1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 11 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 11 2011

አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ትናንት ባከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ሼር ኩባንያ ተቀይሮ ገሚሱ ድርሻ ለቡድኑ ደጋፊዎች የቀረው ደግሞ ለባለ ሐብቶች ሊሸጥ መታቀዱ ተገልጧል። የሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ሊገዙት ነው የሚል ዘገባ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል።

https://p.dw.com/p/3DbeP
Champions League Manchester United v Paris St Germain Paul Pogba
ምስል Reuters/P. Noble

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ትናንት ባከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ሼር ኩባንያ ተቀይሮ ገሚሱ ድርሻ ለቡድኑ ደጋፊዎች የቀረው ደግሞ ለባለ ሐብቶች ሊሸጥ መታቀዱ ተገልጧል። 244 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የኩባንያው ድርሻ ወይንም አክሲዮን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ግብይት ክፍት ይኾናል ተብሏል። በጉባኤው ላይ ተገኝቶ ከነበረ የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ ይኖረናል። የሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድን ሊገዙት ነው የሚል ዘገባ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል። ንጉሣዊው ቤተሰብ ዜናውን አስተባብሏል፤ በቡድኑ ላይ ግን ዐይኑን መጣሉ ታውቋል።

አንድ ምእተ-ዓመት ለመድፈን ሩብ ምእተ ዓመት የቀረው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ቡድን እሁድ የካቲት 10 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ  ሚሊኒየም አዳራሽ ማከናወኑ ተዘግቧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጠቅላላ ጉባኤው ለአክሲዮን ሽያጭ ሊቀርብ መኾኑን የማሻሻጥ ሥራ ጥናቱን ባቀረበው የፌይርፋክስ ኩባንያ (Fairfax Africa Fund) ተገልጧል። ጉባኤውን የታደመው የሰፓርት ተንታኝ እና ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ በጉባኤው የስፖርት ማኅበሩ ወደ አክሲዮን እንደሚቀየር ሲገለጥ «ስለአክሲዮን ድርሻ እና ስለሚቋቋመው የአክሲዮን ማኅበሩ ወይንም ድርጅቱ ምንም የተነሳ ሐሳብ የለም» ብሏል። ይልቁንም «አብዛኛው ደጋፊ በጭብጨባ ነበር ውሳኔውን እንደተቀበለው የተገለጠው። ስለዚህ የተለያዩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ሳይነሱበት ነው እንግዲህ ለውሳኔም ያለፈው፤ ውሳኔውም ቶሎ የጸደቀው። ስለአክሲዮን ማኅበሩ እንዴት ይኹን፤ የሚሉትን ጉዳዮች እንዲሁም አንዳንድ ደጋፊዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አልተመለከትንም» ሲል አክሏል። ይልቁንም ውሳኔው በደጋፊዎች ጭብጨባ መታጀቡን ገልጧል።

ለሕዝብ ክፍት የኾኑ ኩባንያዎች ድርሻዎች መገበያያ ሥፍራ ማለትም (stock Market)በሌለበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ድርሻው ወይንም አክሲዮኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ግብይት ክፍት ይደረጋል (IPO)መባሉ ማነጋገር ይዟል።

ከሽያጭ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተሳታፊው ማንቸስተር ዩናይትድን የሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ሊገዙት ነው መባሉ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል። በብሪታንያ የሚታተመው እለታዊ ጋዜጣ ዘ ሰን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ይዞት የወጣው ዜና አልጋ ወራሹ ማንቸስተር ዩናይትድን በ4 ቢሊዮን ዶላር ሊገዙት እንደኾነ የሚገልጥ ነው። የሣዑዲ አረቢያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አልጋ ወራሹ ኒውዮርክ ውስጥ ዩናይትድ ተብሎ የተመዘገበው የቡድኑ ድርሻን ሊገዙት መቃረባቸውን አስነብቧል። ኾኖም የሳዑዲ ዓረቢያ የመገናኛ አውታር ሚንሥትር ቱርኪ አል ሻባናህ በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ አውታራቸው ላይ ዜናውን አስተባብለዋል። «አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሣልማን ማንቸስተር ዩናይትድን ሊገዙት ነው የሚለው ዘገባ ፍጹም ሐሰት ነው» ሲሉ ጽፈዋል። እንዲያም ኾኖ ግን ከንጉሣዊው ቤተሰብ ሐብት ማንቸስተር ላይ በደጋፊነት ፈሰስ ለማድረግ ንግግር መጀመሩን አልሸሸጉም። በርካታ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች የሣዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ቡድኑን የሚገዙ ከኾነ ከሚወዱት ቡድን እንደሚነጠሉ ሲዝቱ ነበር። አልጋ ወራሹ ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ በአሰቃቂ ኹኔታ ሕይወቱን ባጣው የሳዑዲ አረቢያው ጋዜጠኛ ጀማል ከማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት በሚል ስማቸው ይነሳል።

የሣዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሣልማን
ምስል picture-alliance/abaca/Royal Palace/B. Al Jaloud

ማንቸስተር ዩናይትድ የፊታችን እሁድ በፕሬሚየር ሊጉ ከሊቨርፑል ጋር 27ኛ ግጥሚያውን ያከናውናል።  አርሰናል እና ሳውዝሐምፕተንም በተመሳሳይ ቀን ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ።  ቸልሲ ለኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ዛሬ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ቀጠሮ ስላለው በሳምንቱ መጨረሻ ከብራይተን ጋር ሊያደርግ የነበረው ግጥሚያ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ፍልሚያ  ደግሞ ነገ ማታ፦ የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን የእንግሊዙ ሊቨርፑልን ይገጥማል። የስፔኑ ባርሴሎናም ከፈረንሳዩ ሊዮን ጋር የሚፋለመው በተመሳሳይ ሰአት ነው። ከነገ በስተያ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ እንዲሁም፤ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ከጀርመኑ ሻልከ ጋር ይጋጠማሉ።

በሌላ የስፖርት ዜና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1934 ዓ.ም አንስቶ ከእንግሊዝ ማንቸስተር ሲቲ ከተማ የስፖርት ቁሳቁሶችን በማምረት የሚታወቀው አምብሮ ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የ4 ዓመት ውል መፈጸሙን ገልጧል። ኩባንያው ትናንት በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ባወጣው መረጃ ከፌዴሬሽኑ ጋር የ4 ዓመት አዲስ ትብብር ማድረጉን ገልጦ መደሰቱን ጠቅሷል።  አምብሮ ጽሑፉን ይፋ ባወጣበት ወቅት ባሕር ዳር ከተማ እንደነበር ያሳያል።

የ19 ዓመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ በበርሚንግሐም የ1500 ሜትር የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ለ22 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብር ወሰን መስበሩ አስደምሟል። በውድድሩ የመጨረሻ ሰከንዶች ኢትዮጵያዊ ተፎካካሪው ዮሚፍ ቀጀልቻን በመቅደም ነው ለድል የበቃው። ክብር ወሰኑ ለኹለት ዐሥርተ-ዓመታት ተይዞ የቆየው በሞሮኳዊው ሒሻም ኤል ጎሩዥ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ