1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርካታ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲ ተማሪዎች በኮሌራ በሽታ መጠቃታቸው ተገለጸ

ቅዳሜ፣ የካቲት 23 2016

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተከስቷል በተባለ የኮሌራ በሽታ ሳቢያ ከአራት መቶ የማያንሱ ተማሪዎች መያዛቸውን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4d6OA
Somalia | Hauptstadt der somalischen Region Jijiga
ምስል Mesay Teklu/DW

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተማሪዎች በኮሌራ ሳይያዙ አይቀሩም ተባለ

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተከስቷል በተባለ የኮሌራ በሽታ ሳቢያ ከአራት መቶ የማያንሱ ተማሪዎች መያዛቸውን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ።

ከተከሰተ አንድ ሳምንት ግድም ሆኖታል ስለተባለው ኮሌራም ሆነ በበሽታው ሳቢያ ስለደረሰ ጉዳት ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከክልሉ ጤና ቢሮ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።

በድሬዳዋ ኮሌራ 3 ሰዎች ገደለ

ይሁን እንጂ አስተያየት የሰጡ ተማሪዎች በበሽታው ተይዘው ህክምና ሲደረግላቸው ነበሩ ከተባሉ መካከል አንዳንዶቹ እያገገሙ መሆናቸው ተገልጧል።

በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አስተያየት ሰጪ በዩኒቨርሲቲው ከአንድ ሳምንት ቀደም ሲል ሰማን ባለው ኮሌራ ተይዘዋል የተባሉት ተማሪዎች ከሶስት መቶ የማያንሱ መሆናቸውን ገልጿል።

አሳሳቢዉ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል

ሌላኛው ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ በኮሌራ ተይዘዋል የተባሉት ተማሪዎች አሀዝ አራት መቶ ያህል መሆኑ እንዲሁም መንስኤው በአንድ በኩል "በውሀ ብክለት" በሌላ በኩል "የግል ንፅህና ባለመጠበቅ" የመጣ ነው ሲባል መስማቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

በዩኒቨርሲቲው ተከሰተ ስለተባለው ወረርሽኝ ለተማሪዎች በይፋ የተገለጸ ነገር አለመኖሩን ያነሳው አስተያየት ሰጪ ተማሪው በራሱ ለመጠንቀቅ እየጣረ ስለመሆኑ ጠቅሷል።

ተማሪዎች ወደ መመገቢያ አዳራሾች ሲገቡ ለጥንቃቄ እንዲታጠቡ ሲደረግ እንደነበር የጠቆመው ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ማስታገሻ ህክምና ያገኙ የተወሰኑ ልጆችም እያገገሙ ነው ብሏል።

በሐረሪ ክልል ኮሌራን ለመከላከል የውኃ ጉድጓዶች የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ

በዩኒቨርሲቲው ተከሰተ ከተባለው በሽታ ጋር በተያያዘ እስካሁን የሞተ ስለመኖሩ አለመስማታቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

ከተከሰተ አንድ ሳምንት ግድም ሆኖታል ስለተባለው ኮሌራም ሆነ በበሽታው ሳቢያ ስለደረሰ ጉዳት ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት የሞባይል ስልክ ባለመነሳቱ እና ባለመስራቱ ሳቢያ  ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። 

በሶማሌ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው ይኸው ዩኒቨርሲቲ ከቀናት በኃላ የተማሪዎች ምረቃ መርሀ ግብር እንደሚያከናውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መሳይ ተክሉ

ታምራት ዲንሳ