1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሼንግቤ ፒህ

Murtala Kamara
ሐሙስ፣ ሰኔ 4 2012

ሴራሊዮናዊው ገበሬ እና ነጋዴ ሼንግቤ ፒህ እጎአ በ1839 ለባርነት ታግተው ተወሰዱ። በዚህ ወደ «አዲሱ ዓለም» እየተባለ በሚጠራው ጉዟቸው ላይም የተወሰዱበት መርከብ አሚስታድ ላይ አመፅ አካሂደዋል። ይህም አመፅ ኃላ ላይ የፀረ ባርነት ንቅናቄ ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/3deBr
African Roots | Sengbe Pieh 1 | Porträt

ሼንግቤ ፒህ የት ተወለዱ?
በትክክል የተወለዱበት እለት አይታወቅም። በርካታ የታሪክ ምሁራኖች ግን በጎአ 1814 ገደማ ሴራሊዮን ውስጥ እንደተወለዱ ይጠቁማሉ። የተወለዱት ደግሞ በእርሻ እና በአሳ ማጥመጃነት በሚታወቀው የቦንቴ ደሴት ደቡባዊ አውራጃ ውስጥ ነው። ፒህ እድሚያቸው ከፍ ሲልም የሩዝ ገበሬ ይሆናሉ። እሳቸውም በታገቱበት ወቅት አግብተው እንደነበር እና አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች እንደነበራቸው ይነገራል።
ሼንግቤ ፒህ የምን ጎሳ ነበሩ?
አብዛኛው ማህበረሰብ ፒህ የሜንዴ ጎሳ እንደሆኑ ቢያምንም አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ግን የለም የሼብሮ ጎሳ ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ። የሜንዴ ጎሳ ከሴራሊዮን ትልቁ የህብረተሰብ ቡድን ነው።   ሼብሮ ደሴት በመባልም የምትታወቀው የቦንቴ ደሴት ላይ ቀደም ሲል ከሴራሊዮን አናሳ የሆነው የሼብሮ ጎሳ ሰዎች ይኖሩባት ነበር። በጋብቻ ምክንያት አሁን ላይ አብዛኞቹ ሼብሮዎች ራሳቸውን ሜንዴ ነን ሲሉ ይጠራሉ።  ይህም ሴራሊዮን ውስጥ በሜንዴ እና በሼብሮ መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት እጅግ ከባድ አድርጎታል። 

ከአሚስትድ አመጽ በስተጀርባ ያለው ታሪክ ምንድን ነው?
እ.ጎ.አ ጥር 1839 ሼንግቤ ፒህ እየሰሩ ከነበረበት የሩዝ እርሻቸው ውስጥ በባሪያ ነጋዴዎች ታግተው  ሱሊማ ደቡባዊ ሴራሊዮን ውስጥ ለሚገኙ ለስፓኝ የባሪያ ገዢዎች ይሸጣሉ። ፒህ ከብዙ ሌሎች የሴራሊዮን  ባሪያዎች ጋር  በግዳጅ ወደ ሀቫና ኩባ በመርከው ተጭነው ከተወሰዱ በኋላም በጨረታ ይሸጣሉ። 

የባሪያ ጌቶች ፒህ ና ሌሎች ሰዎችን ላ አሚስታድ በተባለችው መርከብ ላይ ጭነው ወደ የአገዳ እርሻ በሚወስዱበት ወቅት ሼንግቤ ፒህ ሰንሰለታቸውን ሰብረው ራሳቸውን እና ሌሎቹን ታጋቾች ከፈቱ በኋላ ለአገዳ መቁረጫ እንዲሆናቸው መርከብ ላይ ተጭኖ የነበረውን ገጀራ በመታጠቅ አመፅ ይጀምራሉ። የአመፁ መሪ ራሳቸው ፒህ ነበሩ። የመርከቡን ካፒቴን እና ምግብ አብሳዩን ከገደሉ በኋላ አዲስ የመደቡት ሹፌር ወደ ሴራሊዮን እንዲመልሳቸው ያዛሉ። በፒህ መሪነት ብዙም የጉዞ ልምድ የሌላቸው ነፃ የወጡት አፍሪቃውያን እና የተወሰኑ ህፃናት እየተጓዙ ሳሉ ሌሊቱን አዲሱ ካፒቴን ያታልሏቸው እና ወደ ኩባ አቅጣጫቸውን ቀይረው ጉዞ ይጀምራሉ። በወቅቱ የነበረውም ማዕበል ጀልባዋን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የውኃ ክልል ውስጥ ይገፋታል። ፒህ እና ባልደረቦቻቸውም በቁጥጥር ስር ውለው በነፍስ ማጥፋት እና በባህር ላይ ውንብድና ወንጀል ተከሰው እስር ቤት ይገባሉ።  
ነገር ግን ኃላ ላይ « የአሚስታድ ኮሚቴ» በመባል የሚጠራው የፀረ ባርነት ቡድን ጉዳያቸውን በተሳካ ሁኔታ ተከራክሮ ያስፈታቸዋል። ይሁንና በርካታ ሰዎች በጉዞ እና በአመፁ ወቅት ህይወታቸውን አጥተው ስለነበር ወደቤራቸው ለመመለስ አልበቁም። ፒህ እና ሌሎች ግን ከተወሰኑ አሜሪካዊ ሚሲዮናውያን ጋር በመሆን ጥር 1842 ወደ ሴራሊዮን ተመልሰዋል።   

ሼንግቤ ፒህ

ይህ ታሪክ ከዩናይትድ ስቴትስ የባርነት ስርዓት ማክተም ጋር ምን ያገናኘዋል?
የሼንግቤ ፒህ ታሪክ የአሜሪካው ፀረ ባርነት ንቅናቄ ይበልጥ እንዲነቃቃ እና በአሜሪካ የባርነትን ስርዓት እንዲያከትም ዘመቻውን አበረታቷል። ስለ አሜሪካ የባርነት ስርዓት የሚተርክ ማንኛውም የታሪክ መጽሐፍ የሼንግቤ ፒህን ጀግንነት ሳይናገር አያልፍም። አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የሼንግቤ ፒህን ታሪክ ያስተምራሉ። አንዳንድ ግዛቶች ደግሞ የሼንግቤ ፒህ ሐውልቶች አሏቸው። ሆሊውድ በፒህ እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፊልም ሰርቷል።  የሼንግቤ ፒህ ወደ ሴራሊዮን መመለስም ለክርስቲያን ሚስዮናውያን በር ከፍቷል። 
ሼንግቤ ፒህ የት ተቀበሩ?
ሼንግቤ ፒህ የሞቱት እጎአ 1879 ነበር። ከተመለሱም በኋላ ወደ ቤተሰባቸው ስለመቀላቀላቸው ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ሼንግቤ ፒህ ቦንቴ ውስጥ በምትገኘው ሽሪነ ተቀብረዋል ተብሎ ይታመናል። ሼንግቤ ፒህ የሚስጥራዊው የፖሮ ማህበረሰብ ጠንካራ አባል ነበሩ። ሀውልታቸውን ለማየት ይፈቀድ የነበረው ለፖሮ አባላት ብቻ ነበር።  የፒህ መቃብር ቦታ አንዳንድ ምስጢራዊ ኃይል እንዳለው በሰፊው ይታመናል። የቱሪዝም ሚኒስቴር መቃብራቸውን ለሁሉም ህዝብ ክፍት እንዲሆን ወደ ሌላ ስፍራ ለመውሰድ እቅድ አለው። 

ትልቁ ውርሳቸው ምንድን ነው? 

ሼንግቤ ፒህ ሁሉም ሰዎች ያለ ቀለም እና ጎሳ ልዩነት እኩል ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። ለራሳቸው እና ለሌሎች ነፃነት ሲሉም ታግለዋል። 

ሴራሊዮናውያን እንዴት ያስታውሷቸዋል?
ምስላቸው በሴራሊዮን ገንዘብ ላይ ይገኛል። በዋና ከተማዋ ፍሪታውን የሚገኝ አንድ ድልድይ በቅርቡ በስማቸው ተሰይሟል። የእሳቸውን ሥዕሎች በፍሪታውን ጎዳናዎች ላይ ማየት ቀላል ነው።

ሼንግቤ ፒህ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።