1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ሶስት ወር ለገንዘብ ቅያሬው ይበቃል?

ረቡዕ፣ መስከረም 13 2013

የኢትዮጵያ መንግሥት የመገበያያ ገንዘብ ለውጡን በሶስት ወራት ለማጠናቀቅ አቅዷል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን "በዚህ ግርግር፤ በዚህ ፍጥነት የተካሔደ እንደሆነ ብዙ የሕብረተሰብ ክፍል በይበልጥ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን፣ ገበሬውን እና ድንበር አካባቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በጣም የሚጎዳው ይሆናል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

https://p.dw.com/p/3iuM1
Äthiopien Alte Banknoten werden verändert, um die Korruption zu bekämpfen
ምስል Privat

«ብር መቀየሩ ለገበሬዎችና አርብቶ አደሮች ምን ያክል ፈታኝ ነው?»

በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ሐርጌሌ ከተማ የክሊኒክ እና የመድሐኒት መደብር ባለቤት የሆኑት አቶ አሕመዲን ሻፌ ኢትዮጵያ ለ23 አመታት ገደማ የተጠቀመችባቸውን የብር ኖቶች መቀየር መጀመሯን ቢሰሙም እስካሁን አላዩትም። "መንግሥት ብር ቀይሯል እያሉ ነው። እስካሁን አይቼ አላውቅም" የሚሉት አቶ አሕመዲን የኮንትሮባንድ ንግድ በሚበረታባት ከተማቸው ሐርጌሌ ወደሚገኝ የባንክ ቅርንጫፍ ቢጠይቁም እስከ ትናንት መስከረም 13 ድረስ አልተገኘም።

አቶ አሕመዲን አዲሱ ብር እጃቸው ከመግባቱ በፊት ቀድሞ የደረሳቸው በቅያሬው ምክንያት "ሕገ-ወጥ" የተባለ ገንዘብ የጸጥታ አስከባሪዎች ወረሱ የሚለው መረጃ ነው። "በአጠቃላይ መንግሥቱ የሚፈልገው ነገር የሕዝብ ብር መውሰድ ብቻ ነው። ሕግ የሚባል የለም። መንግሥት እና ጦሩ ስንት የሶማሌ ሰው ብር ወሰደ። ብር ከተቀየረ በኋላ አንድ ሚሊዮን፣ ሁለት ሚሊዮን ሶስት ሚሊዮን…ስንት ብር ተወሰደ" ሲሉ ይናገራሉ አቶ አሕመዲን።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና በግላቸው በግብርና ሥራ የተሰማሩት አቶ አብዲሪሳቅ አሕመድ እንደሚሉት ድንገተኛው የመገበያያ ገንዘብ ቅያሬ አርብቶ አደሮች በሚበዙበት እና ኢ- መደበኛ የንግድ የልውውጥ በሚበረታበት የሶማሌ ክልል ግርታ ፈጥሯል።

"የባንክ አገልግሎት፣ የቴሌኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሌላቸው፤ መረጃ ያልደረሳቸው ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች አሉ" የሚሉት አቶ አብዲሪሳቅ "ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት የመገበያያ ገንዘብ ቅያሬው በምስጢር የተያዘ ነበር። በድንገት ነው አንዴ የመጣው። ያ ሲመጣ ግርግር ነገር ይፈጥርና የባንክ አገልግሎትም በበቂ ስለሌለ በመሀል የጸጥታ አስከባሪዎች እንዲቀሙ ክፍተት ፈጥሯል። ከዚያ በኋላ የሶማሌ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት እና ከፌድራል መንግሥት ጋር ተወያይተው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በታች እንዳይያዝ መፍትሔ ሰጡ። ሆኖም ግን ስለልቦናዊ ጫናው ስላለ ሰው እየፈራ ስለነበር ተራው ገበሬ ወይም አርብቶ አደር የራሱን ገንዘብ ለመጠቀም ተፅዕኖ አምጥቶበታል˝ ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የመገበያያ ገንዘብ ሊቀይር እንደሚችል ጭምጭምታዎች ከተሰሙ ወራት ቢቆጠሩም መረጃው አቶ አሕመዲን የሚኖሩበት የአፍዴር ዞንን የመሳሰሉ አካባቢዎች እኩል የሚደርስ አልነበረም። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ "በምስጢር የሚያዝ ጉዳይ አይደለም" ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥትን አካሔድ ይተቻሉ።

"ግልጽ ዓላማ ተቀምጦለት፤ በዝርዝር መርሐ-ግብር ወጥቶለት፤ የትኛው ኖት መጀመሪያ እንደሚተካ፣ ባንኮቹን ጨምሮ የሚሳተፉ አካላት ማንነት፣ የጊዜ ገደቡ፣ በወቅቱ ያልቀየሩ ሰዎች ምን ማድረግ እንደሚችሉ" ታውቆ መከወን እንደነበረበት የሚናገሩት አቶ አብዱልመናን ባንኮች ጭምር የማስፈጸሚያ መመሪያ የደረሳቸው ዘግይቶ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የብር ቅያሬ ሒደቱ ድንገቴነት የፈጠራቸው "ክፍተቶች" መኖራቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አምኗል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ባለፈው ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ማብራሪያ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በታች በኢትዮጵያውያን እጅ በጥሬ ገንዘብ ቢገኝ "ሕገ-ወጥ ነው ተብሎ መያዝ የለበትም። በገመገምንው አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመቶ ሺሕ ብር በላይ የያዘ ሰው ሕገ-ወጥ ነው የሚል አተረጓጎም አለ" ሲሉ ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ በተደረገበት መስከረም 4 ቀን "እኛ ገንዘቡን አንፈልገውም። ወርሰው የሕግ አስከባሪ ተቋማት ይጠናከሩበታል" ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ አዲስ ይፋ ያደረገቻቸው 262 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 2.9 ቢሊዮን የብር ኖቶች በሶስት ወራት ለመቀየር የጀመረችውን ሒደት ከሚፈታተኑ መካከል የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት እና የተጠቃሚዎች ቁጥር ውስንነት ይገኝበታል። "ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር ሔደህ ባንክ ላታገኝ ትችላለህ። ጅግጅጋ ያለው [የባንኮች ቁጥር] ከሌሎች ከተሞች ያነሰ ነው" የሚሉት አቶ አብዲሪሳቅ አሕመድ የአገልግሎት አሰጣጡም ችግሮች እንዳሉበት ያስረዳሉ። "ጅግጅጋ ራሱ ሶስት መቶ ብር ወይም አራት መቶ ብር ለመቀየር አንድ ሚሊዮን ብር እንዳስገባ ሰው የባንክ አካውንት ክፈት ትባላለህ። እዚህ ባንክ የሚሰራው ሰው ቋንቋ [ሶማሊኛ] ራሱ አይችልም። በአማርኛ ወይም ሌላ ቋንቋ ነው የሚያወሩት። አርብቶ አደሩን የራሱን ቋንቋ ተጠቅሞ ማስረዳት ያስፈልጋል" ሲሉ ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ የግል ባንኮች 40 በመቶው ከመንግሥት 25 በመቶ ገደማ ቅርንጫፎቻቸው በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ያስታወሱት አቶ አብዱልመናን "ወደ ድንበር አካባቢ እና በብዛት ገጠራማ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎት አይገኝም። አብዛኛው ሰው የባንክ አካውንትም የለውም። የኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውር ተጠቃሚው ከአንድ በመቶ በታች ነው" ሲሉ አስረድተዋል። ከባንክ ርቀው የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዴት ገንዘባቸውን መቀየር እንደሚችሉ መፍትሔ አልተበጀም የሚሉት ባለሙያው "ድንበር አካባቢ ሰፊ የሆነ የገንዘብ ልውውጥ ይካሔዳል። ያንን የገንዘብ ልውውጥ የሚያካሒደውን ሕብረተሰብ ለለውጡ የባንክ አገልግሎት ተጠቀም ስትለው እንዴት ነው ማድረግ የሚችለው? አንድ ሰው ባንክ ቅርንጫፍ ለማግኘት ምን ያህል ኪሎ ሜትር ይጓዛል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ምስል picture-alliance/M.Kamaci

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ በዛሬው ዕለት የብር ለውጡን ለማጠናቀቅ "ሶስት ወርም ላንጠብቅ እንችላለን" ሲሉ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ይኸ ግን ለአቶ አብዲሪሳቅ የሚዋጥ አይነት አይደለም። "ሶስት ወር የሚበቃ አይመስለኝም። አንዳንድ ቦታ መረጃውን ለማድረስ ራሱ ወር ሊፈጅ ይችላል። ለ23 አመታት የቆየ ጥሬ ገንዘብን ለመቀየር በጣም ይከብዳል" የሚል ዕምነት አላቸው።

አሮጌውን መገበያያ ገንዘብ በአዲስ ለመቀየር "ምክንያታዊ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል" የሚሉት አብዱልመናን የጊዜ ገደቡ ቢያልቅ እንኳ በተባለው ወቅት ላልተሳካላቸው ሌላ ሥርዓት ሊበጅ እንደሚገባ ገልጸዋል። "ያንን የመገበያያ ገንዘብ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ባንክ ሔዶ መቀየር ባይችል ያ የመገበያያ ገንዘብ በኤኮኖሚው ውስጥ አገልግሎት ባይኖረውም ወይ ባንኮቹ እንዲቀበሉ አለበለዚያ ብሔራዊ ባንክ እንዲቀበል መንግሥት ማቀድ ነበረበት" ያሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "አለበለዚያ ግን በዚህ ግርግር፤ በዚህ ፍጥነት የተካሔደ እንደሆነ ብዙ የሕብረተሰብ ክፍል በይበልጥ መደበኛ ባልሆነው ኤኮኖሚ ላይ ያለ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን፤ ገበሬውን፤ ድንበር አካባቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በጣም የሚጎዳው ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እሸቴ በቀለ