1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለተራዘመው የኢትዮጵያ የሰላም ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ ምን አለች?

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 2015

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ንግግር በእቅዱ መሰረት እሑድ ማብቃት ነበረበት ቢባልም አሁንም ቀጥሏል። ስለ ንግግሩ ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም። የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትንናት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ የሰላም ንግግሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4IvuO
USA Ukraine-Russland-Konflikt | Pressesprecher Ned Price
ምስል Tom Brenner/AP Photo/picture alliance

«በመካከላቸው ርቀት እንዳለ አመላካች ነው»

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ንግግር በእቅዱ መሰረት እሑድ ማብቃት ቢባልም አሁንም ቀጥሏል። ስለ ንግግሩ ዝርዝር መረጃዎች ባይወጡም በተወያዮች መካከል ልዩነቶች መጉላታቸው ተጠቁሟል። የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትንናት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ የሰላም ንግግሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ስለሁኔታው ለአንድ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ተወካዮች ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ካለፈው ሳምንት አንስቶ የጀመሩት የሰላም ንግግር እንደቀጠለ ነው። ተወያዮቹ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ የሚያሳይ ይህ ነው የተባለ ዝርዝር መረጃ ግን እስካሁን አልወጣም። በቅጡ የሚታወቀው በሁለቱ ተወያዮች መካከል የነበረው ንግግር እሑድ ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ አለመጠናቀቁ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትንናት ማታ ስለተለያዩ የዓለም ጉዳዮች ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ጥያቄ እና መልስ ስለኢትዮጵያም ተጠይቀው ነበር። የደቡብ አፍሪቃው የሰላም ንግግር ምናልባትም እስከ ረቡዕ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ተገልጧል። ንግግሩ የሚያበቃበት ቀን መቼ እንደሆነ አለመገለጡም «ንግግሩ እየከሸፈ ነው ለማለት አመላካች ነው ወይ?» በሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

«ተወያዮቹ ደቡብ አፍሪቃ የደረሱት ትንሽ በመካከላቸው ርቀት እንዳለ ለመሆኑ አመላካች ነው። ሆኖም ተወያዮቹ አንድ ላይ ለመቀመጥ ያላቸው ፍላጎት ቀጣይ ለመሆኑም አመላካች ነው። ያም ገንቢ በሆነ ድባብ፤ ከምንም በላይ ተወያዮቹ ልዩነቶቻቸውን ሊነጋገሩ በሚያስችል እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት በሚያጠብ መንፈስ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።»

ቃል አቀባዩ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪቃ ኅብረት መሩ የውይይት ሒደት መሳተፏን እንደምትገፋበትም ተናግረዋል። የሀገራቸው የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ንግግሩ እስከቀጠለ ድረስ እዚያው እንደሚቆዩም ገልጠዋል።

USA Ned Price
የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ከጋዜጠኞች ጋር በቃለ ምልልስ ወቅትምስል Nicholas Kamm/AP Photo/picture alliance

«የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልእክተኛችን ማይክ ሐመር ተሳታፊ እና ታዛቢ የሆኑበት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ እየተካኼደ ያለው ንግግር ይቀጥላል ብለን እናምናለን። ይህ ውይይት እና ንግግር ተወያዮቹ አንድ ላይ እንዲቀመጡ እጅግ መልካም አጋጣሚ ነው ብለን እናምናለን። ተወያዮቹ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በእነዚህ አራት ግቦች ላይ እመርታ ያሳያሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

ጦርነቱ በአስቸኳይ ይቁም፦ ዩናይትድ ስቴትስ

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ተወካዮች መካከል በዋናነት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ንግግሩ እንዲቀጥል ፍላጎት ከማሳየትም ባሻገር በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኗን ገልጣለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ባወጣው መግለጫ፦ «ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት» ያላቸው ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሲባል እየፈጠሯቸው የሚገኙ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን አውግዟል። «በምዕራባውያን የተለያዩ አካላት አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ የሚነዛው የሐሰት ስም ማጥፋቶችን» መንግሥት አይታገስም ሲልም በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል አስጠንቅቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ከቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ቅንጅት የአፍሪቃው ክፍል (CGTN Africa) ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ «በርካታ ጣልቃ ገብነቶች» እንዳሉ ጠቁመዋል።

«በእርግጥም ከግራ እና ከቀኝ በርካታ ጣልቃ ገብነቶች የሚኖሩ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የራሳችን ጉዳይ በራሳችን መንገድ መፍታት እንደምንችል ልንገነዘብ ይገባል። ከርቀት ያለውን ከመስማት ይልቅ የራሳችን ሕግ ማክበር ይሻላል፤ የራሳችን ባሕል ማክበር ይበጃል፤ የራሳችንን ልማዶችን ማክበሩም ያሻል። ያን ማድረግ ከቻልን ሰላም ስኬታማ ይሆናል፤ ያን እንደምናሳካም ተስፋ አለኝ።»

ዓርብ ዕለት በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል የወጣው ሰነድ ይዘትን በተመለከተ ኔድ ፕራይስ ትናንት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ቃል አቀባዩ ለጥያቄው መልስ ሲሰጡም በሠነዱ ቀረበ ያሉት ክስ ላይ ያለው ይዘት እና ዓላማን መቃኘት እንደሚፈልጉ በመጥቀስ የዩናይትድ ስቴትስ ያሉትን አራት ግቦች ዘርዝረዋል።

Äthiopien Symbolbild Tigray-Konflikt
መንገድ ዳር የተተወ ታንክ አጠገብ ወጣቶች አልፈው ሲኼዱ፦ ከፎቶ ማኅደርምስል Eduardo Soteras/AFP

«የዩናይትድ ስቴትስ ግብ፤ የአፍሪቃ ኅብረት መር የማደራደር፤ የማነጋገር ግብ ሲበዛ ቀላል ነው። ሌላ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ የለውም። ዓላማው እጅግ በጣም ግልጽ ነው። በአስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ፤ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ የሰብአዊ ርዳታ እገዛ እንዲዳረስ ማስቻል ነው። በተጨማሪም ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ዋስትና መስጠት እንዲሁም ኤርትራ ከሰሜናዊ ኢትዮጵያ መውጣቷን መመልከት ናቸው። ለጥያቄህ እና ላቀበልከኝ መግለጫ ስለ ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ የሚለው ሦስተኛው ነጥብ ጠቃሚ ነው።»

ዩናይትድ ስቴትስ በፕሪቶሪያው የሰላም ንግግር ከታዛቢነት እና ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆንም ባሻገር ወደ ተለያዩ ሃገራት በመጓዝ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ለማድረግ ስትጥር ተስተውላለች።

አንቶኒ ብሊንከን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዚደንት ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በስልክ ደውለው ስለዚሁ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት አነጋግረዋል። በትዊተር ገጻቸው ላይም ከአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር እጅ ለእጅ የተጨባበጡበት ፎቶግራፍን አያይዘው «ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ እየተካኼደ ስላለው ስለ ኢትዮጵያ ትግራይ የሰላም ንግግር እንዲያብራሩልኝ ሐሙስ ዕለት ሞሳ ፋኪን ኦታዋ ካናዳ ውስጥ አግንቻቸዋለሁ።» በማለት ጽፈዋል።

ስለ ደቡብ አፍሪቃው «የሰላም ንግግር» ምን ይታወቃል?

የሚታወቀው የሰላም ንግግሩን፦ የአፍሪቃ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያሸማግሉት፤ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተሳታፊ እንደሆኑ ነው። የሰላም ንግግሩ መቼ እንደሚያበቃ ግን ዐይታወቅም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ