1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵውያኑ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጡ

እሑድ፣ ሚያዝያ 14 2010

ዛሬ በተካሄደው የለንደን ማራቶን ውድድር በወንዶች ቶላ ሹራ ሁለተኛ ሲወጣ በሴቶች ደግሞ ታደለች በቀለ ሶስተኛ ሆናለች። ውድድሩን ያሸንፋሉ በሚል ሲጠበቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ አልቀናቸውም፡፡ ቀነኒሳ ውድድሩን በስድስተኛነት ሲያጠናቅቅ ጥሩነሽ ውድድሩን አቋርጣ ወጥታለች፡፡

https://p.dw.com/p/2wTZZ
UK London Marathon 2018 | Gewinner Eliud Kipchoge und Vivian Cheruiyot aus Kenia
ምስል picture-alliance/Xinhua/R. Washbrooke

ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ በለንደን ማራቶን አልቀናቸውም

በብሪታንያ ለንደን ዓመታዊው የማራቶን ውድድር በሀገሬው አቆጣጠር ረፋዱን ተካሄዷል፡፡ በዚህ ውድድር ያሸንፋሉ በሚል ሲጠበቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ድል ከእነሱ ጋር አልሆነም፡፡ ቀነኒሳ ውድድሩን በስድስተኛነት ሲያጠናቅቅ ጥሩነሽ ውድድሩን አቋርጣ ወጥታለች፡፡ ከውድድሩ በኋላ ቀነኒሳ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው ሩጫው ከጅማሬው አንስቶ መፍጠኑ ለውጤቱ መበላሸት ዋንኛው ምክንያት ነው።  

ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ እንዳሰቡት ባይሳካላቸውም በውድድሩ የተሳተፉት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከአሸናፊዎች ዝርዝር መግባት ችለዋል፡፡ ቶላ ሹራ ሁለተኛ ኬንያዊውን ኢሉውድ ኪፕቼጌን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል። ብሪታንያዊው ሞ ፋራህ በደጋፊዎቹ ፊት ሶስተኛ ሆኖ ጨርሷል። ሆኖም የብሪታንያን የማራቶን ሪከርድ ሰብሯል።

በሴቶች ድል የቀናቸው ኬንያውያን ሆነዋል። በአምስት ሺህ እና አስር ሺህ ሜትር ውድድር የኢትዮጵያውያን ብርቱ ተፎካካሪ የሆነችው ቪቪያን ቼሮይት የሀገሯን ልጅ ብሪጅድ ኮስጊን አስከትላ ገብታለች። ኢትዮጵያዊቷ ታደለች በቀለ ደግሞ ሶስተኛ ሆናለች፡፡

ውድድሩን በስፍራው ሆና ከተከታተለችው የለንደኗ ወኪላችን ሀና ደምሴ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሀና ደምሴ 

ተስፋለም ወልደየስ