1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ወለጋ ተፈናቃዮች ስጋት ላይ መሆናቸዉን ተናገሩ

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2015

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዩ ወረዳ አኖ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ተናገሩ፡፡ በጎቡ ሰዩ ወረዳ የነበሩ በመቶዎች የሞቆጠሩ ነዋሪዎች ከጥቃቱ ወዲህ አካባቢውን ለቀው መሄዳቸው ተመልክቷል፡፡ የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት በጎቡ ሰዩ 5 ሺ የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸዉን ገልጿል፡፡

https://p.dw.com/p/4NnPq
Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

«በጎቡ ሰዩ ወረዳ አኖ ከተማ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ደብረብርሃን ሸሽተዋል»

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዩ ወረዳ አኖ ከተማ ጥር 25/2015 ዓ.ም ጥቃት ወዲህ በርካቶች አካባቢውን ለቀው ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ መሄዳቸው ተገልጸዋል፡፡  በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የተፈናቀሉ  ወይም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሁንም በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ በመቶዎች የሞቆጠሩ  በጎቡ ሰዩ ወረዳ የነበሩ ነዋሪዎች ከጥቃቱ ወዲህ አካባቢውን ለቀው መሄዳቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡  የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ወይም በአዲሱ ስያሜው "ቡሳ ጉኖፋ" ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ  በጎቡ ሰዩ 5 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙህዲን ኢስማኤል  በጎቡ ሰዩ ወረዳ አኖ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን ጥር 25/2015 ዓ.ም በወረዳው ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ወደ ደብረብርሀን መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡ በጎቡ ሰዩ የአካባቢውን ሠላም ለማስከበር የጸጥታ ሀይሎች ቢመደቡም ሰዎች በስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ስፍራ እየሄዱ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በጥቃቱ ወቅት ንብታቸው መውደሙንና 2 ልጆቻውን ይዞ ወደ ደብረ ብርሀን መሄዳቸውን አመልክተዋል፡፡

ለደህንነታቸውን ስለምሰጉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው የአኖ ከተማ   ነዋሪም በከተማው ውስጥ ንብረታቸው የወደመና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ በወረዳው የሚገኙ ጸጥታ ሐይሎች ለስራ በሚንቀሳቀሱት ወቅት ድንገት በታጣቂዎች ጥቃት ሊደርስብን ይችላል በሚል ስጋት ሰዎች እንደሚሸሹም ገልጸዋል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ወደ አምቦና ደብረብርሀን መሄዳቸው እንዲሁም ሌሎች ደግሞ በጸጥታ ሀይሎቸ እንዳይሄዱ መመለሳቸውን አክለዋል፡፡

Äthiopien | Binnenvertriebene aus der Oromia Region in Debre Birhan
ፎቶ ማህደር፤ ከኦሮምያ ተፈናቅለዉ ባህርዳር የሚገኙ ነዋሪዎችምስል North Shewa Zone communication Office

በጎቡ ሰዩ ወረዳ አኖ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የሲንቄ ባንክ ባልደረባ የሆነውን ወንድማቸውን  ጥር 25/2015 ዓ.ም በነበረው ጥቃት ማጣታቸውን የነገሩን ሌላው ነዋሪም ምንም ሰብአዊ ድጋፍ እንደላገኙ ተናግረዋል፡፡ በከተማው አሁን ምንም የጸጥታ ችግር ባይኖርም የሰዎች እንቅስቀሳሴ ግን የተገደበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

.. ብዙም እንቅስቃሴ የለም ሰዎች በፍርሀት ነው እየኖሩ የሚገኙት፡፡ የጸጥታ ችግር ከተፈጠረ ወዲህ ሰዎች እየተጠያየቁ አይደለም፡፡  ወድንሜ ሲንቄ ባንክ ይሰራ ነበር በዕለቱ በጥይት ነወ ተመቶ ህይወቱ ያለፈው፡፡ ሰብአዊ ድጋፍም በእጀባም ቢሆን እንዲመጣልን ጠይቀን ነበር እስካሁን የደረሰብ የለም ብለዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ወይም ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ በጎቡ ሰዩ፣በጊዳ አያና እና ኪረሙ ለሚገኙ ለተፈናቀሉ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ በዞኑና ቀይ መስቀል በኩል ተልእኮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር አንጻር ሰብዊ ድጋፍ በቂ ላይሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በጎቡ ሰዩ ወረዳ ከ5ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደበርም ተናግረዋል፡፡

..የጸጥታ ችግር በተደጋገመባቸው እንደ ኪረሙ ፣ ጊዳ አያና እና ጎቡ ሰዩ ወረዳን ጨምሮ ከጥቅምት ወር መጨረሻ አንስቶ 120 ሺ ሰዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡ በጎቡ ሰዩ አኖ ከተማ አሁን ከ5 ሺ እስከ 6ሺ የሚደርሱ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ ሰብአዊ ደጋፍን በተመለከተም በዞኑ አስተዳደር፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችም እንደ ዎርልድ ቪዥን፣ እንደ ሰቪ ዘ ችልድረን ያሉ ተቋማትና ቀይመስቀል ባደረጉልን እገዛ  ድጋፍ ለማድርስ ጥረት አድረገናል፡፡ ድጋፉ ከተፈነቃይ ቁጥር አንጻር ግን በቂ ነው ብለን አናምን ብለዋል፡፡

 በምስራቅ ወለጋ በተለያዩ ጊዜ በተከሰቱት የጸጥታ ችግሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ሲዘገብ ቆይተዋል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ከ7 መቶ ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከዘህ በፈት ያወጣው ረፖርት ያመለክታል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ