1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመደመር የተቀጨው አብዮታዊ ዴሞክራሲ

ዓርብ፣ ኅዳር 5 2012

የኢሕአዴግ መክሰም ነገር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር። ከዓመታት በፊት ኢሕአዴግ “የሽግግር” በተባለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ከፈጠረ በኋላ ኢሕአዴግ ከስሞ ‘የሶሻል ዴሞክራሲ’ ወይም ‘የሊበራል ዴሞክራሲ’ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል አዲስ ፓርቲ ይሆናል የሚል ዕቅድ ነበረው።

https://p.dw.com/p/3T5Pu
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

የኢሕአዴግ መክሰም ነገር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር። ከዓመታት በፊት ኢሕአዴግ “የሽግግር” በተባለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ከፈጠረ በኋላ ኢሕአዴግ ከስሞ ‘የሶሻል ዴሞክራሲ’ ወይም ‘የሊበራል ዴሞክራሲ’ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል አዲስ ፓርቲ ይሆናል የሚል ዕቅድ ነበረው። ለዚህ ዕቅዱ ምናልባትም እስከ አርባ ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል የፓርቲው መሪዎች ሲናገሩ ከርመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ባሳተሙት “መደመር” በተሰኘ መጽሐፋቸው ካቀረቧቸው ትችቶች አንዱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ “የሽግግር” ርዕዮተ ዓለም ተብሎ ሲያበቃ፥ ዘላቂ እና ቋሚ ሆኖ ቀረበ የሚል አለበት። በዚሁ መሠረት እና ባልተጠበቀው ሕዝባዊ ማዕበል የተገፋው የኀይል ሚዛን መዛወር (power-shift) የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ቀን ያሳጠረው ይመሥላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚደገፈው የኢሕአዴግ ቡድን ኢሕአዴግን አክስሞ አንድ ውሕድ ፓርቲ ሊመሠርት ቅድመ ዝግጅት ላይ ነው።

የፓርቲዎች ውሕደት በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሒደት አነጋጋሪ ሲሆን ይህ ሁለተኛው ነው። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምሥረታን ተከትሎ ሲሆን፣ የአሁኑ ደግሞ የኢሕአዴግ መዋሐድ ቀድሞ ነው። ኢዜማ ሲመሠረት ‘ውሕደት’ ይባል እንጂ፥ ቀድሞ ሕልውና የነበራቸው ፓርቲዎች (ለምሳሌ በምርጫ ቦርድ የተመዘገበው ሰማያዊ ፓርቲ እና ያልተመዘገበው አርበኞች ግንቦት ሰባት) ራሳቸውን አክስመው እና አባላታቸውን በትነው ሲያበቁ፣ ነጠላ አባላቱ ኢዜማን የመሠረቱት የምርጫ ወረዳዎች መዋቅር ውስጥ በየፊናቸው በመግባት አዲሱን ፓርቲ መሥርተዋል። የኢዜማ የምዝገባ ሒደት የሚያሳየውም አዲስ ፓርቲ ተብሎ መመዝገቡን እንጂ ውሕድ ፓርቲ በሚል አለመሆኑ ታውቋል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ከፊል አባላት ፓርቲያችን አልከሰመም የሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም፣ እንዳዲስ ምዝገባ ላይ ላለው ኢዜማ ሕልውና የሚያሰጉ መሆን አልቻሉም። የኢሕአዴግስ ውሕደት ምን ዓይነት ነው? እንደ ኢዜማ እንደ አዲስ ፓርቲ ይመዘገባል ወይስ በፓርቲዎች ሕግ መሠረት ይዋሐዳል?

የኢሕአዴግ አባላት ይከስማሉ?

አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ እንደሚገልጸው ፓርቲዎች ለመዋሐድ ከወሰኑ፣ ምርጫ ቦርድ “ለተዋሐዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰጥቶ የነበረውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ይሰርዛል።” ከዚህ በፊት ግን እያንዳንዱ ለመዋሐድ የፈለጉ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት [ጠቅላላ] ጉባዔያቸው ውሕደቱን መቀበል አለበት። ይህንን የውሕደት ጥያቄ እየተቃወሙ ያሉት ሕወሓት እና አንዳንድ የኦዴፓ አባላት ናቸው። በተለይም ኦዴፓ በፓርቲ ልሳኑ “ኢሕአዴግ አሁን ያለበት ሁኔታ እንኳን ለውሕደት ለግንባርነትም አይመጥንም” የሚል የሰላ ትችት ካቀረበ በኋላ ይከስማል ብሎ መጠበቅ የዋሕነት እየመሰለ ነው። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትም የሕወሓት አዲሱ ውሕድ ፓርቲ ውስጥ መግባት አለመግባት ጉዳይ ያሳሰበው አይመስልም። ምክንያቱም ‘ብዙኀኑ ከኔ ጋር ናቸው’ የሚል እምነት ላይ ተመሥርቶ ይመስላል።

ውሕዱ ፓርቲ ሊመሠረት የሚችልባቸው ሁለት መንገዶች ናቸው። የመጀመሪያው እያንዳንዳቸው አባል ፓርቲዎቹ እና አሁን አካትታቸዋለሁ የሚሏቸው አጋር ፓርቲዎች በጉባዔያቸው የውሕዱ ፓርቲ አባል ሆነው ለመክሰም ከተስማሙ ነው። አዴፓ በይፋ ከስሞ ውሕዱ ፓርቲ ውስጥ ለመግባት መወሰኑን ተናግሯል። ከሕወሓት በቀር ቀሪዎቹ ሁለት የኢሕአዴግ አባላት እና አጋር ፓርቲዎቹም አካሔዳቸው ወደዚህ ይመስላል። በዚህ መልኩ ሕወሓት ከስሞ ለመዋሐድ ባይስማማም አዲሱ ፓርቲ ውስጥ ባለመግባቱ ፌዴራሉ ውስጥ የገዢ ፓርቲነቱን በፈቃዱ ያጣል እንደማለት ነው። በውጤቱም ኢሕአዴግ ቀሪዎቹ አባላቱን በማጣቱ በራሱ ሰዓት ይከስማል። ሕወሓት የአንድ ክልል ገዢ ፓርቲ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ የሚቀጥልበት አጋጣሚ ይፈጠራል ማለት ነው። በተግባር በኢሕአዴግ እና በሕወሓት መሐከል ያለው ግንኙነት አሁንም ቢሆን እንደዚያው ነው። 

በሌላ በኩል አዲሱ ፓርቲ ሊመሠረት የሚችለው እንደ ውሕድ ፓርቲ ሳይሆን ልክ እንደ ኢዜማ በአዲስ ፓርቲነት በመመዝገብ ነው። ይህ አማራጭ ሊከሰት የሚችለው አባል ፓርቲዎቹ በጉባዔያቸው ፓርቲዎቻቸውን ለማክሰም የሚያስችል ድምፅ ካላገኙ ነው። በአዋጁ እንደተደነገገው በተለይም ኦዴፓ ውስጥ ያለው የውሕደቱ ተቃውሞ ከፍ ያለ ከሆነ እና ጉባዔው ውስጥ በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት አስፈላጊው ድምፅ ካልተሰጠበት አዲሱን ፓርቲ የሚመርጡ አባላት በገዛ ፈቃዳቸው ፓርቲዎቻቸውን እየለቀቁ አዲሱን ፓርቲ ሊቀላቀሉ ይችላሉ። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ያሉ የኦዲፒም ይሁኑ ሌሎች አባላት ፓርቲዎቻቸውን እየለቀቁ አዲሱን ፓርቲ ከተቀላቀሉ ቀሪዎቹ እጃቸው ላይ የሚተርፈው የተዳከመ እና የገዢ ፓርቲነት ማዕረጉን ያጣ ፓርቲ ነው። 

በሁለቱም ሁኔታዎች ብዙዎቹ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች እና አባል ግለሰቦቻቸው አዲሱን ፓርቲ መምረጣቸው እና አዲሱ ፓርቲም የገዢ ፓርቲ ሆኖ፣ ቢያንስ እስከመጪው ምርጫ እንደሚቀጥል መገመት ይቻላል። የሆነ ሆኖ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ለኢዜአ ትላንት እንደተናገሩት ከሆነ ውሕደቱ በግንባሩ ውስጥ በድምፅ ብልጫ እንደማይወሰን እና እያንዳንዱ አባል ፓርቲ ወይም አጋር ፓርቲ በራሱ ወስኖ ይዋሐዳል ወይም ይቀራል ብለዋል። ይህም፣ የውሕደቱ ሐሳብ አራማጆች የፈለገ ይምጣ፣ ያልፈለገ ይቅር የሚሉበት የመተማመን ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያመላክት ነው። 

የመደመር ቡጢ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመደመር ዕሳቤ የአዲሱ [ውሕድ] ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም እንደሚሆን ይጠበቃል። መደመር የሚለው ቃል የአዲሱ ፓርቲ ማኒፌስቶ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ላይ ቢጠቃቀስም ርዕዮተ ዓለም ተብሎ እንዳልተጠቀሰ ሰነዱን አይተነዋል ያሉ ሰዎች ይናገራሉ። ነገር ግን የፓርቲው የአስተሳሰብ ቅኝት በመጽሐፉ የተለየ ነው ተብሎ አይጠበቅም። ይሁን እንጂ ይህ የመደመር ዕሳቤ ሕወሓትን መጨመር አልተሳካለትም። እንዲያውም የእስካሁኑ አካሔድ የሚያሳየው “እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” የሚያስብል ዓይነት ነው። ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ለኢዜአ የሰጡትን አስተያየትም ስንመለከተው ሕወሓት በራሱ ፈቃድ ከውሕዱ ፓርቲ እንዲሰናበት መንገድ እያመላከቱት ይመስላል። 

ውሕደቱን የማይፈልጉ ወይም ውሕዱ/አዲሱ ፓርቲ የሚመራበትን ርዕዮት ያልፈለጉ የኢሕአዴግ አባላትም የሚደርሳቸው ዕጣ ፈንታ ከሕወሓት የተለየ አይደለም። ይህ የገዢ ፓርቲነትን ድርሻ በፖለቲካዊ ጫወታ የመነጠቅ ቁጭት ግን መልሶ ሊጎዳ እንደሚችል መገመት አይከብድም። እነዚህ ተሰናባቾች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ጥረታቸውን ሊያደርጉ ይችላሉ። አዲሱ ፓርቲ እስኪመሠረት ድረስ በዚህ ሳቢያ ብዙ ፖለቲካዊ መንገጫገጮች እና ግጭቶ ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ መሐል ጊዜው ይነጉዳል። ዛሬ ላይ እንኳን ሆነን ብናስበው የ2012ቱ ምርጫ ሊካሔድ የቀረው ጊዜ በተለመደው ግንቦት ወር ካሰብነው ስድስት ወር ብቻ ነው። የምርጫ አዋጁ ደግሞ ፓርቲዎቹ ሊዋሐዱ ከወሰኑ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ሁለት ወር ቀድመው ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ አለባቸው ይላል። ይቀናቸው ይሆን?  

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም!

በፍቃዱ ኃይሉ