1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሪያድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ምኒስትር አብይ ድጋፋቸውን ገለጹ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 30 2010

በሳዑዲ ዓረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የጀመሩት የለውጥ መንገድ ከግብ እንዲደርስ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ አረጋገጡ፡፡ መንግስት ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ያቀረበው ጥያቄ በመርኃ-ግብሩ ተሳታፊዎች ዘንድ አወንታዊ ምላሽ አግኝቷል

https://p.dw.com/p/310Ri
Saudi-Arabien - Äthiopier in Riad
ምስል DW/S. Shibru

በሪያድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ

ሪያድ ዲፕሎማቲክ ኳርተር ተብሎ የሚታወቀው የኤምባሲዎች መገኛ ቅጽር እንደ ትላንት ምሽት በኢትዮጵያዊያን ተጨናንቆ አያውቅም ፡፡ ኢትዮጵያን በለውጥ መንገድ እየመሩ ላሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ኣብይ አሕመድ ጉዞ ድጋፋቸውን ለማሳየት እና የለውጡ ሂደት አካል መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጭምር ነው ኢትዮጵያዊያኑ የወቅቱን የሳዑዲ ዓረቢ ከፍተኛ ሙቀት ችላ ብለው የኤምባሲውን ቅጥር የሞሉት፡፡

ኢትዮጵያዊያኑ ለአክሱም ሙስሊሞች መብት ከሚጠይቁት ጀምሮ የተለያዩ ጽሁፎችን አዘጋጅተው በመያዝ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋፋቸውንም ሆነ ቀታይ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ አሰምተዋል፡፡ የተለያዩ ባንዲራዎችም ያለ ከልካይ በኤምባሲው ቅጽር በነጠላም ሆነ በጋራ ተውለብልበዋል፡፡

አቶ አብዱረሂም አህመድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራ እን የቆንስላ ጉዳዮች ኃላፊ የለውጡ መርህ የሆነውን መደመር ስለሚለው ጽንሰ ኃሳብ  ማብራሪ ሰጥተዋል፡፡

በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ወይዘሩ መዲና ኢብራሂም በበኩላቸው ያለፉት ሶስት ወራት ተስፋ የማንቆርጥባት ኢትዮጵያ እውን እየሆነች መምጣቷን አመላካች እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Saudi-Arabien - Äthiopier in Riad
ምስል DW/S. Shibru

የኢትዮጵያን መንግስት አንዳንድ ድርጊቶች እና ተጋባሮች በጽኑ በመንቀፋቸው ሳቢያ ሀገር እንዳይገቡ የተደረጉት ሼህ ሰይድ አህመድ ሙስጠፋም ከምሽቱ የመድረክ ተናጋሪዎች ዋንኛው ነበሩ በሪያድም ሆነ በመላው ሳዑዲ ኣረቢያ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሼክ ሰዒድ ያለፉት 3 ወራት ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ክስተቶች እውነት የሆኑበት ፣ ኢትዮጵያም እጅግ አበረታች የሚባል መስመር የዘረጋችበት እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

ጠቅላ ሚንስትር ዓብይ ለፓርላማው ትላንት ባቀረቡት የባጀት ማብራሪያ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ላቀረቡት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጥቄም በጎ ማላሽ መስጠት እንደሚገባ ሼክ ሰዒድ አስገንዝበዋል፡፡

የተለያዩ ቀስቃሽ ሙዚቃዎችም እለቱን ታዳሚዎች ሲዝናኑ አምሽተዋል ፡፡

ስለሺ ሽብሩ

እሸቴ በቀለ