1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ቀውስ ተባብሷል

ቅዳሜ፣ ኅዳር 8 2016

ሱዳን ዛሬም የጠመንጃ አፈሙዝ ያጓራባታል ። ምንም እንኳን የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ቢገልጹም በተግባር ግን ባላንጣነታቸው ተባብሶ ቀጥሏል ። ከጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች የተቀጠፉበት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሰባት ወራት በኋላም መቋጫ የተገኘለት አይመስልም ።

https://p.dw.com/p/4Z4o9
የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም
የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል AFP

ሱዳን ከ9,000 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም

ሱዳን ዛሬም የጠመንጃ አፈሙዝ ያጓራባታል ። ምንም እንኳን የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ቢገልጹም በተግባር ግን ባላንጣነታቸው ተባብሶ ቀጥሏል ። ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች የተቀጠፉበት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሰባት ወራት በኋላም መቋጫ የተገኘለት አይመስልም ።

ሰባት ወራትን ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት መልኩን እየቀየረ ነው ። በተለይ በምዕራብ ዳርፉር ግዛት የቀጠለው ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ እና ስቅየት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን በእጅጉ አሳስቧል ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመርማሪዎች ቡድን ዐርብ እለት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ፦ በምዕራብ ዳርፉር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል።  ከእልቂቱ የተረፉ ሰዎችን ምስክር ያደረገው የተመድ መረጃ ያልታጠቁ የማሳሊት ጎሳ አባላት «ለስድስት ቀናት የዘለቀ ሽብር» ሰለባ መሆናቸውን ጠቁሟል ።

«አንዳንድ ሰለባዎች በጅምላ የተጨፈጨፉ አለያም ከእነ ሕይወታቸው የተቃጠሉ» እንደሚገኙበት ተመድ ከጄኔቫ ለጋዜጠኞች ገልጿል ። የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ከሰሞኑ ቢገልጹም ተግባሩ ላይ ግን የሉበትም ። ማርታ አማ አኪያ ፖቤ የተመድ ዋና ጸሐፊ የአፍሪቃ ረዳት ጸሐፊ ናቸው ። የሚባለው እና የሚሆነው ለየቅል መሆኑን ይናገራሉ።

«ሱዳን ውስጥ ግጭቱ የመብረድ አዝማሚያ ሳያሳይ ከሰባት ወራት በላይ ዘልቋል በተቃራኒው ባላንጣነቱ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እጅግ ተባብሷል ምንም እንኳን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ቢገልጹም፤ መሬት ላይ ያለው ድርጊታቸው የሚያሳየው ግን ሌላ ነው ።»

ለሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በዋናነት ተጠያቂዎቹ ሁለት ጄኔራሎች ናቸው ። በአንድ ወገን ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው «ሔሜድቲ» የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርን እየመሩ ግፋ በለው ይላሉ ። በሌላኛው ወገን ደግሞ ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ጦር ሠራዊትን ከፊት አስቀድመው ማን ሊረታን ሲሉ ይፎክራሉ ። በሁለቱ ጄኔራሎች መሪነት ሚያዝያ 7 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከመብረድ ይልቅ አሁን ጭራስ ተባብሶ ሱዳንን እያነደዳት ነው ።ማርታ አማ አኪያ ፖቤ ዳፋው በተለይ ሕጻናት እና ሴቶች ነው ይላሉ።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ወታደሮች
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ወታደሮች በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ከባድ ጦር መሣሪያ ጠምደው ምስል Hussein Malla/AP/picture alliance

«ሱዳን በከፋ ሁኔታ የተባባሰ የሰብአዊ ቀውስ እና እጅግ ያሽቆለቆለ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋርጦባታል ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ 6,000 በላይ ንጹሐን ዜጎች ካለፈው ሚያዝያ አንስቶ ተገድለዋል ሱዳን 7.1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቿ የዓለማችን ከፍተኛው የተፈናቃዮች ቀውስ የደረሰባት ሀገር ሆናለች የጤና ሁኔታውም እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ነው »

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት በሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ እስካሁን ከ9,000 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ።  ጦርነቱን ለማስቆም ሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ ውስጥ የተለያዩ ሃገራት ሰሞኑን መክረው ነበር ። ተፋላሚ ኃይላቱም የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር ። ኅብረተሰቡ በስፋት እስካልተሳተፈበት ድረስ የጄነራሎቹ መስማማት ግን ብቻውን መሬት ላይ የሚቀይረው ነገር የለም ።

የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደሮች
የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደሮች በዋና ከተማዪቱ ካርቱም ምስል AFP

«ምንም እንኳ የተኩስ አቁም የሚፈጸመው በተዋጊ አካላት ቢሆንም፤  የፖለቲካ ሒደቱ ዋነኛ አካላት የሆኑትን ሰላማዊ ዜጎች ሳያሳትፉ ግን ዘላቂ ሰላም ሊኖር አይችልም »

ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና ኖርዌይ በሱዳን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መባባስን ጠቅሰው ውግዘት አሰምተዋል ። በተለይ በዳርፉር ግዛት ኹከቱ እና ሰብአዊ መብት ጥሰቱ መበርታቱን ሦስቱ የምዕራባውያን መንግሥታት ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል ። ከውግዘት እና ከንፈር መጠጣው ባሻገር ግን በርካቶች እየረገፉ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ