1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 29 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 29 2012

​​​​​​​በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 16 ጨዋታዎች እስካሁን ሊቨርፑልን የሚረታ አልተገኘም። በጊዜያዊ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ የሚመራው ባየር ሙይንሽን ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ መድኃኒት ኩባንያ ሩስያ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ የእገዳ ውሳኔ አስተላልፏል።

https://p.dw.com/p/3UVg0
Äthiopien EFF 11. ordentliche Generalversammlung, Addis Abeba
ምስል DW/O. Tadele

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 16 ጨዋታዎች እስካሁን ሊቨርፑልን የሚረታ አልተገኘም። ላይስተር ሲቲ በቅርብ ርቀት እየተከተለ ነው። በጊዜያዊ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ የሚመራው ባየር ሙይንሽን ሁለተኛ ሽንፈቱን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አስተናግዷል። ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ መድኃኒት ኩባንያ ሩስያ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ ሰኞ ኅዳር 29 ቀን፣ 2012 ዓ.ም የእገዳ ውሳኔ አስተላልፏል። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ አንቶኒ ጆሹዋ ቀበቶውን ማስመለስ ችሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አከናውኗል። 

እግር ኳስ

Äthiopien Isaias Jira, EFF-Präsident
ምስል DW/O. Tadele

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎችን ከመዳሰሳችን በፊት የኢትዮጵያ እና የጎረቤት ሃገራት እግር ኳስን እንቃኛለን። ዩጋንዳ ውስጥ ዘንድሮ በሚከናወነው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤቶች (CECAFA 2019) የእግር ኳስ ግጥሚያ ኤርትራ ከዐሥር ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያ የኾነውን ድል አስመዝግባለች። በገንዘብ ችግር በውድድሩ እንዳልተሳተፈ የተነገረለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ይገኝበት በነበረው ምድብ ኤርትራ 1 ለ0 ያሸነፈችው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድንን ነው። በውድድሩ ብቸኛዋን ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ጨዋታ 45 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረው 2ኛው ደቂቃ ላይ ነው ሮቤል ኪዳኔ ከመረብ ያሳረፈው።  

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ምድብ ከኤርትራ፣ ቡሩንዲ እና ዩጋንዳ ጋር ተደልድላ ነበር። ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ቡድን ከውድድሩ ራሱን አግልሏል። ትናንት በተከናወነ የሴካፋ ግጥሚያ ኬንያ ታንዛኒያን 1 ለ0 ስታሸንፍ፤ ሱዳን እና ዛንዚባር አንድ እኩል ተለያይተዋል።  

በሴካፋ ተካፋይ ያልኾነችው ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኗ 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ አከናውኗል። የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛው ዖምና ታደለ ትናንት በጉባኤው ላይ ተገኝቶ ነበር። በጉባኤው በተለይ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደነበር ገልጧል። 

ፕሬሚየር ሊግ

Fußball UK Burnley vs. Manchester City
ምስል Getty Images/A. Livesey

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 16ኛ ዙር ጨዋታ የመጨረሻ ግጥሚያ በአርሰናል እና ዌስትሀም ዩናይትድ መካከል ዛሬ ማታ ይከናወናል። 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በ19 ነጥብ ተስተካካይ ኾኖ ከሚከተለው ብራይተን ለመራቅ፤ ዌስትሀም ዩናይትድ ደግሞ ካለበት 16ኛ ደረጃ ቁልቁል ላለመውረድ የሚደረግ ፍልሚያ ነው የዛሬው ግጥሚያ። ትናንት ሼፊልድ ዩናይትድ ኖርዊች ሲሲን 2 ለ1 ሲረታ፤ ብራይተን እና ዎልቨርሀምፕተን ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ኒውካስል ዩናይትድ ሳውዝሀምተንን 2 ለ1 አሸንፎ 10ኛ ደረጃን ተቆናጧል። ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ይበልጣል። በሊቨርፑል በስምንት ነጥብ የሚበለጠው ላይስተር ሲቲ አስቶን ቪላን በሰፋ ልዩነት 4 ለ1 አሸንፏል።

ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ1 ድል አድርጎ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። የማንቸስተር ዩናይትድ የቅዳሜ ዕለት ድል ማንቸስተር ሲቲ በዋንጫ ግስጋሴው ሊቨርፑል ላይ ለመድረስ የነበረውን ተስፋ አመናምኗል።  ማንቸስተር ዩናይትድ 24 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በኤቨርተን 3 ለ1 የተሸነፈው ቸልሲ በ29 ነጥብ አራተኛ፤ ማንቸስተር ሲቲ 32 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። መሪው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በርመስን 3 ለ 0 ድል አድርጎ ነጥቡን ወደ 46 ከፍ በማድረግ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ 14ኛ ግጥሚያ መሪው ቦሩስያ ሞየንሽንግላድባህኅ ባየር ሙይንሽንን 2 ለ1 አሸንፏል፤ ነጥቡንም 31 ማድረስ ችሏል። ላይፕሲሽ 30፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 26፤ ሻልከ 25፤ ፍራይቡርግ 25፤ ባየር ሌቨርኩሰን 25፤ ባየር ሙይንሽን 24 ነጥብ ይዘው ከሁለተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ባየር ሙይንሽን በጊዜያዊ አሰልጣኙ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ የቅዳሜው ሁለተኛ ሽንፈቱ ነው። ቀደም ሲል በባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ 2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። በቅዳሜው ጨዋታ ግን ባየር ሙይንሽን ለ1 ሰአት ያኽል በጨዋታ ልቆ ታይቷል።

ቡንደስሊጋ

UEFA Champions League | Roter Stern Belgrad vs FC Bayern München
ምስል Reuters/N. Djurovic

ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ሞየንሽንግላድባህኅ ከ1969 እስከ 1977 ድረስ ባሉት ስምንት ዓመታት ዘጠኝ የቡንደስሊጋ ዋንጫዎችን ተጋርተዋል። አምስቱን ያሸነፈው ግላድባኅ ሲሆን፤ አራቱ የባየርን ነበር።  የግብ አዳኙ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ባለፉት ሦስት የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች ግብ ማስቆጠር ተስኖታል። ባየር ሙይንሽን ባለቀ ሰአት 90+1 ላይ ዣቪ ማርቲኔዝ መጥፎ ጥፋት ፈጽሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ በተገኘው ፍጹም ቅጣት ምት 90+2 ላይ ራሚ ቤንዜባይኒ የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሯል። የባየር ሙይንሽን አዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት አስኪመጣ አራት ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቃቸዋል። ረቡእ በሻምፒዮንስ ሊግ ከቶትንሀም ጋር ይፋለማሉ፤ በቡንደስሊጋው ደግሞ አሊያንስ አሬና ካይ ከብሬመን፤ ከፍራይቡርግ በሜዳው፤ ከዚያም በሜዳቸው ከቮልፍስቡርግ ይጫወታሉ።

ቡጢ

Boxen IBF, WBA, WBO & IBO World Heavyweight Titel | Andy Ruiz Jr vs. Anthony Joshua
ምስል Action Images via Reuters/A. Couldridge

አንቶኒ ጆሹዋ በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ወሳኝ በነበረው ግጥሚያ አንዲ ሩይዝን በማሸነፍ ቀበቶውን አስመልሷል። አንቶኒ ጆሹዋ ከስድስት ወራት በፊት በሜክሲኮዋዊው አሸማቃቂ የሚባል ሽንፈት ገጥሞት ነበር። ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አንቶኒ ጆሹዋ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ለመጋጠም የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አጥብቆ ተችቷል። ቅዳሜ ዕለት ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በተከናወነው ፍልሚያ የብሪታንያው አንቶኒ ጆሹዋ በ12ኛው ዙር ነበር ያሸነፈው። ዳኞች 119 ለ110 እና 119 ለ109 በኾነ ነጥብ ነው አንቶኒን አሸናፊ ያደረጉት። ሰኔ ወር ላይ ሜክሲኮ አሜሪካዊው አንዲ ሩይዝ አንቶኒን አሸንፎት ነበር። እናም በቅዳሜው ድል አንቶኒ ጆሹዋ ቀበቶዎቹን በመላ ማስመለስ ችሏል። እንዲህ አይነት የከባድ ሚዛን ቡጢ መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ሲከናወን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አትሌቲክስ

Russland Moskau Das Gebäude des Russischen Olympischen Komitees
ምስል imago images/ITAR-TASS/A. Shcherbak

ሩስያ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከማንኛውም አይነት ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ተካፋይ እንዳትሆን ዛሬ እገዳ ተጥሎባታል። እገዳውን ዛሬ ያስተላለፈው ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ (WADA)ነው።  ዋዳ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሩስያ አትሌቶቿ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ላይ በርካታ ሜዳሊያዎችን እንዲሰበስቡ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን መጠቀማቸውን ሸሽጋለች በሚል ነው። ቀደም ሲል የሩስያ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ (RUSADA)የስፖርተኞቹን የደም ናሙና ውጤት ሸሽጓል የሚል ክስ በተደጋጋሚ ሲሰነዘርበት ነበር።  ሩስያ በዋዳ ውሳኔ መሰረት፦ በ2020 የቶኪዮ እና 2022 የፔኪንግ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች እንዲሁም በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ መሳተፍ አትችልም። የሩስያ የስፖርት ሚንስትር የነበረውን ስፖርታዊ ቅሌት ለመፍታት ያልተደረገ ነገር የለም ብለዋል። ሩስያ ላይ የእገዳ ውሳኔው ዛሬ የተላለፈው ላውዛኔ ውስጥ በተሰበሰበው የዋዳ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ