1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሲቲ ቢንቲ ሳአድ

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2010

የዛንዚባር ዝነኛ ድምጻዊት እና የሙዚቃ ደራሲ ነበሩ። በምስራቅ አፍሪካ ለገበያ አልበም በማስቀረጽም የመጀመሪያዋ ነበሩ፤ ሲቲ ቢኒቲ ሳአድ። “የታራብ ሙዚቃ እናት” የሚባሉት ሲቲ በአካባቢው ሙዚቃ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ሴቶች በጥበቡ ዘርፍ እንዲሳተፉ መንገዱን በመክፈት ብቻ ሳይሆን በዛንዚባርም የወንዶችን የበላይነት በመገዳደርም ይታወቃሉ።   

https://p.dw.com/p/304xv
Siti binti Saad
ምስል Comic Republic

የታራብ ሙዚቃ እናት ሲቲ

የሰማችሁት “ዌዌ ፓካ” የተሰኘው ዘፈን ሲቲ ቢንቲ ሰአድ በ1920ዎቹ መጨረሻ ካስቀረጿቸው በርካታ ዜማዎች መካከል አንዱን ነው። ያኔ የእኚህን የዛንዚባር ዕንቁ ዘፋኝ ለየት ያለ ድምጽ ለመቅረጽ ግራማፎን የተባለው የብሪታንያ ኩባንያ እርሳቸውን እና ሙዚቃ ተጨዋቾቻቸውን በሞላ ወደ ቦምቤይ ህንድ ወስዷቸው ነበር። በወቅቱ በእርሳቸው ሀገር ምንም ዓይነት የድምጽ መቅረጫ ስቱዲዩ አልነበረምና ነው ጉዞው ያስፈለገው። በውጤቱም 250 ዘፈኖች መቅዳት ተቻለ። ከጎርጎሮሳዊው 1928 እስከ 1931 ዓ.ም. በነበሩ ሶስት ዓመታት ብቻ 72 ሺህ ቅጂዎችም ተቸበቸቡ።

የሲቲ የአልበም ታሪክ የታላቂቱን ከያኒ ችሎታ እንደው ለማሳየት ተነሳ እንጂ የእርሳቸው እውነተኛ ኃይል ከዚህም የላቀ ነው። ማርያም ሃምዳን በዛንዚባር ያለች ሙዚቀኛም ጋዜጠኛም ናት። የሲቲ ቢንቲ ሳአድን ሙዚቃዎችን ከመጫወትም ሌላ ስለ እርሳቸው ህይወት ጥናት አካሄዳለች።

በጣም ቆንጆ እና ጉልበታም ድምጽ ነበራቸው። ታዳሚያቸውን በቀላሉ መቆጣጠር ይችሉ ነበር።

Siti binti Saad
ምስል Comic Republic

እንደ ማርያም ገለጻ ከሆነ ሲቲ ቢንቲ ሳአድ የዝና ጣራ ላይ ከመድረሳቸው በፊት አነሳሳቸው ሌላ ገጽታ ነበረው። በጎርጎሮሳዊው 1880 ዓ ም ፉምባ በተባለች የዛንዚባር መንደር ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱት ሲቲ ምንም ዓይነት መደበኛ ትምህርት አልቀሰሙም። ኑሯቸውን ለመደገፍ የሸክላ ውጤቶችን በመንገድ ላይ ይሸጡ በነበረ ወቅት የደንበኞችን አትኩሮት ለመሳብ ይዘፍኑ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1911 ከትውልድ መንደራቸው ወደ ከተማ ያቀኑት ሲቲ በዚያ ከተለያዩ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል። አረብኛ ተምረውም የእስልምና ዜማዎችን ያንቆረቆሩት ያዙ። ነገር ግን በጣሙኑ የገነኑት ታራብ በተሰኘው የሙዚቃ ስልት ነው። 

ለዚህ የሙዚቃ ስልት መስፋፋት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ሰይድ ባራጋሽ ቢን ሰይድ የተባሉት ሁለተኛው የዛንዚባር ሱልጣን ናቸው። በጥልቅ ስሜት የሚቀነቀኑ ግጥሞች ከሙዚቃ መሳሪያ ተጫዎቾች ስብስብ ጋር ተዋህደው የሚቀርቡበት ነው- የታራብ የሙዚቃ ስልት። ሲቲ ቢን ሳአድ በአረብኛ ቋንቋ ሊያውም በወንዶች ብቻ ይቀርብ የነበረውን የታራብ ሙዚቃ ደንብ ከእነካቴው ለውጠውታል። ማርያም ሃምዳን፦   

የስዋህሊ ቋንቋን ነበር በዋነኛነት የሚጠቀሙት። እርሳቸው የደረሷቸው ሙዚቃዎች ቀጥታ የህዝቡን ልብ የሚነኩ ነበሩ። ምክንያቱም የእነርሱን የዕለተ ተዕለት ችግሮች እና ፍላጎቶቻቸውን ይዳስሱ ስለነበር። ለምሳሌ ያህል ሴቶች እንዴት በወንዶች ይበደሉ እንደነበር ይዘፍኑ ነበር፤ ስለ መንግስት፣ ስለ ፍትህ ስርዓቱም እንዲሁ።

ማህበራዊ ሂስ በሲቲ ቢንቲ ሰአድ ሙዚቃዎች ዋና ቦታ ነበረው። ስኬታማ ቢሆኑም የመጡበትን አልዘነጉም። ለዛንዚባር ሱልጣን እና ለሀገሪቱ ልሂቃን ሙዚቃቸውን እንደሚያሳዩት ሁሉ በቤታቸው ነጻ የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጁ ነበር። እነዚያ ዝግጅቶች በሀሳብ መለዋወጫነት እና በክርክር ቦታነት አገልግለዋል።

Siti binti Saad
ምስል Comic Republic

እንደ ጋዜጣ ነበሩ ምክንያቱም የሚዘፍኑት ህዝቡ ሊያደምጥ የሚሻውን እና በዚያን ጊዜ ለስርዓቱ መናገር የሚፈልገውን ነው።

ሲቲ ቢኒቲ ሰአድ ህይወታቸው ያለፈው በጎርጎሮሳዊው 1950 ዓ. ም. ነው። አብዛኞቹ ኦሪጅናሌ የዘፈኖቻቸው ቅጂዎች አሁን ባይገኙም ሙዚቃዎቻቸው ግን አሁንም በዛንዚባር ታንዛንያ እና ከዚያም ባሻገር ይከፍቱዋቸዋል። የእርሳቸው ዘፈኖች ከብዙ የታራብ ሙዚቃ ባንዶች ቋሚ የሙዚቃ ዝርዝር ውስጥ የማይጠፉ ናቸው ።

የዛንዚባር ራዲዮ እርሳቸው መጀመሪያ ላይ ያወጧቸውን (ኦሪጅናሌ) ዘፈኖች አልፎ አልፎ  ያስደምጣሉ። በርካታ ቡድኖች ሙዚቃዎቻቸውን ይጫወታሉ። በጣም ቆንጆ ዘፈኖች ነው ያሏቸው ምክንያቱ ደግሞ እንደ ቅይጥ ስለሆኑ ነው። አረብኛ፣ ህንድኛ፣ የአፍሪካዊ፣ የሩቅ ምስራቅ እና የምዕራባውያን ሙዚቃ ተደባልቀውበታል።”   

ሲቲ ቢንቲ ሰአድ ለብዙ የታራብ ዘፋኞች መንገድ የጠረጉ ናቸው። ብዙውን ጊዜ “የምስራቅ አፍሪቃ ድምጽ” እና “የታራብ እናት” በሚል ቁልምጫ የሚጠሩት ሲቲ የዛንዚባርን ባህል በዓለም እንዲታወቅ የድርሻቸውን አበረክተዋል። ከዚህም ባሻገር ሙዚቃ የፖለቲካን ድንበር እንዲሻገር ረድተዋል።

አውደ ጌብስቢትል/ ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

 

ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.