1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ መተከል ግድያ የማሕበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች ምን አሉ? 

እሑድ፣ ታኅሣሥ 18 2013

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሀኑ ጁላና የብሔራዊ የመረጃና የደህንነት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አስከትለው መተከል ደርሰው በተመለሱ በሰዓታት ልዩነት በርካቶች የተገደሉበት አስከፊ ጥቃት ተፈጽሟል። የዛሬው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት በጉዳዩ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ይቃኛል

https://p.dw.com/p/3nCEP
Karte Äthiopien Metekel EN

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው መተከል ዞን ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ማለዳ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ እንደገና የሐዘን፤ እንደገና የቁጣ ግፋ ሲልም የውዝግብ መነሾ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትዊተር እና ፌስቡክ ገፆቹ ይፋ ባደረገው መግለጫ እንዳለው ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው በዞኑ ቡለን ወረዳ ውስጥ ነው። ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ በኩጅ የሚባል ሲሆን ከወረዳው ዋና ከተማ 90 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል። 

አካባቢውን የሚያውቁ እና መረጃ የደረሳቸው በርካታ የማሕበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች አሰቃቂውን ጥቃት የሚያሳዩ ያሏቸውን ምስሎች አጋርተዋል። ጨርቅ ጣል የተደረገባቸው በዚሁ ጥቃት የተገደሉ የተባሉ የበርካታ ሰዎች አስከሬኖች በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወሩ ታይተዋል። የቡለን ወጣቶች ድምጽ የተባለ የፌስቡክ ገፅ ትናንት ሐሙስ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖች በጅምላ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን የሚያሳይ ምስል አጋርቷል። ይኸው ገጽ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ረቡዕ ዕለት «የመተከሉ ማይካድራ፤ ቡለን ወረዳ በኩጅ ቀበሌ አሁን ባለው ቆጠራ የሟቾች ቁጥር 170 ደርሷል። በየጫካው የተገደሉትን ሳይቆጠር» የሚል አጭር መልዕት አስፍሮ ነበር። በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች እና የተቃጠሉ መኖሪያ ቤቶች ምስሎችም «በኩጅ ቀበሌ በንፁሀን ለተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የቤኒሻንጉል ልዩ ኃይል መለዮ የለበሱ ተሳታፊ እንደነበሩ ከዓይን እማኞች ለማረጋገጥ ችለናል» በሚለው በዚሁ የቡለን ወጣቶች ድምጽ የተባለ የፌስቡክ ገፅ ላይ ይገኛሉ። 

ሳምራዊት የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ «እንዲሁ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች እየተባለ በመተከል ሕይወታቸው የሚቀጠፈው ንፁሀን ቁጥር ባለፉት ወራት 5ም 10ም 20ም እያለ አዲስ ሳምንት ሲመጣ ያለፈው ቁጥር ብቻ ሆኖ እየተረሳ ዛሬ እዚህ ደረሰ። ሰሚ አጥቶ እንጂ ሕዝቡ ድረሱልኝ ካለ ቆየ» ሲሉ ጽፈዋል። ኦስማን ሐምዛ «የቤኒሻንጉል ሕዝብ ይደመጥ። ይህ የዘወትር ጥያቄዬ ነው። ከመተከል ጭፍጨፋ ጀርባ ማን እንዳለ በገለልተኛ ወገን ይጣራና በይፋ ይገለጥልን» የሚል ጥያቄ በትዊተር አቅርበዋል።

ጥቃት ፈፃሚዎቹ እነማን ናቸው?

እንደ አብዛኞቹ በክልሉ የተፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ እስካሁን በይፋ ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ገዳዮች «ጸረ-ሰላም ኃይሎች» የጥቃቱን ሰለባዎች ደግሞ «ንጹሃን ዜጎች» ብሏቸዋል። ይኸው ጽሕፈት ቤት ባሰራጨው መረጃ የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት «ለውጥን በማይፈልጉ አማጺያን» ጥቃቱ እንደተፈጸመ መግለፁን አስታውቋል። 

እስከ ዕለተ ሐሙስ ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የመተከል ዞን የወቅቱ እና የቀድሞ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። ከታሰሩ መካከል የቤኒሻንጉል ጉምዝ የቀድሞ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የቤጉሕዴፓ ሊቀ-መንበር የነበሩት አድጎ አምሳያ ይገኙበታል። የኢትዮጵያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ምኒስትር ድኤታ ቶማስ ኩዊ፤ የክልሉ ገጠር መንገድ እና ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አድማሱ ሞርካ፤ የጋራ ግዥ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ገመቹ አመንቴ እንደታሰሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ያሰራጨው መግለጫ ይጠቁማል። 

የመተከል ዞን በፌስቡክ ለጸጥታ ጥበቃ ከዚህ ቀደም የተቋቋመውን ኮማንድ ፖስት መግለጫ መሠረት አድርጎ ባሰፈረው አጭር መረጃ ሥር ይኸነው በላይ የተባሉ ግለሰብ «ትንሽ እንኳን አታፍሩም? ገዳይም፣ አስገዳይም፣ ሕዝብ ሰብሳቢም እናንተው» ሲሉ ኮንነዋል። ጥሩዬ ተሰማ ደግሞ «ኮማንድ ፖስቱ መርዶ ለማርዳት ነው እንዴ የተቋቋመው ሕዝቡን ከመታረድ ካላዳነ» ሲሉ የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ተችተዋል። አላምረው ደረሳ «ችግሩ እንደሚከሰት በተደጋጋሚ ብንነግራችሁ አንቀበልም በማለት ሕዝቡን አስፈጃችሁ። የንፁሀን ደም ከእናንተ እጅ ላይ እንዳለ አትዘንጉ። ገዳዮቻችን ጎረቤቶቻችን መሆናቸው በጣም ሀዘናችንን ጥልቅ አድርጎታል።» ብለዋል። 

«ጥቃት ፈፃሚዎች ሕብረተሰቡን አይወክሉም» መባሉ ያልተዋጠላቸው ደምቢ ቦጎ «የተሰጣችሁትን አደራ ወደጎን በመተዉ አመራር ስታጅቡ ቆይታችሁ፤ ካለፈ በኋላ ማዘን በኅብረተሰቡ እንደማሾፍ ይቆጠራል። ጥፋተኞቹ ብሔረሰቡን ካልወከሉ ሲያግዟቸዉ ቆይተዉ የታሰሩ አመረሮችን ማን ነው የወከላቸዉ? ኅብረተሰቡ አይደል እንዴ» የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።
መተከል ሚዲያ ኔትወትክ የተባለ የፌስቡክ ገፅ «ካስጨፈጨፉ በኋላ ተከበዋል ምናምን የሚል ለዜና የማይበቃ ወሬ መስማት አንፈልግም። ነገ ልትፈቷቸው ምን ይፈይዳል? ካስገደላችሁ በኋላ ድራማ መስራታችሁን እንኳ አቁሙ» የሚል መልዕክት አስፍሯል። 

አይመን አሊ «ትክክለኛ ለሰው ልጅ ሞት አዝናችሁ ከሆነ፤ በመተከል ዞን ተጨማሪ መከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አስገብቶ የጉምዝ ሽፍቶች አድኖ እርምጃ መውሰድ ነዉ ወሬው ለሕዝቡ አይጠቅምም» የሚል ጠጠር ያለ አስተያየት አስፍረዋል። ጥላሁን ጉርሜሳ «የምን ኮማንድ ፖስት ነው? ምንም አይፈይዱም። የንጹሀን ዜጎች ደም ከማፍሰስ አልታደጓቸውም። ይቅርታ አድርጉልኝ እንጅ እነሱንም ይጠራጠራቸዋለሁ» ብለዋል። 

ሥጋት እና ፍርሐት

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ በመተከል ዞን እንዲህ የከፋ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያው አይደለም። ተመሳሳይ ጥቃት በዚያ አካባቢ ሊፈጸም ይችላል የሚል ሥጋት ግን አሁንም አለ። 

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር «በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ውስጥ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል። በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ። ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት ያደረግነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም። የጠላቶቻችን ዓላማ በጁንታው ላይ የሠነዘርነውን ብርቱ ኃይል ለመበተን ነው። ይህ የሚሳካ አይደለም። መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል። የምንፈልገውን ውጤት ለማግኘት ሁላችንም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረትና በኅብረት እንድንሠራ ጥሪ አቀርባለሁ።» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ «ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌድራል ፖሊስ እና ከክልሉ ፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት ዜጎቻችን ራሳቸውን ተደራጅተው ከጥቃት መከላከል» አለባቸው ብሏል። 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ