1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐጫሉ ሞት የተቀሰቀሰው ቀውስ ወዴት እያመራ ነው?

እሑድ፣ ሰኔ 28 2012

ከድምፃዊ ሐጫሉ ግድያ በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ እየተባባሰ ሔዷል። ካለፈው ማክሰኞ ወዲህ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 156 ደርሷል፤ 165 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ 1084 ሰዎች ታስረዋል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ቀውስ ወዴት እያመራ ነው?

https://p.dw.com/p/3epbK
Äthiopien Rauch über Addis Abeba nach der Ermordung von Hachalu Hundessa
ምስል Reuters/Str

ከዶክተር አደም ካሴ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

ከድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የተከሰተው ቀውስ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ  “የርስ በርስ ጦርነት የመቀስቀስ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ለረዥም ጊዜ ሲታቀድ፤ ሲታሰብ የቆየ” ውጥን ነው ብለዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ወታደራዊ መለዮ ለብሰው ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ባደረጉት ውይይት “በመሳሪያ፣ በሚዲያ እና በገንዘብ” የተቀናጀ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ከድምፃዊው ሞት በኋላ በተለይ በኦሮሞ ፖለቲካ ከፍተኛ ተደማጭበት ያላቸው የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መሪ እስክንድር ነጋ ታስረዋል።

የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጆች በማኅበራዊ ድረ ገፆች በጀመሩት ዘመቻ ጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ነው። ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ ገፆች በሚካሔደው ዘመቻ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ፣ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአፋጣኝ ሥልጣን እንዲለቁ፣ የዘፈቀደ ግድያዎች ይቁሙ የሚሉት ይገኙበታል። ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፤ በሚቀጥሉት አምስት ወራት ነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫ እንዲካሔድ፤ የተቋረጠ የኢንተርኔት እና የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲመለስ የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል። እነዚህ ጉዳዮች መልስ ካልተሰጣቸው በጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣልም ግፊት ያደርጋል። 

በአሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ አገሮች ባለፉት ተከታታይ ቀናት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት የሚተቹ ተቃውሞዎች እየተደረጉ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገፆች መቃቃሩ መበርታቱን የሚጠቁሙ መልዕክቶች ይታያሉ። በጉዳዩ ላይ የሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦች ልዩነቱ መክረሩን መቃቃሩ መበርታቱን ይጠቁማሉ። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ለመሆኑ በሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተቀሰቀሰው ቀውስ ወዴት እያመራ ነው? የሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አደም ካሴ ስለ ጉዳዩ አነጋግሪያቸዋለሁ።

እሸቴ በቀለ