1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሃገር በቀል ዕይታ ግብርናን ማዘመን

ሐሙስ፣ ሐምሌ 8 2013

በኢትዮጵያ በርካታ ሃገር በቀል ባህላዊ ዕውቀቶች አሉ። እነዚህን ዕውቀቶች በቅጡ ተገንዝቦና አጥንቶ ለሃገር ልማት ጠቀሜታ እንዲሰጡ ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ላይ ክፍተቶች አሉ። በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ባህላዊ የረቀቁ አስተሳሰቦችን የጋራ እሴት በማድረግ ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/3wTMm
Äthiopien Wanchi Ökotourismus
ምስል Seyoum Getu Hailu/DW

ሃገር በቀል ባህላዊ ዕውቀቶችን ማዘመን


በኢትዮጵያ በርካታ ሃገር በቀል ባህላዊ ዕውቀቶች አሉ። እነዚህን ዕውቀቶች በቅጡ ተገንዝቦና አጥንቶ ለሃገር ልማት ጠቀሜታ እንዲሰጡ ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ላይ ክፍተቶች አሉ። በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ማኀበራዊ የሥነ-ልቦናና ባህላዊ የረቀቁ አስተሳሰቦች የጋራ እሴት በማድረግና ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ። ከዚህ አኳያ በተውሶ ሳይሆን በሃገር በቀል ዕውቀትና መፍትሔዎች የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን አልሞ ስለተቋቋመው የሃገር በቀል ዕይታ መስራችና መሪ ዶክተር ፀደቀ አባተ እንዲሁም ከማህበሩ አባል ዶክተር ወርቅነህ አያሌው ጋር ቆይታ አድርገናል። 
"ስንነሳ የእኛ ዓላማ ለዚህች ሃገር መልሰን መስጠት የምንችለው ምንድን ነው? የሚለውን ይዘን ነው የተነሳነው። የምንችለውን እያደረግን ነው። እያስተማርንም እየተማርን እየተማማርን ነው። የእኛ ዓላማ የሃገር ዓላማ ነው። የኢትዮጵያን ልማት ወደፊት አራምዳለሁ የሚል በቀና መንፈስ የሚነሳ አካል ከመጣ በነፃም እናገለግላለን። ያለንን ሁሉ እንሰጣለን። በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ብዙ ጉልበት አፍስሰን የምንሰራበት ወጣቱን ልማቱን እንዲያግዝ መርዳት ነው። የምናደርጋቸው ነገሮች ዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ነው።"
ስለሃገር በቀል ዕይታ አጠቃላይ ዓላማ የተናገሩት ዶክተር ፀደቀ አባተ ናቸው::የቀድሞ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፀደቀ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የግብርና ምርምር ሳይንቲስት ናቸው።
የሃገር በቀል ዕይታ መስራችና መሪ ዶክተር ፀደቀ አባተ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ትብብር ሃገር በቀል ዕይታ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ገለፃ ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የቆየ የግብርና ታሪክ አላት::ማረሻ መጠቀም የጀመረችው ከ 500 ዓመተ ምህረት በፊት መሆኑንም የታሪክ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ጠቅሰዋል።
ዶክተር ፀደቀ አባተ እንደሚሉት ባለፉት 60 ዓመታት የነበሩ ስርዓቶች የኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል::በተለይም ባለፉት አስር ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን በመንግስት በኩል ከፍተኛ እና ልዩ ጥረት ተደርጓል::ይሁንና ዓላማው በጎ ሆኖ ሳለ አጀማመሩና አተገባበሩ ላይ ችግር ስለነበረበት ግቡን ሊመታ አልቻለም::ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሷቸው ደግሞ ሲጀመር ሁሉን አቀፍ ጥናት ላይ የተመሠረተ አለመሆኑና ዕውቀትና ሠፊ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሳተፉበትና የተወያዩበት ሳይሆን ከላይ ወደታች ዓይነት አሠራር ስለነበረበት ነው።
የሚፈለገው ለውጥ ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ሰብሮ ለመውጣት የሚይስችል መሆን ይኖርበታል የሚሉት ዶክተር ፀደቀ ለኢትዮጵያ ችግር መፍቻ ቁልፉ ያለው ኢትዬጵያውያን ዘንድ መሆኑ ታውቆ ለተውሶ ሳይሆን ለሃገር በቀል መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
"ሃገር በቀል ልማትህን ለሰው አሳልፈህ ሰጥተህ በውድ ዋጋ ልትገዛ አይገባህም::ልማትን በአቋራጭ መንገድ እነርሱ ሰርተው ሰጥተውን ከድህነትና ከምግብ እጦት ያወጡናል ብሎ መገመት ውጤቱን እስካሁን አይተነዋልና እንደእርሱ አይሆንም::እኛው ራሳችን ጠንክረን ሰርተን መስዕዋትነት ከፍለን ማምጣት ያለብን ጉዳይ ነው።"
የሩቅ ምሥራቅ ሃገሮች በተለይም ጃፓን ታይላንድና ቻይና አብዛኛው የሳይንስና የምርምር ዕድገታቸው ከሃገር በቀል ባህላዊ ዕውቀቶች ጋር ይያያዛል::ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያው ሃገር በቀል ዕይታ ምን ውጥን ይዞ እንደተነሳ ዶክተር ወርቅነህ ያብራራሉ። 
"በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የግብርና ልማት ፈጠን አድርገን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የምንፈልግ ከሆነ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ስራዎችን ማሰብ ይኖርብናል የሚል አጠቃላይ ግንዛቤ አለ:: በመንግሥትም ከአንዳንድ ድጋፍ ለመስጠት ከውጭ በሚመጡ ድርጅቶችም::ግን ይህንን ለውጥ ለማምጣት ምን ዓይነት አካሄድ ነው መከተል ያለብን እስካሁን የሞከርናቸው የተማርንባቸውና ልምድ ያገኘንባቸውን አሠራሮች እንዴት አድርገን ነው ወደሌላ መሄድ ያለብን የሚል ውስጣችን የሚመላለስብን ጉዳይ ነው::ከውጭ የሚመጣው ብቻ ይጠቅማል የሃገር ውስጡ ኃላቀር ነው ውጤታማም ምርታማም ያልሆነ ቴክኖሎጂ የሌለው መቀየር አለብን የሚል የተዛባ አሰራር አለ::በምርምር ተቋማት በወጣት ተመራማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎችም አካባቢ የምናየው መተማመኛ የሌለው መረጃም ሳይኖር ያለን ነገር ብዙ አይጠቅመንም  መቀየር አለብን ከውጭ የሚመጣውን አምጥተን ነው መስራት ያለብን የሚል  ሐሳብ አለ::ያ ደግሞ እኛ እስከምናውቀው ድረስ ብዙ ጊዜ ቆይተናል በመማሩም በማስተማሩም በልማት ስራውም ቆይተናል::ከግድ ከውጭ እየመጣ አይደለም ትልቅ ለውጥ ልናመጣ የምንችለው በግብርና ውስጥ::እና እስካሁን ስንሠራበት የነበረውን በደንብ አይተን ጠለቅ ያለ ግምገማ አድርገን ሃገር በቀል ስንል ከዚህ በፊት ምን ሰርተን ምን ተምረን ነው እንደገና ወደልማት ስራ መሄድ የምንችለው የሚል አካሄድ ነው መነሻው::ከዚህ በመነሳት እኔ አተኩሬ በምሰራበት በእንሰሳት ዕርባታውም ይሁን በሰብል ልማት በአፈርና ውኃ ጥበቃና በደን ልማት በእጃችን በሃገር ውስጥ የነበሩ ልምዶች አሰራርና ተሞክሮዎችን በደንብ ዐይተንና ገምግመናቸው ከእነሱ ተነስተን ነው አዲስ ነገር ማምጣት አለብን የሚለው ላይ የጋራ ስምምነነት ስላለን ነው እንግዲህ ይህንን ሐሳብ የምንጋራ ባለሙያዎች ሰብሰብ ብለን የመሠረትነው ማለት ነው::አደረጃጀቱን አስተካክለን ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በመንግስትም ፈቃድ አግኝቶ ልማት ላይ ሐሳብ ለመለዋወጥና ሐሳቦችን ለሌሎችም ለማካፈል ነው የተቋቋምነው ማለት ነው።“ ሕዝቡ በተለይም አዲሱ ትውልድ የራሱን ባህልና ሃገር በቀል ዕውቀቶች ማወቁ ብዙ ጥቅም አለው የሚሉት ዶክተር ፀደቀ የድርጅቱን ሃገራዊ ግብ በማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። 
"ትልቅ ነው ብለን የምንገምተው የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና እያሻሻልን ነው::ሁለተኛው ከእርሱ ጋር የተያያዘ የፖሊሲ ሰዎችም ቢሆኑ ምናልባት በቀጥታ ይሄ የእነርሱ ውጤት ነው ላይሉ ይችላሉ::ብዙ ቦታ እኛን ቋንቋ የሚናገሩ ብዙ ናቸው::በቆሎ ላይ ስንፅፍ ነበር ሃገር ውስጥ ያለነውም ከሃገር ውጭ ያለን ተሰብስበን አንድ የውጭ ሰው ሳናስገባ የኢትዮጵያ የበቆሎ ምርት እዚህ የደረሰው ብለን ለዓለም ለማሳወቅ ፈለግን 2015 ላይ እንደጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ታትሞ ወጣ::ፉድ ሴኩሪቲ በሚል ታዋቂ ጆርናል ላይ::እዛ ላይ ስናወጣ እንደትልቅ መነሻና ምክንያት ያደረግነው ኢትዮጵያ ሃገር በቀል ዕይታ ነው የነበራት ምርምራችን በለጋሾች ግፊት የሆነ አይደለም እኛው ራሳችን ነው ደግሞም ትክክል ነው::ከጃንሆይ ጊዜ ጀምረን የፈጠርነው ነገር ውሎ ሲያድር ጥሩ ትምህርት ስንወስድ ጥሩ ምርምር ስናካሂድ ስንወድቅም ስንነሳም ቆይተን አሁን ፍሬ ማፍራት የጀመርነው ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሃገራት  ስሩ ስለተባለ ሳይሆን አምነንበት ሰርተን እዚህ ደረስን:: ሃገር በቀል ብለን የጀመርነው ያኔ ነው።"
ዶክተር ወርቅነህ እንዳሉትም ይህ ሃገር በቀል ዕይታ ሃሳብ ተቀባይነት እያስገኘላቸው ለውጦችም እየመጡ ነው። 

Äthiopien | Zentral Gonde
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Äthiopien | Einsturz der Tekeze-Brücke
ምስል Waghemera zone communications
Addis Abeba I Äthiopischer Neujahrsmarkt
ምስል DW/S. Getu

ታሪኩ ኃይሉ 
አዜብ ታደሰ