1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የወደሙ ጤና ተቋማት መልሶ ግንባታታ

ማክሰኞ፣ ጥር 2 2015

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግጭት የወደሙ ጤና ተቋማትን ምልሶ ለመገንባት ቢያንስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ዐስታወቀ። ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከቅርብ ጊዜው የትግራይ ጦርነት በሰላም መቋጨት በኋላ በርካታ የህክምና ተቋማትን ስራ ማስጀመር መቻሉንም አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4LyWl
Äthiopien PK Gesundheitsministerin Lia Tadesse Gebremedhin
ምስል Seyoum Getu/DW

መልሶ ግንባታ

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግጭት የወደሙ ጤና ተቋማትን ምልሶ ለመገንባት ቢያንስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ዐስታወቀ። ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ ከሰዓቱን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከቅርብ ጊዜው የትግራይ ጦርነት በሰላም መቋጨት በኋላ በርካታ የህክምና ተቋማትን ስራ ማስጀመር መቻሉንም አመልክተዋል። 

በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ በነበሩ አከባቢዎች የጤና ተደራሽነት እና የመልሶ ግንባታ ስራዎች በማስመልከት መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዳመለከቱት ላለፉት ሁለት ዓመታት ግጭት የተከሰተባቸው እና አሁንም ግጭቱ በሚስተዋልባቸው አከባቢዎች የጤና መሰረተ ልማቶች እና መገልገያዎቹ በመጎዳታቸው አገልግሎቱን ማዳረስ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡ 
በተለይም በቅርቡ በሰላም ስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የጤናው አገልግሎትን ክፉኛ መጉዳቱ ነው የተገለጸው፡፡ በመሆኑም በነዚህ አከባቢዎች የተጎዱ የጤና መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ከጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ ከ30 በላይ የባለሙያዎች ቡድን መላካቸውንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡   
“ቡድኖቹ በአላማጣ፣ ኮረም፣ ሽሬ፣ አክሱም እና አዳዋ ላይ በሁለት ዙር ተሰማርተው ጤና ተቋማቱ ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ሲሰሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየሰሩ ነው” ብለዋል፡፡
በዚህም 33 የሚሆኑ የጤና ተቋማት፣ በአክሱም በሚገኘው የደም ባንክ እና ተፈናቃዮች ያሉባቸው መጠለያዎች ላይ ዳሰሳዊ ትናት መካሄዱንም ዶ/ር ሊያ አንስተዋል፡፡ በነዚህ በተጠቀሱ አከባቢዎች 12 ሆስፒታሎች እና 28 ጤና ጣቢያዎች ባጠቃላይም 36 የጤና ተቋማት አገልግሎት ወደ መስጠት መመለሳቸው እና 95 በመቶ ሰራተኞቻቸውም ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውንም እንዲሁ ገልጸዋል፡፡ “በነዚህ አከባቢዎች ከ104 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ባለፈው አንድ ወር አገልግሎት አግኝነተዋል፡፡ 11 ሚሊየን ገደማ ብር ደግሞ በጊዜያዊ ክፍያነት ተከፍሏልም” ብለዋል፡፡
ከጤና ቁሳቁስና ህክምና መዳሃኒት ስርጭት ጋርም በተያያዘ በመጀመሪያ ዙር በሚኒስቴሩ 79 ሚሊየን ገደማ የሚያወጣ የጤና ቁሳቁስና መድሃኒቶች መላካቸውም ተብራርቷል፡፡ የጤና መገልገያ ቁሳቁሶች ጥገናም ከስር ከስር እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ 81 ሚሊየን የሚገመቱ የተለያዩ መድሃኒቶች ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ወደ መቀሌ መላካቸውንም ያመለከቱት ዶ/ር ሊያ 112 ሚሊየን የሚገመቱ ክትባቶች ደግሞ በዩኒሴፍ እና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ድርጅት በኩል መላካቸውን አብራርተዋል፡፡
ከነዚህ በመንግስት ከተላኩት የህክምና ቁሳቁሶች በተጨማሪ በግብረሰና ድርጅቶችም የተለያዩ መድሃኒቶች እና ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ መላካቸውን አንስተዋል፡፡ “1525 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቆሶች እና መድሃኒቶች በመንግስት እና አጋር ድርጅቶች እንዲላክ የተደረገ ሲሆን አሁንም 10 ሺህ ቶን ገደማ የህክማና ቁሳቁሶች ዝግጁ ተደርገዋል፡፡”
በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ያለውን የኩፍኝ ክትባትንም በትግራይ ተደራሽ ለማድረግ ለ1.1 ሚሊየን እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ክትባቱ መላኩንም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡ 
ከትግራይ ክልል ውጭ በአማራ እና በአፋር ክልሎችም የወደሙ የጤና መሰረተ ልማቶች እና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሚኒስቴሩ ሲንቀሳቀስ መቆየቱም ተነግሯል፡፡ በዚህም በአማራ ክልል ብቻ 40 ሆስፒታሎች እና 415 ጤና ጣቢያዎችን አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 
በአፋርም የጦርነት ሰለባ የሆኑ 1 ሆስፒታል እና 25 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም በኦሮሚያ 33 በግጭት የተጎዱ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉንም አክለዋል፡፡
አጠቃላይም በሶስት አማታት መልሶ ለመጠገን እቅድ የተያዘለት የጤና መሰረተ ልማትን ወደ ነባር አገልግሎታቸው ለመመለስ 1.4 ቢሊየን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል፡፡
 

በጦርነቱ ከወደሙና ከተዘረፉ የጤና ተቋማት አንዱ-ደሴ ሆስፒታል
በጦርነቱ ከወደሙና ከተዘረፉ የጤና ተቋማት አንዱ-ደሴ ሆስፒታልምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ