1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን የሽግግር መንግስት ዉል

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2011

አርባ ሚሊዮን የሚሆነዉ የሱዳን ሕዝብ የሚመራዉ አስራ-አንድ አባላት ባሉት «ሉዓላዊ» ምክር ቤት ነዉ።የምክር ቤቱ አባላት ከጦር ጄኔራሎችና ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚወከሉ ናቸዉ።ምክር ቤቱን ለሚቀጥሉት 21 ወራት የጦር ጄኔራል፣ ለቀሪዎቹ 18 ወራት ደግሞ የሲቢሎቹ ተወካይ ይመሩታል።

https://p.dw.com/p/3O8vs
BdTD Sudan Feier zu Machtübergabe des Militärs
ምስል REUTERS

የሱዳኖች ስምምነት፣ ያዲስ ተስፋ መሠረት

የሱዳን የጦር አዛዦችና የፖለቲካ መሪዎች የጋር መንግስት ለመመስረት ተስማሙ።ቅዳሜ።ለስምት ወራት ገዢዎቹን ባደባባይ ሲቃወም፣ሲታገል፣ሲገደል ሲደበደብ የነበረዉ ሕዝብ ርዕሠ ከተማ ካርቱምን በድጋፍ ሰልፍ አጥለቀለቃት።ቅዳሜ።እሁድም ደገመዉ።እፎይታ።ደስታ።ፌስታ።ተስፋም።ዳር ይዘልቅ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ሱዳኖች ሥለ ስራና ቀጠሮ በራሳቸዉ የሚቀልዱበት ሶስት አባባል አላቸዉ አሉ።«ኢንሻአላሕ ቡክራ፣ ማዐል ኤሽ» የሚሉ።IBM አሉት የሶስቱን የአረብኛ አባባል በእንግሊዝኛ አፅሕሮቱ።ግርድፍ ትርጉሙ፣ ፈጣሪ ቢሻ፣ ነገ፣ ችግር የለም እንደማለት ነዉ።

የሱዳን ወታደራዊ ገዢዎችና ወታደራዊዉን አገዛዝ የሚቃወመዉን ሕዝብ የሚያስተባብሩት ወገኖች የጋራ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መደራደር የጀመሩት ሚያዚያ ነበር።ሲደራደሩ፣ሲወዛገቡ፣ሲወቃቀሱ፣ ሰልፈኛ ሲያስግድሉ፣ሸምጋዮችን በተለይ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ሕብረት ዲፕሎማቶችን ሲያመላልሱ ወራት አስቆጠሩ።

ባለፈዉ ሐምሌ አጋማሽ አጠቃላይ የሰላም ዉል ለመፈራረም የሰጡትን ቀጠሮ ሲገፉ፣ሲቀይሩ፣እስከ ኃምሌ ማብቂያ አራዘሙት።የመጀመሪያዉ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ባጭር ጊዜ ይመሠረታል ተብሎ የተነገረዉን «ሉዓላዊ» ምክር ቤት ለመመስረትም እንደዚሁም ቀጠሮ በቀጠሮ ሲቀየር እስከ ቅዳሜ መጠበቅ ግድ ነበር።

ሱዳናዊ የፖለቲካ ተንታኝ አብድል ለጢፍ አል ቡኒ እንደሚሉት የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት ቀጠሮን-በቀጠሮ እየቀየሩ እስካሁን የቆዩት ከወትሮ ሥራና ቀጠሮን ችላ ከማለት የወትሮዉ (IBM) ይትባሕል ይልቅ ከፖለቲካዊ አለመተማመን የመነጨ ነዉ።የሱዳን ሕዝብ ግን የቅዳሜዉን ስምምነት እንደሰማ ደስታ፣ፌስታዉን ባደባባይ ለመግለጥ «ቆይ ነገ» ብሎ አላመነታም።

Sudan Khartum | Zeremonie Unterzeichnung Verfassungserklärung
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/C. Ozdel

ወጣትዋ የካርቱም ሰልፈኛ ሐይጂር ኢብራሒም እንዲሕ ትላለች።

«ዛሬ የመጀመሪያዉ የደስታችን ቀን ነዉ።በረመዳንም ሆነ በኢድ አል-አድኻ አልተደሰትንም ነበር።አሁን ግን ቱቢታችንን የምናወልቅበት ጊዜ ነዉ።ሐዘን ላይ ነበርን።አሁን ግን የሐዘን ልብሳችንን የምንቀይርበት ወቅት ነዉ።ኑሯችንም፣ሌሎች በርካታ ነገሮችም ይቀየራሉ።ሰዎችም ሱዳንን ያዉቋታል።»

የወደፊቷን ሱዳን ያዉ የካርቱሟ ወጣት እንዳለችዉ ወደፊት እናዉቃት ይሆናል።ከአስካሁኗ ሱዳን በጣሙን ከርዕሠ-ከተማ ካርቱም ረጅም ታሪክ ያለፉት ሶስት አራት ዓመታትን ሚስጥር በግርድፉ ስንቃኝ ምናልባት የሱዳንና የጎረቤቶችዋን ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ሴራን ይጠቁም ይሆናል።

መጋቢት 23፣ 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታስገነባዉ ግዙፍ ግድብ ሰበብ ከግብፅ ጋር የገጠመችዉን ዉዝግብ ለማስወገድ ይረዳል የተባለዉን ስምምነት የግብፅ፣የሱዳንና የኢትዮጵያ መሪዎች ፈረሙ።ሶስቱ መሪዎች ከስምምነቱ በኋላ እጆቻቸዉን አጨባብጠዉ ሽቅብ የዘረጉበት ፎቶ ግራፋቸዉ ዛሬም በየድረ-ገፁ (ምናልባትም በየአድናቂ አፍቃሪያቸዉ አልበም) እንደተለጠፈ ነዉ።

ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አልሲሲም የካይሮን ቤተ-መንግስት እንደተቆጣጠሩ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከፖለቲካዉ «ጡረታ» ወጥተዉ ቀሪ ሕይወታቸዉን እያጣጣሙ ነዉ።ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አል በሽር ግን ከሰላሳ ዘመን ሥልጣንናቸዉ ተወግደዉ ካርቱም ወሕኒ ቤት ናቸዉ።

ኢትዮጵያና ግብፅን ያቀራረቡት ሱዳኖች በጣሙን ደግሞ አልበሽር ነበሩ።ዘንድሮ በአራተኛ ዓመቱ አል በሽርን ባደባባይ ሰልፍ የተቃወሙትን ፖለቲከኞች እና አልበሽርን በጠመንጃ ከስልጣን ያስወገዱትን ጄኔራሎች ከሸመገሉት ግንባር ቀደሞቹ አዲሱ የኢትዮጵያ መሪ በጣሙን ዲፕሎማቶች ናቸዉ።ካርቱም የሚገኙት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ስለሸመገሉት ስምምነት እንዲነግሩን ከአርብ ጀምሮ በስልክ ስንጠይቃቸዉ ነበር።

Sudan: Proteste in Khartoum
ምስል Getty Images/A. Shazly

ጥንታዊ አዉሮጶች «ሮም ስትሆን እንደሮሞች ሁን» እንዲሚሉት ሆኖ-ነዉ መሰል፣ አዲስ አበቦች ካርቱም ሲሆኑ እንደካርቱሞች፤ ኢንሻአላሕ፣ ቡክራ፣ ማዐሌሽ ማለታቸዉ ይሁን-አይሁን በርግጥ አናዉቅም።የምናዉቀዉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ቆይ በኋላ እያሉን ሥራና ዉጤታቸዉን እነሆ ለዛሬ ሳይነግሩን መቅረታቸዉን ነዉ።

የኢትዮጵያ የዉጪ ግንኙነት የስልታዊ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ግን የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት ቅዳሜ የፈረሙት ስምምነት ለሱዳኖች ትልቅ ስኬት፣ ለኢትዮጵያና ለአፍሪቃ ሕብረት ደግሞ የከፍተኛ ጥረት ዉጤት  ነዉ።

እደገና ካርቱም።

ሰኔ 27፣2018። የደቡብ ሱዳን መንግስትና መንግሥትን የሚወጉት አማፂያን ተወካዮች አዲሲቱን ሐገር ያወደመዉን ጦርነት በ72 ሰዓታት ለማስቆም ተፈራረሙ።የስምምነቱን መፈረም ያበሰሩት ፕሬዝደንት ዑመር አል በሽር፣ የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴ ቬኒ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ሙሳ ፋኪ ነበሩ።

የአል በሽርን ስልጣን የወረሱት የጦር ጄኔራሎችና ጄኔራሎቹን የሚቃወሙት ፖለቲከኞች የቅዳሜዉን ዉል ሲፈራረሙ፤ፕሬዝደንት ሙሳ ቬኒ ካርቱም አልነበሩም። ሳል ቫኪር ግን ዋና ታዛቢ ነበሩ።ሙሳ ፋኪ ደግሞ የሸምጋዮቹ ዋና ተጠሪ።ቃል ገቡም።«ይሕንን ስምምነት ገቢራዊ ለማድረግ፣ በሕዝብ የሚመረጥ ሲቢላዊ ሥርዓት እንዲመሠረት፣ ነፃ፣ዴሞክራሲያዊና  ግልፅ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሚቆየዉ የሽግግር ጊዜ እንዲሳካ፣ የአፍሪቃ ሕብረት በሚችለዉ አቅም ሁሉ ለሱዳን የሚሰጠዉን ድጋፍ ይቀጥላል።»

ካርቱም።በተቃዉሞ ሰልፍ፣አድማ መሐል እንኳን የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተፋላሚ ኃይላትን አደራድራ-አስማምታች።የካቲት፣ 2019።ሚያዚያ ላይ የ30 ዘመን ገዢዋን አስወገደች።ከሚያዚያ ጀምሮ በአደባባይ ሰልፍ፣ ጩኸት፣ በግጭት ግድያ ስትታበጥ፣ በዜጎችዋ ደም፣ እንባ ስትጎድፍ ወራት አስቆጠረች።

በቅዳሜዉ ስምምነት ዜጎችዋን እያስቦረቀች፣ዛሬ የቀድሞ ገዢዋን ፍርድ ቤት ገትራ ዉላለች።ሰዉዬዉ በዘመነ ስልጣናቸዉ ከሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች 90 ሚሊዮን ዶላር «ስጦታ» መቀበላቸዉን አምነዋል ተብሏል።ግን አልተረጋገጠ።

የአልበሽር የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲሳካ፤ ብዙ ያጨፈረዉ የሽግግር ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ዝርዝርን ይፋ ማድረጉ አልሆነም።ለትናንት ነበር የተቀጠረዉ።አልደረሰም።ለዛሬ ተቀጠረ።ዛሬም አልሆነም።ለሌላ ጊዜ መለወጡን ማምሻዉን ተነገረ።ካቢኔዉም አልተመሰረተም።ወደፊት ለሚሆነዉ IBMን እያሰብን የሆነዉን ስንቃኝ፣ ኃምሌ ማብቂያ (ኦገስት 4)፣ በተፈረመዉ ስምምነት መሰረት የሽግግር ዘመኑ ለ39 ወራት ይቆያል።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ የሐገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን እሰወስት ይከፈላል።የሽግግር ምክር ቤት ወይም ፓርላማ።የሽግግር ወቅት አስተዳደር ወይም ላዕላይ ምክር ቤት እና ካቢኔ።

Sudan Khartum Machtabgabe Militär
ምስል Getty Images/AFP/A. Mustafa

አርባ ሚሊዮን የሚሆነዉ የሱዳን ሕዝብ የሚመራዉ አስራ-አንድ አባላት ባሉት «ሉዓላዊ» ምክር ቤት ነዉ።የምክር ቤቱ አባላት ከጦር ጄኔራሎችና ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚወከሉ ናቸዉ።ምክር ቤቱን ለሚቀጥሉት 21 ወራት የጦር ጄኔራል፣ ለቀሪዎቹ 18 ወራት ደግሞ የሲቢሎቹ ተወካይ ይመሩታል።

የተቃዋሚዎቹ ተወካይ መሐመድ ናጂ አል አሳም እንዳሉት አጠቃላይ ስምምነቱ ወራት ላስቆጠረዉ ሕዝባዊ አብዮት ድል።ለመላዉ ሱዳን ደስታ ነዉ።

«ለመላዉ የሱዳን ሕዝብ፣ እንቀራረብ፣ እስካሁን ብዙ በተሰቃየችዉ በተወዳጇ ሐገራችን ባንድነት እንኑር።የሱዳን አብዮት ድል በማድረጉ የምደሰትበት ጊዜ ነዉ።»

ሱዳንና ሕዝቧ በርግጥም በአምባገነን መሪዎች፣ በወታደራዊ ገዢዎች፣ በርበርስ ጦርነት፣ በዉጪ ኃይላት ጫና ለዘመናት  ተሰቃይተዋል።ለሁለት ተገምሰዋልም።የሱዳን ሕዝብ በሰላሳ ዘመን ገዢዉና ገዢዉን አስወግደዉ አዲስ ገዢ በሆኑበት ጄኔራሎች ላይ ያደረገዉ አመፅም ብዙ መስዋዕትነት አስከፍሎታል።

ከሚያዚያ ወዲሕ ብቻ 230 ያሕል ሱዳናዉያን ተገድለዋል።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።የጠፉ፣ የተደፈሩ፣የተፈናቀሉ፣የተዘረፉትን የቆጠራቸዉ የለም።ዓለም አቀፍና የአካባቢዉ ኃያላን መንግሥታት ለየራሳቸዉ ጥቅም ያደሩ ወገኖችን በመደገፍ ሱዳኖችን አጋድለዋል።የፖለቲካ ተንታኝ አበበ አይነቴ እንደሚሉት የሱዳኖች መስማማት የዉጪ ኃይላትን ጫና እና ጣልቃገብነትን ጭምር ያከሸፈ ነዉ።

ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ሳዑዲ አረቢያ ከግብፅ እስከ ብሪታንያ ያሉ መንግስታት ለስምምነቱ ገቢራዊነት ድጋፍ እንደሚሰጡ ቃል እየገቡ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን ጄኔራሎቹም የተቃዋሚዎቹ መሪዎችም ስልጣን ለመጋራት የተስማሙት ሌላ አማራጭ ስላጡ ነዉ።በተለይ በሕዝባዊዉ ተቃዉሞ ወቅት ሰልፈኞች አስገድለዋል የሚባሉት የጦር ጄኔራሎች ስልጣን እንደያዙ ይቀጥላሉ መባሉ ሽግግሩን ለጥርጣሬና ሥጋት አጋልጦታል።ትናንት ስምምነቱን በመደገፍ ካርቱም  አደባባይ የወጣዉ መሐመድ ዩሱፍ፣ እንደ ፖለቲካ አዋቂዎቹ ሁሉ «መጪዉን ጊዜ ደስታን ከስጋትና ሐዘን የቀየጠ» ይለዋል።

Sudan Khartum Ex-Präsident Umar al-Baschir vor Gericht
ምስል Getty Images/AFP/E. Hamid

«ዛሬ ደስታ ተሰምቶናል።ይሁንና አሁንም በቁጭታ አድማዉ ወቅት በተገደሉትና ያሉበት በማይታወቀዉ ወንድሞቻችን ምክንያት እንዳዘንን ነዉ።ለወደፊቱም ማሰባችን አይቀርም።ያም ሆኖ ለፈጣሪ ምስጋና ይግባዉና ፍላጎታችንን ተግባራዊ ለማድረግ የሲቢላዊዉ መንግስት ሥራ ይጀምራል የሚል ተስፋ አለን።ከዚሕ ደስታ ጋር ተወዳጆቻችን በመገደላቸዉ የሚሰማን ሐዘንም አብሮን ይኖራል»

የሽግግር ወቅቱ ርዕሠ-ብሔር ወይም ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ይፋ የሚሆኑበት ጊዜ ከትናንት ወደ ዛሬ፣ከዛሬ ደግሞ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ፣ በጄኔራሎቹና በሲቢል ፖለቲከኞች መካከል ያለዉ መጠራጠር ለመቀጠሉ  ማረጋገጪያ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት የሰፊይቱን ደሐ፣የየዋሆች ምድር ፖለቲካን እነ ሙሳ ፋኪ እንዳሉት ዴሞክራሲያዊ፣ነፃ፤ ግልፅና ከሁሉም በላይ ሰላማዊ ለማድረግ ካርቱሞች ጥንቃቄ፣ጥበብ፣ ትዕግስትን መላበስ ግድ አለባቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ