1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ሰው ሰራሽ ማህፀን፤ የወደፊቱ ቴክኖሎጂ ኤክቶላይፍ፤የወደፊቱ የሥነ-ተዋልዶ ቴክኖሎጂ

ረቡዕ፣ ጥር 17 2015

ጀርመን በርሊን በቅርቡ ፅንስ ከሰውነት ውጭ እንዲያድግ እና እንዲወለድ የሚያስችል ሰው ሰራሽ ማህፀን በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ በአንድ የስነ-ህይወት ቴክኖሎጅ ባለሙያ ይፋ ተደረጓል።ይህ ቴከኖሎጀ ውጤታማ ከሆነ እና የህግ ድጋፍ ካገኘ በዓመት እስከ 30,000 ሕፃናትን ማሳደግ የሚችል በዓለም የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ ማህፀን ይሆናል ።

https://p.dw.com/p/4Mh2f
Mäuse Embrio
ምስል Gianluca Amadei, Charlotte Handford/AP Photo/picture alliance

ኤከቶላይፍ፤ የወደፊቱ የሥነተዋልዶ ቴክኖሎጅ

የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በቅርቡ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ይፋ በተደረገ እና በተለያዩ ምክንያቶች ፀንሰው መውለድ ለማይችሉ ሴቶች የአብራካቸውን ክፋይ ማግኜት እንዲችሉ ያደርጋል በተባለ ቴክኖሎጅ ላይ ያተኩራል።
ወልዳችሁ ሳሙ ዘርታችችሁ ቃሙ።በኢትዮጵያ ዘር የመተካት ፀጋን እንዲጎናፀፉ እና ዓይናቸውን በዓይናቸው እንዲያዩ  ለጥንዶች  የሚቸር  ምርቃት ነው።በቅርቡ ከወደ በርሊን የተሰማው የሥነ-ተዋልዶ ቴክኖሎጅ ዜና ግን ይህንን የሚለውጥ ይመስላል።መቀመጫውን ጀርመን በርሊን ባደረገው እና የስነ-ህይወት ቴክኖሎጅ /biotechnologist/ ፤ እና የሳይንስ ተግባቦት ባለሙያ በሆነው ሃሽም አልጋሃሊ በፅንሰ ሀሳብ  ደረጃ ይፋ የተደረገው ይህ ቴክኖሎጅ ኤክቶላይፍ /EctoLife/ በመባል የሚጠራ ነው።
ኤክቶላይፍ ፤ ያለ እርግዝና ከሰውነት ውጭ ፅንሱ እንዲያድግ እና እንዲወለድ የሚያስችል ሰው ሰራሽ ማህፀን ነው።  
የፅንሰ ሀሳቡ ባለቤት ሀሽም አልጋሃሊ ሚሊዮኖች በተመለከቱት ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ እንዳደረገው ይህ የሰው ልጆችን ማህፀን ተክቶ ይሰራል የተባለው መሳሪያ ከ50 አመታት በላይ በዘርፉ የተደረገውን ምርምር መሰረት በማድረግ የተሰራ ነው።
ለመሆኑ ፅንስን ከማህፀን ውጭ ማሳደግ ይቻላልን?በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የስነ-ተዋልዶ እና የመካንነት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቶማስ መኩሪያው።

«አሁን የታየውን ነገር ላይ ለመድርስ በጣም ይቀረናል።አስካሁን ባለው  ሳይንሱ የደረሰበት ፅንስን ከማህፀን ውጭ ማቆየት የተቻለው ለ14ቀናት በቻ ነው።ቪዲዮወ ላይ የታየውን አሁን ባለው ቴክኖሎጀ  ማድረግ አይቻልም።ለወደፊቱ ግን ስይንሱ እያደገ ሲሄድ በሚቀጥሉተት 20 እና 30 ዓመታት  ሊሳካ ይችላል።» በማለት  ዶክተር ቶማስ  ስኬቱን እስከ 30 ዓመታት ያደርሱታል።ምንም እንኳ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ የተሰራ ቢሆንም በሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሰው ሰራሽ ማህፀን በሚቀጥሉት አስር ዓመታት እውን ሊሆን ይችላል ።ሌላው በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን እንዲሁም  የመካንነት  ባለሙያ የሆኑት  ዶክተር አብዱ መንገሻ  በበኩላቸው ይፋ የተደረገው ሀሳብ እውን ለመሆን ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ አለበት ይላሉ።

Peter Gabriel in San Remo
ምስል AP

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የስነ-ተዋልዶ  ቴክኖሎጂ ከፊትለፊቱ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም፤  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትልቅ መሻሻል አሳይቷል። በጎርጎሪያኑ በ2017ም ፣ ሳይንቲስቶች ከማህፀን ውጭ የሆነ የህይወት ድጋፍ ስርዓት ወይም «ባዮባግ» በተባለ መሳሪያ የበግ ፅንስ ለማሳደግ ጥቅም ላይ ለማዋል ሞክረዋል። በዚህ የተነሳ በብሪታኒያ ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ የስነ-ተዋልዶ ሥነ ምግባር ባለሙያ የሆኑት ኤልዛቤት ክሎ ሮማኒስ በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ እንደፃፉት በሰው ሰራሽ ማህፀን የመጀመሪያውን የሰው ልጅ ማግኘት ከምናስበው በላይ ቅርብ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ዶክተር ቶማስ እንደሚሉትም ከጎርጎሪያኑ 1970 ጀምሮ  ልጅ ያለመውለድ ችግርን ለመፍታት እስከአሁን ድረስ ሳይንሱ በርካታ አማራጮችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጓል። የሳይንሱ የእድገት ግስጋሴ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ታዲያ ጊዜው ይርዘም ይጠር እንጅ ኤክቶላይፍ ተግባራዊ መሆኑ አይቀሬ ነው። 
በዚህ ሁኔታ ቴክኖሎጅው ውጤታማ  እና ደህንነቱ የተጠበቀ ከሆነ እንደ ባለሙያው በተለያዩ ችግሮች መውለድ ለማይችሉ ጥንዶች ዘራቸውን እንዲተኩ እና የአብራካቸውን ክፋይ እንዲገኙ ያስችላቸዋል። 

Bangladesch Baby aus eingefrorenem Embryo
ምስል Samir Kumar Dey

ከዚህ በተጨማሪ በካንሰር ወይም በሌሎች ችግሮች ምክንያት ማህፀናቸው በቀዶ ሕክምና ለተወገደባቸው ሴቶችም መፍትሄ ሊሰጥ ይችላል። እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ በአሁኑ ጊዜ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች በየዓመቱ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሴቶች ይሞታሉ።ከዚህ አኳያ ይህ ቴጅኖሎጅ በወሊድ እና ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ህመም እና ሞትን ያስቀራል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ቴክኖሎጅው በበቂ ሁኔታ ከዳበረ እና ጥቅም ላይ ከዋለ የከፋ የህዝብ ቁጥር መቀነስ ለሚታይባቸው እንደ ጃፓን፣ቡልጋሪያ እና ደቡብ ኮሪያን ለመሳሰሉ  ሀገራት ሊጠቅም ይችላል።
በሌላ በኩል  የሕዝብ ብዛት መቀነስ  በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ችግር ባለመሆኑ ከችግር ፈችነቱ አንፃር በቴክኖሎጅው ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።አንዳንዶችም ከህዝብ ብዛት መጨመር ጋር ያያይዙታል። ዶክተር ቶማስ ግን ይህንን አይቀበሉትም።
አዲሱ ጽንሰ ሃሳብ ኤክቶላይፍ ጽንሱ በእናቱ ሆድ የሚያገኘውን ሁሉ እንዲያገኝ ተደርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ የፅንሱን የሙቀት መጠን፣ የደም ግፊት እና የአተነፋፈስ ስርዓት ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔውን የሚቆጣጠሩ ሴንሰሮችም የተገጠመለት ነው።ወላጆች የሚወለደውን ልጃቸውን ባሉበት ሆነው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የተመሠረተ ክትትል ማድረግ እንዲሁም ለዚሁ ተብሎ በሚሰራ መተግበሪያ አማካኝነት የህጻናቱን እድገት በሞባይል ስልካቸው በቀጥታ መከታተል ይችላሉ። እንዲሁም  ለሚወዷቸው ሰዎች በቀጥታ ማጋራት ይችላሉ ተብሏል።ህጻናት ገና በማህፀን ውስጥ እያሉ ቋንቋን ማወቅ እና አዲስ ቃላትን መማር እንዲችሉም ፤በመተግበሪያው በኩል ለፅንሱ ሰፋ ያሉ ቃላትን እና የሚያዳምጠውን ሙዚቃ ዝርዝር መምረጥ ይችላሉ።ወላጆች በቀጥታ በመዘመር ከሚወለደው ልጃቸው ጋር  በድምጽ እንዲተዋወቁም ማድረግ ያስችላል ነው የተባለው። 

4D Aufnahme Fötus - Im Bauch der werdenden Mutter
ምስል FETAP/Cover Images/picture alliance

እንደ ሀሳብ አመንጭው ባለሙያ በአዲሱ ቴክኖሎጅ የእድገት ተፈጥሯዊ ሂደቶችን በመቆጣጠር  የሕፃኑን አንዳንድ የዘረ-መል ባህሪያት ማስተካከል እና በዘር  የሚተላለፍ በሽታን  ለመቀነስም ያገለግላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ወላጆች የልጆቻቸውን  የዓይን፣ የፀጉር እና የቆዳ ቀለም እንዲሁም ቁመት ፣ጥንካሬ እና  የማሰብ ችሎታ የመሳሰሉትን ባህሪያት እንዲመርጡ ያስችላቸዋል።ነገር ግን ቴክኖሎጅው  ከሀይማኖት፣ ከከባህል እና ከሥነ-ምግባር አኳያ ብዙ ፈተና ይገጥመዋል  ይላሉ። ዶክተር አብዱ መንገሻ።
ዶክተር ቶማስ በበኩላቸው ቴክኖሎጅው ለሚያስፈልጋቸው ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል በህግ እና በመመሪያ መመራት ይኖርበታል ይላሉ።ያ ሳይሆን ቀርቶ  የፈለገ ሁሉ  እንዲጠቀም ከተፈቀደ ግን ቴክኖሎጅው አደገኛ  ይሆናል ባይ ናቸው።
የወደፊቱ የሥነ-ተዋልዶ ቴክኖሎጂ ኤክቶላይፍ፤ ውጤታማ ከሆነ እና የህግ ድጋፍ ካገኘ በዓመት እስከ 30,000 ሕፃናትን ማሳደግ የሚችል የዓለም የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ ማህፀን ይሆናል።
መሳሪያውን በጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በቤታቸው ውስጥ በግል  መጠቀም ለሚፈልጉ  ወላጆችም አማራጭ እንደሚኖራቸው የሀሳቡ አመንጪ ይተነብያል።እንዲያ ከሆነ ምጡን እርሽው ልጁን አንሽው። ይቀር ይሆኝ? ጊዜ የሚመልሰው ጉዳይ ይሆናል።

ሙሉ ዘገጀቱን የድመፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ