1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመንግሥት ላይ የቀረበ አቤቱታ

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2015

በመንግሥት መዋቅር ይደረጋል ያለውን መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ለአፍሪቃ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን አቤቱታ ማቅረቡን የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ አስታወቀ። ማኀበሩ አቤቱታውን ያቀረበው ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4NtHN
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

በመንግሥት ላይ አቤቱታ መቅረቡ

 

ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸዉ የማኀበሩ አድቮኬሲ ዳይሬክተር አቶ ሆነ ማንደፍሮ እንደሚሉት፣አቤቱታው በኦሮሚያ ክልል በዐማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የተመለከተ ነው። « በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዐማራዎች በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው ነው። የሰብአዊ መብት ጥሰቱን የሚፈፀሙት አካላቶች መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ ወይም በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውጭ ያሉ ነገር ግን በመንግሥት መዋቅሩ በኦሮሚያ ክልል በተለይ የፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ የሚደረግላቸው የኦነግ ሸኔ አባላቶች በተደጋጋሚ፣ እዛ አካባቢ በተለይም ወለጋ አካባቢ የሚገኙ አምስት ዞኖች ላይ ያተኮረ ነው። እዛ ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዶክመንት አድርጎ እነዚህን በማውጣት ሰብዓዊ ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ወይም ደግሞ እንዳይፈጸሙ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍሪቃ ህብረት አባላትና በአፍሪቃ ህብረት የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽን የፈረመውን ኃላፊነት አልተወጣም የሚል ክስ ነው ያስገባነው።»

ቅሬታው፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ባሏቸው ኃይሎች አማካይነት በዋናነት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋና መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይዳስስ እንጂ ወደ ኋላ ተመለሶ ከ1980ዎቹ ዓም ጀምሮ የተሰነዱ ጉዳዮችን ሁሉ የሚመለከት እንደሆነ አቶ ሆነ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ክልል የሚደርሱ፣ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎችን የሚያጋልጡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እና ማኀበራዊ አንቂዎች ላይ እንዲሁም ተቃውሞአቸውን በሰልፍ እና በሌሎች ሰላማዊ መንገዶች ለመግለጽ በሚሞክሩ የማኀበረሰብ ክፍሎች ላይ የመንግሥት ኃይሎች አፈና ግድያና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እየፈጸሙ እንደሚገኙ አቤቱታው አትቷል።

እንዲሁም ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በሚፈጽሙበት ጊዜ እና ከተፈጸሙ በኋላ መረጃዎች እንዳይወጡ ለማድረግ፣ በመንግሥት በኩል የግንኙነት አገልግሎቶች ማለትም የስልክና የበይነ መረብ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጋቸውን ዘርዝሯል።

USA Hone Mandefro
ምስል Tariku Hailu/DW

እነዚህና ሌሎች ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈፀሙ፣ መንግሥት በድርጊቶቹም ሆነ ባሳየዉ ዳተኝነት ሳቢያ፣ በአፍሪቃ የሰዎች እና ህዝቦች ቻርተር ዕውቅና የተሰጣቸውን መብቶችና ነፃነቶች ከማስከበር አንፃር፣ የተጣለበትን ግዴታ ሳይወጣ በመቅረቱ ተጠያቂነት እንዳለበት በቀረበው አቤቱታ ላይ ተገልጿል። ቅሬታው ስለቀረበለት፣ የአፍሪቃ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን የጠቅናቸው ዳሬክተሩ ሲገልጹ፤ «የሰብዓዊና የህዝቦች መብት ኮሚሽን የሚባል አለ። እሱ ኮሚሽን እንደ ፍርድ ቤት ነገር ነው የሚያገለግለው እና አባል አገሮች አቤቱታ ያስገባሉ፣ ከዚያም የተከሰሰው ሃገር መልስ ይሰጣ፤ እንደዛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የአፍሪቃ ህብረት ዋና ጠንካራ ኮሚሽን ነው የራሱም የሆነ ምርመራዎች ይሰራል አልፎ አልፎ። እዚያ የሚያገኘውን ጉዳዮችን ተቀበሎ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።» ነው ያሉት። የኮሚሽኑ መቀመጫ በ ጋምቢያ ዋና ከተማ ባንጁል ሲሆን፣ በየስድስት ዓመቱ ባላቸው ስነ ምግባርና መልካም ስም፣በሰብዓዊ መብቶች መስክ ባላቸው ችሎታና የሕግ ልምድ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ የባንጁል ስምምነትን ከተቀበሉ የአፍሪቃ አገሮች፣ በሚመረጡ ባለሙያዎች፣ የተዋቀረና ተቋም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በዚህ አቤቱታ ላይ ስሙ የተጠቀሰውና መንግሥት «ኦነግ ሸኔ» ሲል በአሸባሪነት የፈረጀው፣ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለው ድርጅች ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ከዚህ ቀደም በዶይቸ ቨለ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ጥቃቶቹን የዐማራ ኃይሎች ናቸው የሚፈጽሟቿው በማለት ማስተባበላቸው አይዘነጋም። የዐማራ ማኀበር በአሜሪካ ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ጋር በመተባበር ባቀረበው አቤቱታ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት አስተያየት ለማካተት፣ለኮሙኒኬሽን አገልግሎት መሥሪያ ቤት የሥራ ኀላፊ ደውለን ጥያቄ ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።

ታሪኩ ኃይሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ