1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲና በእስራኤላውያን ትብብር

ዓርብ፣ መጋቢት 23 2014

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና በእስራኤላውያን የጋራ ትብብር ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው "Fair Planet" ፕሮጀክት ዝናብ አጠር የሆኑትን የምስራቅ ሀገሪቱ አካባቢዎች ምርታማነት ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተገለፀ።

https://p.dw.com/p/49LB8
Äthiopien  Haremaya-Israel Fair Planet Project
ምስል Messay Mekonnen/DW

«እውቀቱን መውሰድ እና በተግባር ማዋል አስፈላጊ ነዉ»

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና በእስራኤላውያን የጋራ ትብብር ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው "Fair Planet" ፕሮጀክት ዝናብ አጠር የሆኑትን የምስራቅ ሀገሪቱ አካባቢዎች ምርታማነት ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተገለፀ። "Fair Planet" ለአካባቢው ተስማሚ ዘር ማውጣት የሚያስችል የአዝርዕት ምርምር እና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን ለባለሞያዎች እና ለአርሶአደሩ በማካፈል ላይ አተኩሮ ሲያከናውን የቆየ ፕሮጀክት ነው።

የፕሮጀክቱ ምርምር በሚካሄድበት እና ድሬደዋ በሚገኘው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ቶኒ ፋርም የመስክ ምልከታ ላይ ከተገኙ አርሶ አደሮች አንዱ የሆኑት አቶ አብዲ ኢብሮ ፕሮጀክቱ የሰጣቸው ድጋፍ የተሻለ ምርት ለማምረት እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

 በበጎ ፈቃደኛ እስራኤላውያን እየተተገበረ የሚገኘውን የfair planet ፕሮጀክት ውጤታማ ለማድረግ በትብብር እየሰራ የሚገኘው የሀረማያ ዩኒቨርስቲ መምህር ተመራማሪ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ከበደ ወልደፃዲቅ በበኩላቸው  ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው በበጎፈቃደኝነት በፕሮጀክቱ እየሰሩ ያሉት እስራኤላውያን ቴክኖሎጂን ብቻ ሳይሆን የስራ ባህልን እያስተማሩን ነው ብለዋል።

Äthiopien  Haremaya-Israel Fair Planet Project
ምስል Messay Mekonnen/DW

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስቴር ሚንስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በfair planet ፕሮጀክት መስክ ምልከታ ያዩትን ጥረት ማስፋት እንፈልጋለን ብለዋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ፣ የመስኖ ስራዎችን ማሳደግ የመንግስት ፍላጎት መሆኑን በማንሳት በጋራ ከሰራን አሁን ያለንበትን ችግር መሻገር እንችላለን ብለዋል። ፌየር ፕላኔት የጀመረው ጥረት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲያድግ የጠየቁት ሚንስትር አይሻ መስሪያ ቤታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በግብርና በኩል እስራኤል ብዙ እውቀት መኖሩን ያነሱት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በበኩላቸው በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ውጤት እንዲመጣ እየተሰራ መሆኑን እና ወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። አምባሳደሩ በፕሮጀክቱ እየሰሩ ያሉት እስራኤላውያን በጎፈቃደኞች መሆናቸውንና ይሄ በኢትዮጵያም መለመድ እንዳለበት ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ያመጣውን  እውቀት መውሰድ እና በተግባር ማዋል አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ዝናብ አጠር ለሆነው አካባቢ ተስማሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዘሮችን በምርምር አዘጋጅቶ ከማቅረብ ባለፈ አሰራርን ለማሻሻል የሚያግዝ የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው  ፌየር ፕላኔት ፕሮጀክት ከድሬደዋ በተጨማሪ  በሀረሪ እና ምስራቅ ሀረርጌ አካባቢዎች የሚገኘውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑ ታውቋል።

 

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ