1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ደሴ ከተማ አቅራቢያ የዛሬ ውጊያ

ዓርብ፣ ጥቅምት 19 2014

ደሴ ከተማ አቅራቢያ ዛሬ ብርቱ ውጊያ እንደነበር አንድ የከተማው የዐይን እማኝ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናገሩ። የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሠዒድ የሱፍ በከተማዪቱ አቅራቢያ የተኩስ ድምጽ የሚሰማ ቢሆንም፤ «ከተማው ላይ ጠላት እንዳሰበው የተረበሸ ነገር የለም» ብለዋል።

https://p.dw.com/p/42Lt7
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በከተማዪቱ አቅራቢያ የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበር

ደሴ ከተማ አቅራቢያ ዛሬ ብርቱ ውጊያ እንደነበር አንድ የከተማው የዐይን እማኝ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናገሩ። የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሠዒድ የሱፍ በከተማዪቱ አቅራቢያ የተኩስ ድምጽ የሚሰማ ቢሆንም፤ «ከተማው ላይ ጠላት እንዳሰበው የተረበሸ ነገር የለም» ብለዋል። የሕዝቡ የተለመደ እንቅስቃሴ መቀጠሉንም ከሰአት ላይ በሰጡት ቃለመጠይቅ አክለው ተናግረዋል። በትናንትናው ዕለት ምንነቱ ያልታወቀ ከባድ ጦር መሣሪያ ባደረሰው ጉዳት አንድ ሰው ላይ ከባድ ሁለት ሰዎች ላይ ቀላል በአጠቃላይ ሦስት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱንም አቶ ሠዒድ ገልጠዋል። የከባድ ጦር መሣሪያ ጥቃቱ ትናንት የተሞከረው  ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች አርፈውበት በነበረው መጠለያ አቅራቢያ ነውም ብለዋል። ዓላማውም መጠለያው ላይ ጉዳት ማድረስ ነበር ሲሉ አክለዋል። 

ደሴ ከተማ አስተዳደር መናፈሻ ክፍለ-ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይመር ሐሠን በበኩላቸው፦ ትናንት እና ከትናንት በስትያ በከባድ ጦር መሣሪያው ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ከትናንትና ወዲያ ገራዶ የሚባለው አካባቢ ትናንት ደግሞ ዘጠኝ ሰአት አካባቢ ላይ «እኔ በር ላይ ከባድ መሣሪያ ወድቆ የአንድ ንፁሃን ሰው ሕይወት ጠፍቷል» ሲሉም አክለዋል። ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ያሉት የባሕር ዛፎች ፍንጣሪውን ቢቀንሱትም መኖሪያ ቤታቸው እና ሱቃቸው ላይ እንዲሁም የጎረቤቶቻቸው መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል። መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ትናንት ሕይወቱ ያለፈው ወጣትም መርሳ ከሚባል አካባቢ ተፈናቅሎ የመጣ መሆኑን ገልጠዋል። በተጨማሪም በትናንቱ ጥቃት ሌላ አንዲት ሴት ቆስላ ሐኪም ቤት በሕክምና ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል። «አሁን ደሴ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ውጊያ ነው ያለው» ብለዋል። የተኩስ ድምፁም ከከተማዪቱ አቅራቢያ የሚሰማ መሆኑን ገልጠዋል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ