1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥቅምት 10 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥቅምት 10 2012

በጀርመን ቡንደስሊጋ በተቀራረበ የነጥብ ልዩነት የእግር ኳስ ፉክክሩ ተጧፉፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ሊቨርፑል ለመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል። ኢትዮጵያውያት አትሌቶች በአምስተርዳም ማራቶን ድል ተቀዳጅተዋል።

https://p.dw.com/p/3RfHF
Deutschland Borussia Dortmund gegen Borussia Mönchengladbach
ምስል Getty Images/Bongarts/D. Mouhtaropoulos

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ በተቀራረበ የነጥብ ልዩነት የእግር ኳስ ፉክክሩ ተጧፉፏል። ከ18ቱ የቡንደስ ሊጋ ቡድኖች መካከል ከሁለቱ በስተቀር የሌሎቹ ነጥብ አንዱ ከአንዱ ጋር የመመሳሰል ነገር አለው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ሊቨርፑል ለመጀመሪያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል። ማንቸስተር ሲቲ በ6 ነጥብ ልዩነት ሊቨርፑልን ተጠግቷል። ኢትዮጵያውያት አትሌቶች በአምስተርዳም ማራቶን ድል ተቀዳጅተዋል።

ትናንት ወደ ኦልትራፎርድ ያቀናው ሊቨርፑል በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ ተስኖታል። ኾኖም ግን መደበኛ የጨዋታው ክፍለ-ጊዜ ከመጠናቀቁ አምስት ደቂቃ ቀደም ብሎ አዳም ላላና ባስቆጠረው ግብ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በዚያም ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በዘጠነኛ ግጥሚያቸው ዘጠነኛ ድል ሳይቀዳጁ ቀርተዋል።

UEFA Champions League 2019/20 | Schachtar Donezk vs. Manchester City
ምስል Reuters/G. Garanich

የመጀመሪያዋን ግብ ለማንቸስተር ዩናይትድ ያስቆጠረው ማርኩስ ራሽፎርድ ሲኾን፤ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ኦሪጂ «ላይ ግልጽ ጥፋት ተሠርቶበታል፤ ሌላ ምንም አይደለም» ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጠዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ኦሪጂ ከቪክቶር ሊንዴሎይፍ ጋር ሲታገል ኳሷን ተነጥቆ በወደቀበት ቅጽበት ነው ግቧ የተቆጠረችው። ዳኛው የቪዲዮ ምስል ከተመለከቱ በኋላ ኦሪጂ አልተጠለፈም በሚል ግቧን አጽድቀዋል። ሳዲዮ ማኔ ያስቆጠራትን ግብ በተመሳሳይ ዳኛው የቪዲዮ ምስል ከተመለከቱ በኋላ ኳሷን በእጁ ነክቷል በሚል ሽረዋል። ዬርገን ክሎፕ በቪዲዮ ድጋፍ የዳኝነት ብያኔ የሚሰጥበትን  (VAR)  ስልት ነቅፈዋል።  

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ማንቸስተር ዩናይትድን ያሸነፉት ለሁለት ጊዜያት ብቻ ነው፤ እንዲያም ኾኖ ማንቸስተርን በሜዳው ኦልትራፎርድ አሸንፈው ዐያውቁም።

UEFA Super Cup - Liverpool vs Chelsea
ምስል Reuters/M. Sezer

በፕሬሚየር ሊጉ በሊቨርፑል በ6 ነጥብ ተበልጦ በ19 ነጥቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቡድናቸው በሻምፒዮንስ ሊግ ድል የማድረጉ ነገር አጠያያቂ ነው አሉ። ምንም እንኳን ማንቸስተር ሲቲ በአቡዳቢ ባለቤቶቹ ከፍተኛ የገንዘብ ፈሰስ ቢደረግበትም ስፔናዊው አሰልጣኝ ግን ማንቸስተር ሲቲ እንደ ፕሬሚየር ሊግ አያያዙ ከኾነ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ዋንጫ የማሸነፍ ዕድል የለውም ሲሉ የገዛ ቡድናቸውን ተችተዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ለሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ማታ ከጣልያኑ አታላንታ ቤርጋሞ ጋር ይፋለማል። አታላንታ ቅዳሜ ዕለት ከሌላኛው የጣሊያን ቡድን ላትሲዮ ጋር በሴሪ ኣው 3 እኩል አቻ ወጥቷል።  የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከቱርኩ ጋላታሳራይ፤ ዶኒዬትስክ ከዲናሞ ኪዬቭ ጋር፤ብሩዠ ከፓሪ ሴንጄርሜን፤ ጁቬንቱስ ከሎኮሞቲቭ ሞስኮው፤ ቶትንሀም ከሮተር ሽቴርን፤ እንዲሁም ሌኛው የስፔን ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ ከጀርመኑ ሌቨርኩሰኑ ጋር የሚፋለሙት በነገው ዕለት ነው። የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ እና የጀርመኑ ባየር ሙይንሽንም  ነጋ ማታ ይጋጠማሉ።

Manchester City Trainer Pep Guardiola
ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto

ቅዳሜ ዕለት ከአውስቡርግ ጋር 2 እኩል የተለያየው ባየር ሙይንሽን በቡንደስሊጋው ከመሪው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በአንድ ነጥብ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።ለባየር ሙይንሽን ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ በ14ኛው ደቂቃ እንዲሁም ሠርጌ ግናብሬ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ለአውስቡርግ ማርኮ ሪሽተር ጨዋታው በተጀመረ በ1 ደቂቃ እና 90ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው 1 ደቂቃ ፊንቦጋሰን ግብ አስቆጥረዋል።

ከቮልፍስቡርግ ጋር ተመሳሳይ 16 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ8 የግብ ክፍያ በመሪነት ተቀምጧል። ትናንት በቦሩስያ ዶርትሙንድ የአንድ ለባዶ ሽንፈት በደረጃ ሰንጠረዡ የነጥብ ልዩነቱን እጅግ አጥብቧል። ቅዳሜ ዕለት ከላይፕሲሽ ጋር 1 እኩል የወጣው ቮልፍስቡር በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 6 የግብ ክፍያ አለው። ላይፕሲሽ እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባየር ሙይንሽን 15 ነጥብ አለው። በግብ ክፍያ ልዩነት ግን ከ3ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ይዘዋል።

Fußball Bundesliag - FC Bayern München gegen Mainz 05
ምስል AP

ፍራይቡርግ፤ ሻልከ፤ ፍራንክፉርት እና ሌቨርኩሰን በ14 ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ ብቻ ከ6 እስከ 9ኛ ደረጃን ተቆናጠዋል። 10ኛውና 11ኛው ሔርታ ቤርሊን እና ሆፈንሃይምም ነጥባቸው 11 ነው። 12ኛው ቬርደር ብሬመን 9 ነጥብ፤ ፎርቱና ዱስልዶርፍ 13ኛ፤ ዩኒየን ቤርሊን 14ኛ እና ኮሎኝ 15ኛ  ላይ ሲገኙ ሁሉም 7 ነጥብ አላቸው። 16ኛው አውስቡርግ እና 17ኛው ማይንትስም ተመሳሳይ 6 ነጥብ አላቸው።

ኮሎኝ በሜዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ፓዴርቦርንን 3 ለ0 አሸንፎ ከወራጅ ቃጣና ውስጥ ለመውጣት ችሏል። በ7 ነጥብ 15 ደረጃ ላይ ይገኛል። ምንም ማሸነፍ ያልቻለው ፓዴርቦርን አንድ ጊዜ አቻ በመውጣቱ 1 ነጥብ እና 13 የግብ እዳ ተሸክሞ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል። ማይንትስ እና አውስቡርግ በ6 ነጥብ፤ ኾኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ተለያይተው ፓዴርቦርንን ተከትለው ወራጅ ቃጣናው ላይ ተዘርግተዋል።  ፓዴርቦርን 18ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ 1 ነጥብ አለው። 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቬርደር ብሬመን  ነጥቡ 9 ነው።  

ቦሩስያ ዶርትሙንድ መሪው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 1 ለ0 ድል አድርጓል። ለዶርትሙንድ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ያስቆጠረው ማርኮ ሮይስ ነው። ሞይንሽንግላድባኅ በሜዳው ነው የተሸነፈው። 12ኛው ደቂቃ ላይ ማርኮ ሮይስ በ3 ተከላካዮች መሀል ወደቀን ተጠማዞ ለዩሊያን ብራንድት የላካት ኳስ በግብ ጠባቂው ጥረት ነው ግብ ከመኾን የተረፈችው። አስደንጋጭ ሙከራ ነበር።

Fußball Saison 1993 - 1994 | Inter Mailand vs. Borussia Dortmund
ምስል picture-alliance/dpa/F.P. Tschauner

26ኛው ደቂቃ ላይ ሞይንሽንግላድባኅ በስተግራ በኩል ያገኘውን ቅጣት ምት 22 ቁጥሩ ላስሎ ቤኔች ወደግብ ልኳት ይንችከ በችንቅላት ከዚያም ላይነር ወደግብ በቀጥታ የላካትን ግብ ጠባቂው ቡርኪ አድኗታል። ወዲያው ኤምቦሎ ለብቻው ወደ ግብ ጠባቂው ቡርኪ ተጠግቶ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ቡርኪ ኳሷን ነው ያወጣት፤ እሱ ግን መሬት ላይ ወድቆ ነበር። ፍጹም ቅጣት ምት አልተሰጠም፤ ሊሰጥም አይገባም ነበር። ሁምል ከማዕዘን የተላከችውን ኳስ ለጥቂት ነበር ሊያገባት የነበረው። የሞይንሽን ግላድባኁ ግብ ጠባቂ ዞመር ተወርውሮ አትርፏታል። በሒደት እያደገ የመጣ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ ተብሏል።

ማርኮ ሮይስ፤ ዩሊያን ብራንድት እና ቶርጋን ሐዛርድ ተቀባብለው የተቆጠረችው ግብ ቆየት ብሎ በደንብ ሲታይ ማርኮ ሮይስ ከጨዋታ ውጪ በመኾኑ ተሽሯል። 50ኛ ደቂቃው ላይ ዶርትሙንድ አስጨንቆ ዩሊያን ብራንድት የመታት ኳስ ከአግዳሚው በላይ ወጥታለች። ቶርጋን ሐዛርድ ለማርኮ ሮይስ 58ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ ሁኔታ ያሳለፋትን ኳስ መሬት ለመሬት መትቶ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

Fußall 1. Bundesliga Borussia Dortmund vs. Bayer Leverkusen
ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto/J. Fromme

የቱርክ ዜግነት እና ትውልደ ቱርካዊ የጀርመን ተጨዋቾች ሶሪያ ውስጥ የሚገኘው የቱርክ ጦርን በመደገፍ የሚያሳዩት ወታደራዊ ሰላምታ ጀርመን ውስጥ መነጋገሪያ ኾኗል። በቡንደስሊጋው ለፎርቱና ዱይስልዶርፍ ተሰልፎ የሚጫወተው ቱርካዊው ካኣን አይሃን ቱርክ ከአልባንያ ጋር ስትጫወት ከቱርክ ተጨዋቾች ጋር በጋራ የቱርክ ወታደሮች ሰላምታን በማሳየቱ ተተችቷል። እንደ ካኣን አይሃን ሁሉ ሌላኛው ቱርካዊ የዱስልዶርፍ ተጨዋች ኬናን ካርማንም ከትችት አልተረፈም። የዱስልዶርፍ አሰልጣኝ፦ «ሁለቱም ተጨዋቾች ለቱርክ ወሳኝ ተጨዋቾች መኾናቸውን ዐሳይተዋል። የተቀረው ሌላ ነገር አይመለከተኝም» ብለዋል። የቱርክ ዜግነት ያላቸው ጀርመን ውስጥ ለቡድኖች እና ለጀርመን ቡድን የሚጫወቱ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ጊዜያት ለቱርክ ያላቸውን አክብሮት ዐሳይተዋል። በተደጋጋሚ ታዲያ ተጨዋቾቹ ከትችት አልዳኑም።

Joachim Löw und Mezut Özil
ምስል Getty Images/M. Hitji

ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን ራሱን ካገለለ ከአንድ ዓመት ግድም በኋላ ሜሱት ዖይትሲል «ጀርመን ውስጥ ግዙፍ ችግር አለ» ሲል ሰሞኑን ተናግሯል። የቱርክ ዝርያ ያለው ጀርመናዊ የእግር ኳስ ተጨዋች ከቱርኩ ፕሬዚደንት ሬቺፕ ጣይብ ኤርዶኃን ጋር ፎቶግራፍ መነሳቱ በጀርመን ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር። አንዳንዶች ለጀርመናዊነቱ ታማን አልኾነም ሲሉ ነቅፈውት ነበር። ከሩስያው የዓለም ዋንጫ የጀርመን ቡድን ደካማ ውጤት በኋላም ለብሔራዊ ቡድኑ ሽንፈት ሜሱት ያስነሳው ውዝግብ ሰበብ ነው መባሉን ተጨዋቹን አበሳጭቶት ነበር። 

በተለይ የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚደንት ራይንሀርድ ግሪንድል ሜሱትን ተችተው የሰጡት አስተያየት ብሎም በአንዳንድ ጀርመናውያን ፖለቲከኞች እንዲሁም ኳስ አፍቃሪዎች የደረሰበትን መገለልንም በወቅቱ መቋቋም ባለመቻሉ ከቡድኑ ራሱን አግሎ ቆይቷል። ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን ባገለለበት ወቅት፦ «ሳሸንፍ ጀርመናዊ፤ ስሸነፍ ስደተኛ ነኝ» የሚለው አባባሉ ከብዙዎች ኅሊና የሚጠፋ አይደለም። እሱ ግን ድምፁን አጥፍቶ ለረዥም ጊዜ ቆይቶ ነበር። ለምን ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን ለመውጣት እንደወሰነ ምክንያቱን ከዓመት በኋላም ቢኾን ባሳለፍነው ሳምንት ተናግሯል። «ያኔ ከፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች ሳይቀር ዘረኛ አስተያየቶች ሲሰጡኝ ነበር» ያለው የ31 ዓመት እግር ኳስ ተጨዋች፤ ብሔራዊ ቡድኑ አለሁልህ ብሎ ለተቺዎቹ መልስ አለመስጠቱ እንዳበሳጨው ገልጧል። ይልቁንስ፦ «ከፕሬዚደንቱ ጋር ስለመገናኘቴ ይቅርታ እንድጠይቅ አለበለዚያ በቡድኑ ውስጥ ቦታ እንደማይኖረኝ ይፈልጉ እንደነበር ተሰምቶኛል፤ ያንን ደግሞ አላደርገውም» ነበር ብሏል።

Bildergalerie Regina Schmeken "Unter Spielern- Die Nationalmannschaft"
ምስል Regina Schmeken

ትናንት የአውስትራሊያዎቹ ሜልቦርን ሲቲ እና አደላይዴ ዩናይትድ ቡድኖች ባደረጉት ግጥሚያ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወጣት የእግር ኳስ ተጨዋች ያሬድ አብተው በ46ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል። ምንም እንኳን በተከላካይ መስመር የሚጫወተው ያሬድ በመጀመሪያ ግጥሚያው ጉዳት ቢደርስበት እና ቡድኑ አደላይዴ ዩናይትድ በልቦርን ሲቲ 2 ለ1 ቢሸነፍም ማለት ነው። ያሬድ ቁርጭምጭሚቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ የፊታችን ረቡዕ ቡድኑ አደላይዴ ዩናይትድ ከሜልቦርን ሲቲ ጋር በሚያደርገው የፍጻሜ ግጥሚያ አይሰለፍም ሲል ዘ አውስትራሊያን የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። በነገራችን ላይ የያሬድ ቡድን ከሜልቦርን ሲቲ ጋር ከነገ በስተያ በድጋሚ ሲጋጠም በአራት ቀናት ልዩነት ለሁለተኛ መኾኑ ነው።

አትሌቲክስ

Symbolbild Selbstläufer
ምስል Colourbox

አምስተርዳም ውስጥ በተደረገ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ትናንት ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል። በአምስተርዳሙ ማራቶን ደጊቱ አዝመራው 2 ሰአት ከ19 ደቂቃ ከ26b ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። ከ26 ሰከንድ በኋላ ትእግስት ግርማ ተከትላ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። አዝመራ ገብሩ ከደጊቱ በ1 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ ተበልጣ ሦስተኛ ወጥታለች። በትናንቱ የአምስተርዳም ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኬንያዊው ኤሊሻ ሮቲች 2ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ደቅሲሳ በ7 ሰከንድ ብቻ ለጥቂት ተበልጦ ሁለተኛ ወጥቷል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ «ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ሽልማቱን» ለንደን ውስጥ መቀበሉን በኢሜል የደረሰን መልእክት ያሳያል። ሽልማቱ በይፋ የተሰጠውም ጥቅምት 7 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ነው። «ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ » ተሸላሚ የኾነው «በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ በዓለም ቀዳሚ ተብሎ» እንደኾነው የደረሰን መልእክት ይጠቅሳል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ