1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊቢያ ምርጫ ማካሄድ ይቻል ይሆን?

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 27 2010

በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ የሚገኘው አስመራጩ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት የአሸባሪዎች ጥቃት ሆነ። ባለፈው ረቡዕ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ራሱን በጽህፈት ቤቱ ውስጥ በፈንጂ ባነጎደበት ጥቃት እና የአንድ የሚሊሺያ ቡድን አባላትም በጽህፈት ቤቱ ላይ በሰነዘሩት የቃጠሎ ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል።

https://p.dw.com/p/2xCIC
Kampf gegen IS in Libyen
ምስል picture-alliance/dpa

ሊቢያ

ይህ ጥቃት የተጣለው  የተመድ፣  የአፍሪቃ ህብረት፣ የዐረብ ሊግ እና  የአውሮጳ ህብረት የበሊቢያ መረጋጋት ማስገኘት ስለሚቻልበት ጉዳይ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በካይሮ ግብፅ ተገናኝተው ከመከሩ እና በሊቢያ ጎርጎሪዮሳዊው 2018 ሳያበቃ በፊት አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚጥሩ ካሳወቁ በኋላ ነበር። አስመራጩ ኮሚሽን ለዚሁ ይደረግ ይሆናል በሚል ለታሰበው አዲስ ምርጫ መራጮችን ይመዘግብ በነበረበት ጊዜ ነው የጥቃት ሰለባ የሆነው።

ሊቢያ የቀድሞው መሪዋ ሞአመር ጋዳፊ በ2011 ዓም በኔቶ በተደገፈ የህዝብ ዓመፅ  ከስልጣን ከተወገዱ እና ከተገደሉ ወዲህ መረጋጋት እንደተሳናት ትገናለች። የተመ ልዩ የሊብያ ልዑክ ጋሳን ሳላሜ፣ የአፍሪቃ ህብረት የማሊ እና የሳህል አካባቢ ሀገራት ከፍተኛ ተጠሪ ፒየር ቡዮያ ፣ የዐረብ ሊግ መሪ አህመድ አቡል ጌይት እና የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ ከምክክሩ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫቸው ሊቢያ በዚህ በተያዘው ጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓም ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ ማካሄድ ትችል ዘንድ  ድጋፍ  ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  በሊቢያ ሁኔታዎች ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ጀምሮ አዎንታዊ ለውጥ ማሳየታቸውን የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ አስታውቀዋል። «በርግጥ፣ ባለፉት ሰባት ወራት በሀገሪቱ መሻሻል አይተናል። ገና በሚገባ ያልተጠናከረ  ፣ የተወሰነ መሻሻል ። ይሁንና፣ ካለፉት ጊዚያት ጋር ሳነፃፅረው  አበረታቺ መስሎ ይታየኛል። ይህ መሻሻል ሊደገፍ ይገባዋል ባይ ነኝ። ይህ መጠነኛ መሻሻል ሊታይ የቻለውም  በድርጅቶቻችን መካከል የነበረውን ክፍፍል በማስወገዳችን እና  የጀመርነውን የተለያየ ስራችንን አጠናክረንና አስተባብረን መቀጠል በመቻላችን ይመስለኛል። »

Iatlien Asylbewerberlager bei Mineo auf Sizilien
ምስል picture alliance/dpa/B. Wegener

የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ፌዴሪካ ሞጌሪኒ አክለው እንዳስረዱትም፣ በሊቢያ ምርጫ እንዲደረግ ጥያቄው እየተጠናከረ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም  ብዙ ስደተኞች ወደየትውልድ ሀገራቸው በብዛት የተመለሱበት ድርጊት በሊቢያ ለታየው መሻሻል ድርሻ አበርክቷል። «በተለያዩ የሊቢያ ማጎሪያ ጣቢያዎች ታስረው ለነበሩ ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ስደተኞች ጉዳይ መፍትሔ ለማስገኘት ሁላችንም ባንድነት ለመስራት ቁርጠኝነት አሳይተናል። በሁለት ወር ውስጥ ብቻ ስደተኞች በፈቃዳቸው እንዲመለሱ ረድተናል፣ ማለትም፣ ከ16,000 የሚበልጡ ስደተኞች  ለአደጋ ሳይጋለጡ፣  በደህና እንዲመለሱ ርዳታ አድርገናል።  ይህ በጣም የሚሞገስ እና ቀደም ባሉ ዓመታት ያልታየ  ድርጊት ነው።»

በካይሮ የተሳተፉት የአራቱ ድርጅቶች ተጠሪዎች እንዳስታወቁት፣ እስካሁን ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ስደተኞች ከ16,000 ይበልጣሉ። 

Libyen General Chalifa Haftar
ጀነራል ሀፍታርምስል Imago/S. Savostyanov

በሊቢያ ዘንድሮ እንዲደረግ የታሰበው ምርጫ ሀገሪቱን ያረጋጋል  የሚል ተስፋ ማሳደሩን የዐረብ ሊግ መሪ አህመድ አቡል ጌይት ገልጸዋል። «እንደ የተመድ የሊቢያ ልዑክ አስተሳሰብ፣ በቀጣዮቹ ጊዜ ምርጫ ማካሄድ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ አትኩሮ መስራት ይገባል። ልዑኩ ፕሬዚደንታዊውን እና ምክር ቤታዊውን ምርጫ ዘንድሮ ባንድ ላይ ማድረግ እንደሚቻል እና የሚሳካበትም ጥሩ እድል እንዳለ ያምናሉ።  ዓመቱ ሊያበቃ ከስድስት እስከ ሰባት ወር ነው የቀረው፣ እና በሚቀጥሉት ቀሪዎቹ ወራት የምናደርገው ጥረት ከተሳካ፣  ይህ ርምጃችን፣  ምርጫ የሚደረግበትን  መንገድ  ይከፍታል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን ቀውሱ ይቀጥላል። »

ይሁን እንጂ፣ ምርጫ ማካሄድ አሁንም ሀገሪቱ ትልቅ ፈተና ሆኖባታል። «በሀገሪቱ፣ በተለይ በምዕራባዊው አካባቢ በርካታ ሚሊሺያ ቡድኖች መኖራቸውን አልረሳንም። ከነዚሁ ሚሊሺያ ቡድኖች አንዳንዶቹ የምርጫውን ሀሳብ ላይደግፉ ይችላሉ። ሁኔታዎች አሁን እንዳሉ ከሚቀጥሉበት ድርጊት ገንዘብ ማግኘት እና አቋማቸውን ማጠናከርን የመሳሰሉ  የሚያገኙት አንዳንድ ጥቅሞች ስላሉም፣ ምርጫውን ለማደናቀፍ ሊሰሩም ይችሉ ይሆናል።  ያም ቢሆን ግን፣ እኛ ምርጫው እንዲካሄድ ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። »ምርጫው ነፃ እና ትክክለኛ እንዲሆንም የምርጫ ታዛቢዎችን እና አስፈላጊ የምርጫ ርዳታ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ሊቢያውያንም የምርጫውን ውጤት እንዲያከብሩ ፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ሁከት እና የማስፈራራት ተግባር እንዲያስወግዱ አራቱ  ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሳስበዋል።  የተመድ ልዩ ለሊቢያ ቀውስ መፍትሔ ለማስገኘት በጀመሩት ጥረታቸው የተለያዩት ተቀናቃኝ ወገኖች ለፖለቲካዊው ውይይት እድል እንዲሰጡ ለማግባባት እና ምርጫ የማካሄዱ እቅድ እውን እንዲሆን  ሙከራቸውን ቀጥለዋል።  ይሁንና፣ በጦር ኃይሉ እና በፖለቲካ አንጃዎች በተከፋፈለች እና በ2014 ዓም ከተካሄደው ምርጫ ውጤት በኋላ ተቀናቃኝ  መንግሥታት ከጀመሩት የስልጣን ሽኩቻ ወዲህ   በሀገሪቱ ምርጫ ማካሄድ ዛሬም ዓቢይ ተግዳሮት እንደሆነ ይገኛል።   
ይህ ዓላማ በሀገሪቱ ባሉት የተለያዩ የሚሊሺያ ቡድኖች እና በምሥራቃዊ ሊቢያ ቁጥጥራቸውን ባጠናከሩት በጀነራል ሀፍታር በሚመራው የሊቢያ ብሄራዊ ጦር ሰበብ እስከዛሬ ግቡን ሊመታ አልቻለም።  ምንም እንኳን በመዲናይቱ ትሪፖሊ እና ሌሎች ከተሞች በታጣቂ ቡድኖች መካከል  ውጊያው ቢቀንስም በብዙ የሊቢያ አካባቢዎች የፀጥታው ሁኔታ አሁንም አስተማማኝ አለመሆኑ  ሀገሪቱ እንድታደርገው የሚፈለገውን የፖለቲካ ሽግግር ሂደት አዳጋች እንዳደረገው  የፖለቲካ ታዛቢዎች አመልክተዋል።

Karte Libyen Tobruk Deutsch

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ