1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሲዳማ...10ኛው የኢትዮጵያ ክልል?

ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 2010

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ዞኑ ወደ ክልል እንዲያድግ በትናንትናው ዕለት በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በሚደነግገው መሠረት ውሳኔው ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ በሕዝበ-ውሳኔ ከጸደቀ ሲዳማ 10ኛው የኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ይሆናል።

https://p.dw.com/p/31mPi
Neujahrsfest der Sidama
ምስል ARCCH

Sidama Zone Council votes for greater Autonomy as a region/MMT - MP3-Stereo

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰብስቦ ሲዳማ 10ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል። የሲዳማ ዞን የባሕል፣ ቱሪዝም እና የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ውሳኔው 161 ገደማ ከሚሆኑት የምክር ቤቱ አባላት አንድም ተቃውሞ አሊያም ድምፀ ተዓቅቦ ሳይገጥመው በሙሉ ድምፅ ጸድቋል። "በወጣቱ አዋቂው ውስጥ ያለ ጥያቄ በመሆኑ ሰፊ ውይይት ነው የተደረገበት። ከዚህ አንፃር ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት በሲዳማ ሕዝብ ውስጥ በምሁራኑ፣ በወጣቶቹ እስከ አርሶ አደር ድረስ ማለት ይቻላል ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ የሲዳማ ሕዝብ በክልል መደራጀት አለብኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ትናትና ባካሔደው አራተኛ ዙር ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ይኸን ውሳኔ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል"

በሕገ-መንግሥት ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ማብራሪያ መሠረት የሲዳማ ዞን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን ሲያጸድቅ ክልል ለመሆን ከሚያስፈልገው ሒደት ግማሽ ያክሉን አጠናቋል ማለት ነው። "የመጀመሪያው በአዋጁ አንቀፅ 21 ላይ እንደተቀመጠው ክልል ይገባኛል ከሚለው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም  ሕዝብ 5 በመቶው በተሰበሰበ ፊርማ መልክ ለራሱ ለብሔረሰቡ ምክር ቤት ማቅረብ አለበት። የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ሲወስን እነዚህ ሒደቶች ተጠናቀዋል ማለት ነው። ከዚያ የብሔረሰቡ ምክር ቤት የሚጠበቅበት በ2/3ኛ ድምፅ ይኸን ጥያቄ መቀበል ነበር።  እንደሰማንው ከሆነ ደግሞ በሙሉ ድምፅ ነው የደገፈው" የሚሉት አቶ ውብሸት የውሳኔ ሐሳቡ በቀጣይነት ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚቀርብ ያስረዳሉ። የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት "በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔ ያዘጋጃል። የሲዳማ ሕዝብ ሕዝበ-ውሳኔ ይቀርብለት እና በአብላጫ ድምፅ ከደገፈው ሒደቱ እዚያ ላይ ያልቃል ማለት ነው"

ይኸ ብቻ ግን በቂ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም የሲዳማ ሕዝብ እንደ ክልል የመቆም ጥያቄ በዞኑ ምክር ቤት ሲጸድቅ ይኸ የመጀመሪያው አይደለም። አካባቢውን ያጠኑ ባለሙያዎች ጥልቅ የሥልጣን ባለቤትነት እና የማንነት ፉክክር አለበት በሚሉት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው ዞን ከ12 አመታት ገደማ በፊት ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔ ገቢራዊ ሳይሆን ቀርቷል። 

"ከ12 አመታት በፊት የሲዳማ ዞን እንዲሁ ተመሳሳይ ውሳኔ በመወሰን በምክር ቤት ደረጃ ጸድቆ ለውሳኔ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ነበር። በወቅቱ ከነበረው የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር ጋር በተደረገ ሥምምነት እንዲቆይ ነው የተደረገው። ሆኖም ግን በሕዝቡ ውስጥ የመልካም አስተዳደር እና የፍትኅ ጥያቄ ሆኖ ነው የከረመው" የሚሉት አቶ ጃጎ አገኘሁ ውሳኔው በመዘግየቱ ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ ተከፍሏል ሲሉ ይናገራሉ።

የሲዳማ ነፃነት ግንባር የውጭ ጉዳይ ኃላፊ እና የሕዝቦች ጥምረት ለነፃነት እና ዴሞክራሲ ዋና ጸሃፊ አቶ ደንቦባ ናቲ ግን ለውሳኔው መሠረዝ የቀድሞው የደኢሕዴን ሹማምንት ጭምር ተጠያቂ ያደርጓቸዋል። "ልክ ትናንትና በመቶ ድምፅ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት እንደ ወሰነው ተወስኖ ክልል የመሆን መብታችን ይከበር ተብሎ የተላለፈውን ጥያቄ ሽፈራው ሽጉጤ ከሕውሓት አመራር ጋር ተነጋግሮ ይኼ መሰረዝ አለበት ብሎ እንደገና ተወካዮችን ገንዘብ ከፍሎ አበል ከፍሎ ሰብስቦ አምጥቶ በግድ አስፈርሞ ከዛሬ 12 አመት በፊት የተወሰነውን ውሳኔ ነው የሰረዘው" ሲሉ ይከሳሉ።

የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ላለፉት 27 አመታት ሲነሳ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ደንቦባ የኢሕአዴግ መንግሥት የክልል መንግሥታትን ሲያዋቅር ጀምሮ ስህተት ተሰርቷል ሲሉ ይተቻሉ። "በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1992 ዓ.ም. በነበረው የሽግግር መንግሥት የተዋቀሩ 14 ክልሎች ነበሩ" የሚሉት አቶ ደንቦባ ክልል ከነበሩ አንዱ  የዛሬው ሲዳማ ዞን እንደሆነ ያስረዳሉ። "በጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ ሕብረተሰቡም ሳይመክርበት በሽግግር ጊዜ ምክር ቤት ተብሎ የተቋቋመውም ሳይመክርበት በአቶ መለስ ዜናዊ እና የዚያን ጊዜ የደቡብ የኢሕአዴግ ተወካይ በነበሩት ቢተው በላይ ብቻ ውሳኔው ተግባራዊ ሆኖ አምስት ክልላዊ መንግሥታት አንድ ሆነው እንዲዋቀሩ ሲደረግ ሲዳማ ተቃውሞውን ሲያሰማ ነበር" ሲሉ ያክላሉ።

የሲዳማ ዞን በሰሜን ምሥራቅ ከኦሮሚያ፣ በምዕራብ ከወላይታ በደቡብ ከጌዲዖ ይዋሰናል። ከአዲስ አበባ ሞያሌ የተዘረጋው አውራ ጎዳና ዞኑን ለሁለት ሰንጥቆት የሚያልፍ ሲሆን ለሲዳማ ሕዝብ እርሻ እና ከብት እርባታ ዋንኛ የኑሮ መሠረቶች ናቸው።  ቡናም ያመርታል። አቶ ደንቦባ ዞኑ ወደ ክልል ቢያድግ ለሲዳማ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ባህላዊ ፋይዳ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ