1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ስዕሎቼ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ» ጌታቸዉ ብርኃኑ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 13 2013

በባህላዊ የአሳሳል ስልትን ከወላጅ አባቱ እንደቀሰመ እና በዚሁ ጥበብ እንዳደገ የሚናገረዉ ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ ሰሞኑን አንድ ታዋቂ የፓሪስ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ በቤሌቪል ክፍለ ከተማ ሲል ሰዓሊ ብርኃኑን በማወደስ አስተዋዉቆታል።

https://p.dw.com/p/3zBsH
Äthiopien, Addis Abeba | Kunst von Getachew Berhanu
ምስል Getachew Berhanu

ፓሪስ የዓለም ሃገራት ሕዝብ በሰላም እንደፈለገዉ የሚኖርባት ከተማ ነች

በባህላዊ የአሳሳል ስልትን ከወላጅ አባቱ እንደቀሰመ እና በዚሁ ጥበብ እንዳደገ የሚናገረዉ ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ ሰሞኑን አንድ ታዋቂ የፓሪስ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እስከ ፓሪስ በቤሌቪል ክፍለ ከተማ ሲል ሰዓሊ ብርኃኑን በማወደስ አስተዋዉቆታል። የጥበብ ትርኢቱ ላይ ስዕሎቻቸዉን ካቀረቡ ሰዓልያን መካከል ኢትዮጵያዊዉ ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ እና አንድ የዩክሬይን ተወላጅ ብቻ እንደነበሩ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዉ ጌታቸዉ ተናግሮአል። ብርኃኑ ከሰዓልያኑ መካከል ተመርጦ በጋዜጣዉ ላይ የቀረበዉ ስዕሎቹ ለየት ያለ ያሳሳል ስልት ስለያዙ እና በበርካታ የስዕል አፍቃሪዎች እና ሰዓልያን በመወደሱም እንደሆነ ተነግሮአል። ቡሩሽን ከቀለም አገናኝቼ ስዕልን የየእለት ተግባሪ አድርጌ ከተቀመጥኩ ወደ 30 ዓመት ሆነኝ የሚለዉ ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ፤ ፓሪስን መኖርያ ከተማዉን ካደረገ ወደ አራት ዓመት አስቆጥሮአል።

Äthiopien, Addis Abeba | Kunst von Getachew Berhanu
ምስል Getachew Berhanu

« ስዕሎቼ እዚህ ፈረንሳይ ከሚታየዉ የአሳሳል ስልት ለየት ያለ በመሆኑ ብዙዎች ይደነቃሉ። የኔ ስዕሎች ይበልጥ ኢትዮጵያዊ መልክን የያዙ ናቸዉ። ኢትዮጵያ ስዕል ስንል በቀለማት የደመቁ ናቸዉ ማለት ነዉ። በተለይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን የያዙ ናቸዉ» ይላል ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ።  በፓሪስ ሲኖር ወደ አራት ዓመት ሆኖታል።

Äthiopien, Addis Abeba | Kunst von Getachew Berhanu
ምስል Getachew Berhanu

ጌታቸዉ ወደ ፓሪስ ከመምጣቱ በፊት ግን ማዮት በምትባል ሲሸልስ አጠገብ በምትገኝ ደሴት ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ሦስት ዓመት ገደማ ኖርዋል። ማዮት በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች እና ነዋሪዎችዋ ከፈረንሳይ ጋር መሆን ይኃለናል ብለዉ በሪፈረንደም ወስነዉ የፈረንሳይ አካል የሆነች ሃገር ናት። ማዮት በጣም ብዙ ቱሪስቶች የሚጎበኝዋት ደሴት ናትም ሲል አክሎአል። ፓሪስ የዓለም ሃገር መዲና ነች የሚለዉ ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ፤ በየክፍለ ከተማዉ ከዓለም የመጡ ዜጎች ባህላቸዉን የሚያስተዋዉቁበት፤ ምግብ ቤት አልያም፤ የገፀ-በረከት መሸጫ ሱቆች አዉደ ርዕዮች ይገኛሉ። የዉጭ ዜጎችም ባህላቸዉን እያስተዋወቁ ነዉ የሚኖሩት። ይህን ጉዳይ  አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ ሁኔታ ጋር ሳስተያየዉ በጣም ያሳዝነኛል፤ ሲል ስሜቱን ተናግሮአል።   

የኮቪድ ወረርሽኝ ከመጣ ወዲህ የስራችን ሁኔታ ተቀዛቀዘ እንጂ ፓሪስ ለሥነ-ጥበበኞች ፍፁም የተመቸች ሃገር ናት ሲልም ይገልጻታል። አዲስ አበባ የተወለደው ጌታቸው ብርሃኑ እራሱ ከባህላዊ ሰዓሊዎች ጋር የሰለጠነው አርቲስት አባቱ ባስተማረው ትምህርት “ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥዕላዊ ወግ ውስጥ ተጠምቆ ነዉ። ሰዓሊ የሚል ዲፕሎማም ይሁን ዲግሪ እንደሌለዉ በፈገግታ ነዉ። ይሁንና ስዕሎቹ በዓለም መድረክ ተፈላጊነታቸዉ እየጨመረ የመጣ ይመስላል።  ጌታቸዉ ብርኃኑ የጥበብ ስራዉን ይዞ በሃገር ቤት ዓዉደርእይን የመዘርጋት ህልምን ሰንቆአል። በጥበብ ስራዉ ሃገሩን ያስጠራዉን ሰዓሊ ጌታቸዉ ብርኃኑ ለሰጠን ቃለ ምልልስ በማመስገን ሙሉ ቃለ ምልልሱን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

Äthiopien, Addis Abeba | Getachew Berhanu
ምስል Getachew Berhanu

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ