1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አላሙዲ በቅርቡ ሊፈቱ ይችላሉ ተብሏል

ሰኞ፣ ጥር 21 2010

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ታላላቅ ቱጃሮች ገሚሶቹን መፍታት ጀምሯል፡፡ ከተለቀቁት መካከል ልዑል ወሊድ ቢን ጥላል ይገኙበታል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቱጃር ሼህ መሀመድ አላሙዲን ዛሬ አሊያም ነገ ሊፈቱ እንደሚችሉ ሪያድ ከሚገኙ የቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

https://p.dw.com/p/2rj7L
Billionär Al-Waleed Bin Talal bin Abdulaziz al Saud
ምስል Getty Images/AFP/I. S. Kodikara

አላሙዲ በቅርቡ ሊፈቱ ይችላሉ ተብሏል

በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሶስት ወር ሊሞላቸው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ነው የቀራቸው፤ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ታላላቅ ባለሀብቶች፡፡ በሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የሀገሪቱ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከገንዘብ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ  በአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር ጠርጥሮ ነው ዘብጥያ ያወረዳቸው፡፡ ታዲያ ለደረጃቸው የሚመጥን በሚመስል መልኩ በሀገሪቱ አለ የተባለውን ባለ አምስት ኮከብ የሪትዝ ካርልተን ሆቴል ነው ለተጠርጣሪዎቹ ቱጃሮች ማረፊያነት የተመረጠው፡፡ ሀምሳ ሰባተኛው የዓለማችን ቱጃር ልዑል ወሊድ ቢንጥላል ቢን አብዱልአዚዝ መገናኛ ብዙሃን ቅንጡ እስር ቤት ካሉት ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ከመውጣታቸው በፊት  ለሮይተርስ መግለጫ ሰጥተዋል ፤ ለሶስት ወራት ያህል የቆዩበትንም ቤት አስጎብኝተዋል፡፡

Ritz-Carlton in Saudi Arabien
ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto/El-Saqqa

ታዛቢዎች ሽበታቸው ጨመረ ሰውነታቸው ቀነሰ ፤ ጎስቆል ቆል ብለዋል ቢሉም ልዑል ወሊድ ቢን ጥላል ግን ምንም የጎደለብኝ የለም ነው ያሉት፡፡ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት የተስተካከሉት ባይመስልም ጸጉር አስተካካያቸው ጭምር በፈለጉት ጊዜ እንደሚመጣላቸው ከኩባንያዎቻቸው የስራ ኃላፊዎች ጋርም እየተወያዩ ስራቸውን ሲመሩ እንደነበር ነው ያወሱት፡፡ ለእስር የዳረጋቸው ጥፋት ሰርተው ሳይሆን ከሳዑዲ መንግስት ጋር ያለ መናበብ እና ያለ መግባባት ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰትተውታል፡፡

«ምንም የምደብቀው ነገር የለኝም በጣም በተዝናና ሁኔታ ነበር ያሳለፍኩት ፡፡ ለመንግስትም እነሱ እስከፈለጉ ድረስ እዚህ መቆት እንደምችል ነው ስነግራቸው የነበረው፡፡ ምክንቱም በእኔ በኩባንያዎቼም ሆነ ከእኔ ጋር ንኪኪ ባላቸው ተቋማት እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ እንዲያውቁት እና እንዲያረጋግጡት ስለምፈልግ ነው» ብለዋል ወሊድ ቢንጥላል። 

ለሰላሳ ደቂቃ በቆየው የቪድዮ ቃለመጠይቅ ልዑል ወሊድ አያያዛቸውን በተመለከተ ባንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ይቀርብ የነበረውን ዘገባ የተዛባ ብለውታል፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አሁንም ለልዑሉ መፈታት ምክንያቱ የከፈሉት አሊያም ለመክፈል የተስማሙት ገንዘብ ነው ቢሉም እርሳቸው ግን ምንም አይነት ገንዘብ እንዳልከፈሉ ነው ያስታወቁት፡፡

የሳዑዲ አረቢያ ልዩ ዓቃቤ ህግ ምክር ቤት እንዳስታወቀው ደግሞ የሙስናውን ጉዳይ የሚመለከት ልዩ ችሎት  አቋቁሟል፡፡  እንዲመልሱ የተጠየቁትን ገንዘብ ለመመለስ ፍቃደኛ ባልሆኑት ላይም በቅርቡ ክስ ይመሰረታል ፡፡ ከድርድር ውጭ በፍርድ ቤት መዳኘት የወሰኑ ከስልሳ በላይ ባለሀብቶች እና ባለ ስልጣናት በቅርቡ ከርዕሰ መዲናዋ ሪያድ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው ሀየር እስር ቤት መዘዋወራቸው ይታወሳል ፡፡ በቅንጡው የሪትዝ ካርልተን ሆቴል የሚገኙትም ከዘጠና በላይ ባለ ሀብቶች በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውሳኔ እንደሚሰታቸው ተገልጹዋል፡፡ ለዚህም ሆቴሉ ከሚቀጥለው ወር አጋማሽ ጀምሮ መደበኛ ስራውን እንደሚጀምር እያስተዋወቀ መሆኑን በማሳያነት የሚያቀርቡ በርካታ ናቸው፡፡ 

Russland Mohammed bin Salman
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/Pool/P. Golovkin

ትውልደ ኢትዮጵዊው ቱጃር ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በሪትዝ ካርልተን ሆቴል የሚገኙት ተጠርጣሪዎች በርካታ ንብረታቸውም ሆነ ጥሬ ገንዘባቸው በውጭ ሀገር መገኘቱ የሚፈለግባቸውንም ሆነ ያመኑትን ያህል ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ያለው ሂደት የራሱን ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ እስካሁን ለመቆየታቸው ምክናያት ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ነገር ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመረጃ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ 

ሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ሳዑዲ ኣረቢያ ሪያድ ካሉዋቸው ድርጅቶች በአንድኛው የሚገኙ የቅርብ ሰዎቻቸው እንደሚሉት ወደ  ሪትዝ ካርልተን የሚሄዱ ሹፌሮች ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ዛሬ ረፋዱ ላይ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ እውን ባይሆንም በቀጣዮቹ ሰዓታት ሊፈቱ እንደሚችሉ ሌሎች ውስጥ አዋቂ ምንጮችም ለዶቸቨለ ጠቁመዋል፡፡ 

ይሁንና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ እና ከመንግስት ጋር ባደረጉት ድርድር ጉዳያቸው እልባት ያገኙ ባለ ሀብቶችም ሆኑ ባለ ስልጣናት ለሚቀትሉት ሶስት ኣመታት ከሳዑዲ ኣረቢያ መውጣት እንደማይችሉም መመሪያ መተላለፉንም ውስጥ አዋቂ ምንጮች አመልክተዋል፡፡ 

ስለሺ ሽብሩ 

ተስፋለም ወልደየስ

ሒሩት መለሰ