በሳምንታዊ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

በሳምንቱ በአፋር ለ78 ሺህ እንዲሁም በአማራ ክልል በሁለት ዙር ለ127 ሺህ ዜጎች እርዳታ ማዳረሱንም ገልፆ፤ በአንጻሩ በሰሜን አፋር በሚደረገው ጦርነት ምክኒት በገፍ ለሚስተዋለው መፈናቀል የደህንነት ስጋት በመኖሩ እርዳታ ማድረስ አልተቻለም ብሏልም፡፡

ስለዚሁ የሰብዓዊ እርዳታ መስተጓጎል የተጠየቁት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሰመራ-አባዓላ-መቀሌ የእርዳታ ኮሪደርን በመዝጋት ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ 

የፌዴራል መንግስት በአፋር በኩል ይደረጋል ያሉትን ትንኩሳ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እና በቅርበት እየተከታተለ ድጋፍም ያደርጋል ሲሉ የሞገቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለያዩ ጊዜያት የፌዴራሉ መንግስት በአፋር 5 ወረዳዎችን አዳርሶ በርካቶችን ላፈናቀለው ጦርነት ትኩረት ነፍጎታል መባሉን አይቀበሉትም፡፡ 

አመት ከአራት ወራት ገደማ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ ቆይቶ አሁንም እየቀጠለ ያለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም የመደምደም እድልና ዝግጁነትም ላይ ለአቶ ከበደ ጥያቄ አቅርበንላቸው መልስ ሰጥተዋል፡፡ 

የህወሓት ሊቀ መንብር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 መታሰቢያን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ላይ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ 

ስዩም ጌቱ 

ታምራት ዲንሳ