1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐዋሳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ጽንስ ማቋረጥን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሔደ

ሰኞ፣ ሰኔ 26 2015

በሐዋሳ ከተማ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ጽንስ ማቋረጥን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሒዷል። ሰልፉን ያዘጋጁት በከተማዋ ከሚገኙ 22 የቃለ ሕይወት አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያናት የተውጣጡ ምዕምናን ናቸው። ሠልፈኞቹ ትላንት እሁድ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ ባሰሙት መፈክር የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ጽንስ ማቋረጥን አውግዘዋል።

https://p.dw.com/p/4TMWs
 Anti Homosexuality protest in Hawassa
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሐዋሳ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ጽንስ ማቋረጥን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሔደ

በሀዋሳ ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን እና የውርጃ ድርጊቶችን በሠላማዊ ሰልፍ አወገዙ ፡፡ በከተማው ጎዳናዎች በመዘዋወር የተቃውሞ ሠልፍ ያካሄዱት ነዋሪዎች ቁጥራቸው በብዙ ሺህ ይገመታል ፡፡

ሠልፈኞቹ በተመሳሳይ ፆታዊ ግንኙነት እና በውርጃ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ያሰሙት የጹሁፍ መልዕክቶችን በማንገብና መፈክሮችን በማሰማት ነው ፡፡ ሠልፈኞቹ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል “ ግብረ ሶዶማዊነትን እንቃወማለን “ ፣ “ ጽንስ ሕይወት አለው “ ፤ “ ህይወትን መግደል ሀጢያት ነው “ የሚሉ ይገኙባቸዋል ፡፡

የተመሳሳይ ጋብቻንና ውርጃን ለመቃወም እንደወጣ ለዶቼ ቬለ DW አስተያየቱን የሰጠው አማኑኤል መሀሪ “ድርጊቱ ቀደምሲል ያልተለመደ ቢሆንም አሁን ላይ ግን እየተስፋፋ ይገኛል ፡፡ ይህም በሥነ ምግባር የታነጸና ገብረ ገብነት ያለው ትውልድ አንዳይኖር እያደረገ ነው ፡፡ ትውልዱን ከዚህ አደጋ ለመታደግና   ድምፃችንን ለማሰማት ነው ወጣነው “ ብሏል፡፡

 Anti Homosexuality protest in Hawassa
ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰልፍ በሀዋሳምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የተቃውሞ ሠልፉን ያካሄዱት በሀዋሳ ከተማ ከ22 የቃለ ህይወት አጥቢያ ቤተክርስቲያናት የተሰባሰቡ ምዕመናን መሆናቸውን ከሠልፉ አስተባባሪዎች አንዱ መጋቢ ፍፁምዘለቀ ይናገራሉ ፡፡ ሠልፉ ያስፈለገበት ምክንያትም አገር ፣ ከተማ ፣ ህዝብ እንዲነቃ ለማድረግ መሆኑን የገለጹት መጋቢ ፍፁም “ ህዝቡ ጉዳዩን እንደተራ ነገር ሊያየው አይገባም ፡፡ አስከፊነቱን ሊረዳ ይገባል ፡፡ አዲስ ነገር አይደለም እየተባለ በማህበረሰቡ ውስጥ ሥፍራ እያገኘ ወጣቶችንም ከመንገድ እያስቀረ ይገኛል ፡፡ ሠልፉ ህብረተሰቡ ይህን እንዲውያቅ ለማድረግ የታሰበ ነው “ ብለዋል፡፡

የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትና የውርጃ ጉዳዮች ከህግና ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታይሉ ሲል ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ ብረሃኑ ጋኔቦ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ የተከለከለ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡ ውርጃን መፈጸምም ቢሆን ተመሳሳይ የህግ ክልከላ መኖሩን የጠቀሱት የህግ መምህርና ተመራማሪ ይሁንእንጂ  ሴቲቱ በአስገድዶ መድፈር ጋረገዘች ፣ ፅንሱ ለህይወቷ አስጊ ከሆነና በሌሎችም ምክንያቶች ውርጃ ሊፈቀድ የሚችልባቸው ሁኔታዎች በህጉ መዘርዘሩን አስረድተዋል ፡፡

 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ