1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ጥረቶች 

ረቡዕ፣ ሰኔ 10 2012

የአፈር ለምነት ማጣት በዓለም በ3.2 ቢሊየን ሕዝቦች ኑሮ ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን የተመድ አመልክቷል። ከደረሰው ጉዳት 70 በመቶው በሰዎች እንቅስቃሴ የመጣ በመሆኑ ሰዎች ተፈጥሮን የሚይዙበትን መንገድ በማስተካከል ለትውልድ የተሻለች ምድርን ማስረከብ እንዳለባቸው ታስቦ በዋለው በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ቀን መልእክቶች ተላልፈዋል።

https://p.dw.com/p/3dvy8
DW - eco@africa: Nigerianische Farmer und der Klimawandel
ምስል DW

በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ቀን 2020

ዛሬ በመላው ዓለም የአፈር ለምነትን ማጣትና በረሃማነትን ለመግታት ሊደረጉ የሚገባ ጥረቶችን ያመላከቱ መልእክቶች የሚተላለፍበት ዕለት ነው። በረሃማነትን አስወግዶ ድርቅን ለመቋቋም ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን ማናቸውንም ነገሮች ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንዲያደርጉ ይመከራል።  የአፈር ለምነት ማጣት በመላው ዓለም በ3,2 ቢሊየን ሕዝቦች ኑሮ ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን የተመድ አመልክቷል። በዚህ ረገድ ከደረሰው ጉዳት 70 በመቶው በሰዎች እንቅስቃሴ የመጣ በመሆኑ ሰዎች ተፈጥሮን የሚይዙበትን መንገድ በማስተካከል ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ምድርን ማስረከብ እንዳለባቸው ዛሬ ታስቦ በዋለው በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ቀን መልእክቶች ተላልፈዋል። በደን መራቆትና የአፈር ለምነት መመናመን አፍሪቃ በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቷ ተገልጿል። በአንጻሩ ደኖችን በማልማት ከበረሃማነት ያገገሙ ቦታዎችም አሉ። 

የተመድ በረሃማነትን የመከላከል ስምምነት ዋና ጸሐፊ ኢብራሂም ቲያው እንደሚሉት የዓለም ሕዝብ ለመኖሪያ ያለው ፕላኔት አንድ እንደመሆኑ ከተፈጥሮ ሃብት መራቆት ወይም ድርቅ የሚያመልጥ ማንም የለም። አሁን ባለው ይዞታ በመላው ዓለም ካለው መሬት ከሦስት እጅ የሚልጠው ለበረሃማነት በሚያጋላጥ መልኩ የተፈጥሮ ሃብቱ መመዝበሩን በማመልከትም በዚህ ረገድ በተለይ የአፍሪቃ መሬት በስፋት መጎዳቱን አመልክተዋል። በሕዝብ ብዛት ደረጃ ደግሞ እስያ ውስጥ እጅግ በርጃታ ሕዝብ በዚህ ችግር ምክንያት ተጎድቷል። የተፈጥሮ ሃብት መመናመን የሰዎችን ጤና፤ ኤኮኖሚ እና ደግህነን እንደሚጎዳ ያመለከተው የተመድ አልፎ ተርፎም ሰዎችን ለስደት እንደሚዳርግም ያስረዳል። ዕለቱን አስመልክተው የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባስተላለፉት መልእክት ይህንኑ አጉልተዋል። 

China | Aufforstung | Peking
ምስል picture-alliance/dpa/Xinhua News Agency

«ሰብዓዊ ጤንነት በመሬታችን ጤንነት ላይ ጥገኛ ነው። ዛሬ መሬታችን ታማለች። የመሬት የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ወደ3,5 ቢሊየን ገደማ ሰዎችን እየጎዳ ነው። 70 በመቶ የሚሆነው የመሬት የተፈጥሮ ሃብት በሰዎች እንቅስቃሴ ምክንያት እየተለወጠ ነው። ይህን ችግር በመቀልበስ ተገድዶ መሰደድና ረሃብን ጨምሮ እጅግ ለበረከታ ተግዳሮቶች መፍትሄ ማምጣት እንችላለን። በአፍሪቃ የሳህል አካባቢ ታላቁ አረንግዴ ግንብ ከሴኔጋል አንስቶ እስከ ጅቡቲ ድረስ የበርካቶችን ሕይወት እየለወጠ ነው።  100 ሚሊየን ሄክታር አካባቢ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ተችሏል፤ ኗሪዎች ከስደት አምልጠው የሥራ ዕድሎጽ ተፈጥረዋል።»

 ይህ ጥረትም በዚህ በረሃማ አካባቢ ብዝሃ ሕይወት  መልሶ እንዲበረካት ከማድጉ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ የኅብረተሰቡ ኑሮ ዳግም እንዲቋቋም ማገዙንም ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል። ዛሬ ታስቦ በዋለው በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ዕለት መልእክታቸው ጉተረሽ አክለውም ለቀጣዩ ትውልድ ጥቅም ሲባል ተፈጥሮን መሠረት ያደረጉ መፍትሄዎችን በመጠቀም የመሬትን የተፈጥሮ ሃብት መጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። በደን መመናመንና በአፈር መሸርሸር መሬታቸው ከተጎዳ የአፍሪቃ ሃገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። በአንዳንድ አካባቢ የተጎዳው መሬት መልሶ እንዲያገግም ከንክኪ በማግለል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ይናገራሉ። ከ2000 ዓ,ም መባቻ ጀምሮ በዘመቻ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች እየተተከሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት በ12 ሰዓታት ውስጥ 354 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሪከርድ አስመዝግባለች። ዘንድሮም አምስት ቢሊየን ችግኞችን የመትከል እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በአራት ዓመት 20 ቢሊየን የመትከል ዕቅድም ተይዟል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የሚታሰበውን በረሃማነትና ድርቅን የመከላከል ዕለት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛው ዘዴ ባስተላለፉት መልእክት «የደን ምንጣሮ እና የአየር ንብረት ለውጥ ከሌሎች መንስኤዎች ጋር ተዳምረው በየዓመቱ በኢትዮጵያ የለም አፈር መሸርሸርን ያስከትላሉ፣ ጫካዎችን እና ለምለም ሜዳዎችን ያመናምናሉ። የአረንጓዴ አሻራ አንዱ ግብ ይህንን እጦት መቀልበስ ነው።» በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም አረንጓዴ አሻራውን እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል። አረንጓዴ አሻራ የማኖሩ ተነሳሽነት የተጎሳቆለውን ተፈጥሮ መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ የታለመ ነው። በተመሳሳይ በመላው ዓለም ከ80 የሚበልጡ ሃገራት እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ድረስ 400 ሚሊየን ሄክታር መሬት ዳግም የተፈጥሮ ይዞታውን እንዲያገኝ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። እንዲህ ያለው ተግባር በባለሙያዎች ወይም በተፈጥሮ ወዳጆች ወይም በሳይንቲስቶች የሚከናወን ነው ተብሎ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ሊሳተፍበት እንደሚገባ የተመድ አሳስቧል።

Äthiopien Hawassa | Premierminister | Abiy Ahmed
ምስል DW/S. Wegayehu

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ