1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሠዓሊ ለማ ጉያ ሲታወሱ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 19 2013

ሠዓሊ ለማ ጉያን የማዉቃቸዉ ልጅ ሆኜ በስዕል ማስተማርያ መጽሐፋቸዉ ነዉ። የሥዕል መማርያ መጽሐፋቸዉ በጊዜ የሥዕል መማርያ መጽሐፍ ባልነበረ ጊዜ የነበረ መጽሐፍ ነዉ። ጀማሪ ለሆኑ የስዕል ዝንባሌ ለሌላቸዉ፤ ወጣቶች ይጠቅማል ብለዉ ያሳተሙት መጽሐፍ ነበር። እኔም ስዕል አፍ አለዉ ካለዉ፤ አፌን የፈታሁት በለማ ጉያ የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3kbv5
Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

«ሥዕል አፍ ካለዉ፤ የሥዕል አፋችንን የፈታነዉ በለማ ጉያ መማርያ መጽሐፍ ነዉ»

«ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ፤ ለማ ጉያ ያሳተሙት መጽሐፍ ብቸናዉ የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ ነበር። እኔም  ስዕል አፍ ካለዉ የስዕል አፌን የፈታሁት በሳቸዉ መጽሐፍ ነዉ።»

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ ሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ፤ የክቡር ዶክተር ሠዓሊ ሻምበል ለማ ጉያን በማስታወስ ከተናጉርት የተወሰደ ነዉ። ቀለምን ከብሩሽ ብሎም ለየት ባለ መንገድ በፍየል ቆዳ ላይ ሲጠበቡ፤ በጥበብ ኖረዉ ዛሬ ቡሩሻቸዉን ለአዲሱ ትዉልድ አስቀምጠዉ አሸልበዋል! የሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ የጥበብ ሥራዎች አገር አገር ባህል ባህል የሸተቱ ብሎም የብዙሃንን ቀልብ የገዙ ጥበበኞችን  የወለዱ ናቸዉ ። ዛሬ አዛዉንቱ ሠዓሊ ለማ ጉያ የቀለም ቡሩሻቸዉን ብዙዎች ለሚወድዋቸዉ ተከታዮቻቸዉ አስቀምጠዉ አሸልበዋል። ሠዓሊ ለማ ጉያ ለጥበብ ያላቸዉ ፍቅር ጥልቅ መሆኑን በስዕሎቻቸዉ አንፀባርቀዋል ተናግረዋልም ፤ “ሰዓሊ ባልሆን ኖሮ የዛሬ 50 ዓመት ነበር የምሞተው" ብለዉ መናገራቸዉ ረጅም ለመኖራቸዉ ዋናዉ ምክንያት ስዕሎቻቸዉ የሚወዱትን ነገር መስራታቸዉ እንደሆን አሳይተዉበታል፤ አስተምረዉበታልም።  ከ10ሺህ የሚልቁ የቆዳ ላይ ድንቅ ስራዎች ባለቤት የሆኑት  ሰዓሊ ለማ ጉያ “ስዕልን ያለአስተማሪ” የተሰኘ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍን እንዳሳተሙ ይነገርላቸዋል።  ሙዚቃ ቋንቋ ነዉ እንደሚባለዉ ሁሉ ፤ ሰዓልያን በስዕሎቻቸዉ ስሜታቸዉን የሚገልፁበት ቋንቋቸዉ እንደሆን ይናገራሉ ። የሻምበል ለማ ጉያ ሃገራዊ ስዕሎችን ከሚያደንቁ ከአድናቂዎቻቸዉ መካከል የኢላይትመንት የስዕል አካዳሚ አንዱ መስራች እና የስዕል አስተማሪ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ  ይናገራሉ። ሰዓሊ ለማ ጉያ ይላሉ አቶ እሸቱ ፤ ለማ ጉያ ወደ ስዕሉ ዓለም ከመምጣታቸዉ በፊት በዉትድርናዉ ዓለም የነበሩ ፤ ይሁንና ተፈጥሮ በሰጣቸዉ ፀጋ የስዕል ዓለምን የተቀላቀሉ፤ ትልቅ አሻራን አስቀምጠዉ ያለፉ ይሏቸዋል።

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya
Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya
Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

« ሰዓሊ ለማ ጉያ ሰዓሊ ከመሆናቸዉ በፊት በኢትዮጵያ አየር ኃይል መኮንን የነበሩ፤ ሻምበልነት ማዕረግ ላይ የደረሱ ናቸዉ። ለማ ጉያ ተሰጦአቸዉ በስዕል ጥበብ ላይ ስለነበር የዉስጥዊ ስሜታቸዉን ታላቅ ፍቅር በመስማት ስዕልን በጣም በብዛት በመስራት ወደ ሰዓሊነት ዓለም ረጅም ጊዜ የገቡ ናቸዉ። እንደሚታየዉ ከስዕል አፍቃሪነታቸዉ የተነሳ ሁሉን ነገር ይሰራሉ። በተለይም ከኢትዮጵያ ነገስታት ጋር በተያዘዘ ፤ የቴዮድሮስ፤ የዮሃንስ ፤የሌሎችንም  ነገስታት ምስል ስለዋል። የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳትን በተለይም ከኦሮሞ ጋር በተያያዘ ያለዉን ልዩ ልዩ ባህልና አልባሳትን በስዕሎቻቸዉ ገልፀዋል።   በንጉሱ ዘነብ ባገኙት ትንሽ እዉቀት የመጀመርያዉን የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ የፃፉም ናቸዉ። ስዕል ራሳቸዉን ያስተማሩ ቤተሰቦቻቸዉ ልጆቻቸዉ ጥበብን እንዲጠበቡ ተጽኖ የፈጠሩ ናቸዉ።

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

ሻምበል ለማ ጉያ በቀድሞ አጠራሩ በየረርና ከረዩ ምስራቅ ሸዋ አድአ ሊበን ነሐሴ 12፤1921 ዓ.ም መወለዳቸዉ የታሪክ መዝገባቸዉ ያሳያል።  በልጅነታቸው ጦር አልሞ መወርወር  ቦክስና ዋና ይወዱም እንደነበር ስለ ሰዓሊዉ የወጡ ጽሑፎች ይጠቁማሉ።  ሻምበል ለማ ጉያ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን የተማሩት ቢሾፍቱ ነዉ። በመለጠቅ  በ1943 ዓ.ም  በአዳማ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ትምህርት ጀምረዉ፤ ልባቸው ወደጦር ሰራዊቱ ያደላ ስለነበር አየር ኃይል ገብተዉ፤ በአየር ኃይል የሜካኒክነት ሞያን ተምረው በአውሮፕላን ጥገና በመካኒክነት አገልግለዋል። ከዚህ ሞያ ትይይዩ ግን በእረፍት ጊዜያቸዉ ተፈጥሮ ባደላቸዉ ክህሎት ቡሩሽን ከቀለም በማገናኘት መጠበብ የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸዉ ነበር። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአለ ሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ፤ በልጅነታቸዉ መሳል የጀመሩት የሰዓሊ ለማ ጉያን የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ አንብበዉ እና ተምረዉ እንደሆነ ይናገራሉ።  

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

« እኔ ሰዓሊ ለማ ጉያን የማዉቃቸዉ መጀመርያ ልጅ ሆኜ በስዕል ማስተማርያ መልመጃ መጽሐፋቸዉ ነዉ። የስዕል መማርያ መጽሐፋቸዉ በጊዜዉ የስዕል መማርያ መጽሐፍ ባልነበረ ጊዜ የነበረ መጽሐፍ ነዉ። የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ አስፈላጊነት ገብቶአቸዉ ፤ ጀማሪ ለሆኑ የስዕል ዝንባሌ ላላቸዉ፤ ጀማሪ ወጣቶች ይጠቅማል ብለዉ የሰሩት መጽሐፍ ነበር። እስካሁንም ባለኝ መረጃ እንዲህ ያሉ የስዕል ማስተማርያ መጻሕፍት እሳቸዉ ባሳተሙባቸዉ ጊዜያት አልነበሩም። በዛ ጊዜ እኔ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ፤ ስዕል አፍ አለዉ ካለዉ፤ የስዕል አፌን የፈታሁት  ለማ ጉያ ባሳተሙት የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ ነዉ።»

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

እንደ ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ ሁሉ በርካታ ሰዓሊያን የስዕል አፍን የፈቱት በሰዓሊ ለማ ጉያ የስዕል ማስተማርያ መጽሐፍ ነዉ። ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የስዕል ክፍለ ጊዜን፤ የለማ ጉያን መጽሐፍ አንደ ዋንና ግብአት ይጠቀሙበት እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ። ሰዓሊ ለማ ጉያ በኢትዮጵያ በተለይ በቤተ እምነት ዘንድ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሚዘወተረዉን በቆዳ ላይ የመሳል ጥበብን ፤ እዉቀት ለማ ጉያ በራሳቸዉ ልዩ ጥበብ ለእይታ ያቀረቡ ሲሉ ሰዓሊ አገኘሁ አዳነ ይገልፁዋቸዋል።  

አቶ አገኘሁ እንደሚሉት ሰዓሊ ለማ ጉያ ስዕል ትምህርት ቤት ገብተዉ የተማሩ እንዳልሆን ይነገራል።  ይሁን  ሰዓሊ ለማ ጉያ በተፈጥሮ ያገኙትን ክህሎት በራሳቸዉ የጥበብ ቋንቋ ሲያዉጁ የነበሩ ፤ ከዘመናዊ የስዕል ዓለም ጋር የተዋሃዱም ነበር። 

ሻምበል ለማ ጉያ የደቡብ አፍሪቃዉን  የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ይወድዋቸዉ ያደንቋቸዉም ነበር። ሰዓሊ ለማ ጉያ የኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ የበርካታ ታዋቂ ሰዎችን ምስል ስለዋል። አንጋፋዉ ሰዓሊ ለማ ጉያ  በ1983 በደብረዘይት ማለት በቢሾፍቱ  ላይ የራሳቸውን ጉያ የሥነ- ጥበብ ስቱዲዮ ከፍተው ሲሰሩ ኖረዉ ፤ የጥበብ ስቱድዮዉ « አፍሪካ የጥበብና ስልጠና ሙዚየም ማእከል» መሰየሙ ማለትም ስሙ መቀየሩ ተመልክቶአል።    

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

ሰዓሊ ለማ ጉያ  በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማህበር ተሸላሚ ሆነዉ በሰሜን አሜሪካ ተጋብዘዉ በነበረ ጊዜ ኢትዮጵያዊው የህግ ባለሞያ ሼክስፒር ፈይሳ አግኝተዋቸዋል። የህግ ባለሞያ ሼክስፔር በወቅቱ የማኅበሩ ሊቀመንበር ነበሩ። ሼክስፒር እንደሚሉት አንጋፋዉ ሰዓሊ በእርጋታ የሚያወሩ ተግባቢ ሃገራቸዉን ወዳጅ ነበሩ። ስዕሎቻቸዉ የኢትዮጵያን ባህል በተለይ የገጠር ሴቶችን፤ ገበሪዎችን አኗኗር አለባበስ የሚያንፀባርቁ ናቸዉ ብለዋል።

Lemma Guya - Äthiopischer Maler verstorben
ምስል Tegen Adane/Lemma Guya

አርቲስት ለማ ጉያ በደቡብ አፍሪካው ኘሬዝዳንት ጀኮብ ዙማ በተደረገላቸዉ ጥሪ ለሦስት ጊዜ በገዥዉ ፓርቲ በኢኢንሲ ዓመታዊ ስብሰባ ተካፍለዋል። በ2ዐዐ7 ዓ.ም አርቲስት ለማ ጉያ ገመዲ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክር ቤት የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል። የሦስት ሴቶች ልጆች እና ሁለት ወንድ ልጆች አባት ለማ ጉያ  ባደረባቸዉ ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ሥነ-ስርዓታቸዉ ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ተፈፅሞአል። ዶቼ ቬለ በአንጋፋዉ ሰዓሊ በለማ ጉያ ሞት የተሰማዉን ሃዘን ይገልጻል። ነፍስ ይማር!

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ