1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስጋት ያጠላባት ሞያሌ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2011

ግጭት በበረታባት የሞያሌ ከተማ ዛሬም የመንግሥትና የግል የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉ እንደተዘጉ የሚገኙ ሲሆን በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች አልፎ አልፎም የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ነዋሪዎቿ ተናግረዋል፡፡በተለይም ቀበና በተባለ ቀበሌ ዛሬ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎቹ ለዲ ደብሊው ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3AH3Y
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

ዛሬም ተኩስ እንደነበረ ነዋሪዎች ይናገራሉ

ከአዲስ አበባ በ 723 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው የጠረፍ ከተማዋ ሞያሌ ከባለፈው ረብዕ ጀምሮ በግጭት ስጋት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በሶማሌ የገሪና በኦሮሞ የቦረና ጎሳዎች መካካል የተነሳው የአስተዳደር ይገባኛል ጥያቄ ዳግም ላገረሸው ግጭት ምክንያት መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት / በከተማዋ ባንኮች ፤ የመንግሥት ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች ዛሬም ድረስ እንደተዘጉ ይገኛሉ፡፡ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭቱ ትናንት ጋብ ብሎ የዋለ ቢመስልም ዛሬ ግን በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ውሏል፡፡ በተለይም ቀበና በተባለች ቀበሌ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱንና በጥይት የቆሰሉ አራት ሰዎችም ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ነው እንድ የከተማው ነዋሪ ለዲ ደብሊው የገለጹት፡፡
ዲ ደብሊው በስልክ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲኜ ቦሩ / በሞያሌ በተከሰተው ግጭት በሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ከመድረሱም በላይ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ ግጭቱን ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ እንዲገባ ፤ የተሰደዱ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱና ለግጭቱ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ከመሠረታቸው እንዲፈቱ የሚሉ ጥያቄዎችን ለፌደራል መንግሥት ማቅረባቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡ 

የቀድሞው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄነራል እና የአሁኑ የሰላም ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው / የሞያሌ ግጭት ዛሬ የተጀመረ አንዳልሆነና ጉዳዩም ከአስተዳደር የባለቤትነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡
በአሁኑወቅት ዳግም ያገረሸውን ግጭት ለመቆጣጠር የፌደራሉ መንግሥት ከየአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ነው ለዲ ደብሊው የገለጹት፡፡
በሞያሌ ከተማ ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በዘለቀው ግጭት እስከአሁን በሁለቱም ወገን 34 ሰዎች ሞተዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ፤ ጥቂት የማይባሉም ነዋሪዎችም ቤት ንብረታቸው ጥለቅ ተሰደዋል፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የአገሪቱ መከላከያ ሚንስቴር የሁለቱ ክልሎች ታጣቂዎች በአስቸኳይ ከትንኮሳ እንዲታቀቡ ሲል ባለፈው ቅዳሜ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየው

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ