1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢጣልያ እና የአውሮጳ ህብረት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22 2010

ኢጣልያ  ስደተኞችን እንደ መያዣ በመጠቀም የወሰደችው እርምጃ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነው። ዲዮቺቲ የታደገቻቸው ስደተኞች ጉዳይ እሁድ ፍጻሜ ማግኘቱ እፎይታ ካስገኘላቸው መካከል ዩ ኤን ኤች ሲ አር አንዱ ነው። ሆኖም ኮሚሽኑ መሰል ችግር በተፈጠረ ቁጥር ስደተኞች ማንገላታቱ እንዲቆም አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/33ucJ
Italien Migranten verlassen Diciotti Rettungsschiff
ምስል Reuters/A. Parrinello

የኢጣልያ እና የአውሮጳ ህብረት ውዝግብ

ከ12 ቀናት በፊት የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ከሜዴትራንያን ባህር ታድጎ ወደ ኢጣልያ ወደብ ያመጣቸው ስደተኞች ጉዳይ ሲያወዛግብ ቆይቶ ባለፈው እሁድ ፍጻሜ አግኝቷል። የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞቹን ካልወሰዱ ድዮቺቲ ከተባለችው ከተሳፈሩባት መርከብ  እንዳይወርዱ የከለከለችው ኢጣልያ፣ የአውሮጳ ህብረት አባል የሆነችው አየርላንድ 20 ውን የአውሮጳ ህብረት አባል ያልሆነች አልባንያም 20 ውን ለመውሰድ ቃል ከገቡ እና የኢጣልያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም 100 ያህሉን  ለመንከባከብ ከተስማማች በኋላ ስደተኞቹ እንዲወርዱ ፈቅዳለች። መርከብዋ መጀመሪያ ከታደገቻቸው መካከል 40 የሚሆኑ ህጻናት ወጣቶች እና አዋቂዎች ከተወሰኑ ቀናት በኋላ እንዲወጡ ሲደረግ 137ቱ ግን እስከ እሁድ ቆይተዋል። ኢጣልያ ሜዴትራንያን ባህር በኩል የሚመጡ ስደተኞችን የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ከዚህ ቀደም በገቡት ቃል መሠረት እስካልተከፋፈሉ ድረስ ስደተኞቹን አላስገባም ከማለት በተጨማሪ ለህብረቱ የምትከፍለውን መዋጮም እንደምታቆምም ዝታ ነበር ። ሆኖም ኢጣልያ  ስደተኞችን እንደ መያዣ በመጠቀም የወሰደችው ይህ እርምጃ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነው። ዲዮቺቲ የታደገቻቸው ስደተኞች ጉዳይ እሁድ ፍጻሜ ማግኘቱ እፎይታ ካስገኘላቸው መካከል የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ዩ ኤን ኤች ሲ አር አንዱ ነው። ሆኖም ኮሚሽኑ መሰል ችግር በተፈጠረ ቁጥር ስደተኞች ማንገላታቱ እንዲቆም ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ ማሳሰቡ አልቀረም። በኢጣልያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ ባርባራ ሞሊናርዮ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የህይወት አድን ሥራ መሆን አለበት።
«የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ችግሩን በጋራ የሚፈቱበት ስልት እንዲቀይሱ ይጠይቃል። ይኽውም ስደተኞች ከተጫኑባቸው ጀልባዎች ይውረዱ አይውረዱ ብሎ በየጊዜው  ከመደራደር በእቅዳቸው መሠረት ሊያከናውኑት ይችላሉ። ሌላው እኛ የምንጠይቀው ነገር የሰው ህይወት ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዲሆን ነው።በአባል ሀገራት መካከል ትብብር ሊኖር ይገባል። ከዚሁ ጋርም የሰብዓዊ መብት መርሆች ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። የስደተኞችን ህይወት መታደግ ከተቻለ በኋላ ወዲያውኑ ከተሳፈሩበት እንዲወርዱ ይደረጋል ይህ የሚሆነውም በአግባቡ መረዳት እንዲችሉ ነው።»
የኢጣልያን እርምጃ ከእገታ ጋር የሚያስተካክሉ ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግጋትን እየተጻረረች ነው ሲሉ ይወነጅሏታል። ኢጣልያ ይህን ለማድረግ የተገደደችው በአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ቸልተኝነት ምክንያት ነው የሚሉት ደግሞ ህብረቱ ችግሩን የሚፈታ የፖለቲካ መርህ እንዲያወጣ ይጠይቃሉ። ህብረቱ በስደተኞች ጉዳይ ላይ እየተነጋገረ መፍትሄ የሚላቸውን የተለያዩ ውሳኔዎች ሲያሳልፍ ቆይቷል። ሆኖም የዶቼቬለ የብራሰልስ ወኪል ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ዋነኛው ችግር መንግሥታት የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ማድረግ አለመቻላቸው ነው። ይህን ማድረግ ለምን እንደተሳናቸው ገበያው ያስረዳል።
ስደተኞቹን ጭነው ወደ ኢጣልያም ሆነ ወደ ማልታ የባህር ዳርቻዎች የሚጠጉ የተለያዩ መርከቦች ሰዎቹን እንዳያወርዱ እየተከለከሉ ለቀናት የሚጉልሉባቸው አጋጣሚዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተደጋገሙ ነው። ከአሁን በኋላም ተመሳሳይ ችግር ላለመድረሱ ምንም ዓይነት ዋስትና አለመኖሩ አስግቷል። የዩኤን ኤች ሲአርዋ ባርባራ ሞሊናርዮ ድርጅታቸው ዩ ኤን ኤች ሲ አር እና ዓለም አቀፉ የፍለሰተኞች ጉዳይ ድርጅት አይ ኦ ኤም ጉዳዩ የሚያሰጋቸው እንደሆነ እና ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውም ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ። እናም  በርሳቸው አስተያየት የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ለዚህ ችግር የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይኖርባቸዋል።  
«አሁን የሆነው የማንቂያ ጥሪ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ ቀጣዩ ጀልባ ምን ሊደርስበት እንደሚችል ከወዲሁ ያሳስበናል። ለዚህም ነው ከባህር ህይወታቸው ለተረፈ ሰዎች የተባበረ እና እምነት የሚጣልበት አውሮጳዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ነው ጥሪ የምናስተላልፈው።»
የአውሮጳ ህብረት ወደ ክፍለ ዓለሙ ስደተኞች በባህር እንዳይመጡ ለማስቆም የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ ቀጥሏል። ገበያው እንደሚለው አሉ የተባሉ የስደተኞች መተላለፊያዎችን የመዝጋቱ ጥረቱ ቀጥሏል። ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለሱም እንዲሁ ። 
ባለፈው ሳምንት በተፈጠረው ቀውስ ላይ ለመነጋገር የህብረቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራስልሰ ቤልጅየም ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ይሁን እና ይሰበሰባሉ ከተባሉት 12 ሚኒስትሮች 9 ብቻ ከመገኘታቸው በተጨማሪ ከዲዮቺቲ መርከብ እንዳይወርዱ ለተከለከሉት ስደተኞች መፍትሄ ላይ ሳይደርሱ ነበር የተለያዩት። ያም ሆኖ ጉዳዩ በቅርቡ የአባል ሀገራት መሪዎች በሚያካሂዱት ጉባኤ ላይ መነሳቱ አይቀርም ይላል ገበያው።
ድምጽ  ገበያው
ምንም እንኳን በጎርጎሮሳዊው 2018 ወደ አውሮጳ የሚገባው ስደተኛ ቁጥር ቢቀንስም በአንጻሩ በጉዞ ላይ ህይወታቸው የሚጠፋው ቁጥር ግን ከፍተኛ ነው። በ2018 ብቻ ከ1600 በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። የስደተኞችን ሞት ለማስቀረት የስደት ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ዩ ኤን ኤች ሲ አርን የመሳሰሉ ድርጅቶች ዘላቂ የሚሉት መፍትሄ ነው። 

Schiff Diciotti vor der italienischen Küste
ምስል picture-alliance/dpa/I. Petyx
Italien Migranten können Rettungsschiff «Diciotti» verlassen
ምስል picture-alliance/AP Photo/O. Scardino

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ