1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞዛምቢክ የሰላም ድርድር

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 14 2008

በሞዛምቢክ በገዢው የፍሬሊሞ ፓርቲ እና በቀድሞው ያማፅያን ፓርቲ «ሬናሞ» መካከል ሀገሪቱን እንደገና ወደ የርስበርሱ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል በሚል ብዙዎችን ላሰጋው ውዝግብ መፍትሔ የሚያፈላልግ የሰላም ድርድር በመካሄድ ላይ ይገኛል። ሬናሞ የሰላም ውል እንደተደረሰ ቢያስታውቅም፣

https://p.dw.com/p/1JmD8
Afonso Dhlakama Filipe Nyusi Bildkombo Montage
ምስል picture-alliance/dpa/Pedro Sa Da Bendeira/Getty ImagesGianluigi Guercia/Montage

[No title]

ገዢው ፓርቲ ይህንን የተቃዋሚ ቡድን ፓርቲ አባባል ሀሰት ሲል አስተባብሎዋል። የሬናሞ ዋና ተደራዳሪ ኾዜ ማንቲየጋስ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ፓርቲያቸው እና ፍሬሊሞ የሚመራው የሀገሪቱ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሸምጋዮች ርዳታ በሰላሙ ውል ላይ የሚሰፍሩ አቅጣጫ ጠቋሚ ውሳኔዎች ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር። ማንትየጋ በዚያን ዕለት በሁሉም ተደራዳሪዎች ስም እንዳስረዱት፣ እነዚህ ውሳኔዎች በሞዛምቢክ ዘላቂ ሰላም ማውረድ ያስችላሉ። በሰላሙ ውል መሰረትም፣ የሀገሪቱ ምክር ቤት እስከ ቀጣዩ ህዳር ወር ድረስ በሞዛምቢክ ሕገ መንግሥት ላይ መደረግ አለባቸው የሚባሉ አስፈላጊ ለውጦች ሀሰቦችን በተጨባጭ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ሬናሞ እንደሚለው፣ የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ የሞዛምቢክ መንግሥት የሚከተለውን ማዕከላይ አመራር ወደ ፌዴራል ስርዓት መቀየር ይኖርበታል። በዚህም አማካኝነት፣ አስራ አንዱ የሀገሪቱ ግዛቶች የራሳቸውን ምክር ቤት እና መንግሥት ያቋቁማሉ። ሬናሞም እጎአ በ2014 ዓም ምርጫ አሸንፌአለሁ ላለባቸው ስድስት ግዛቶች የራሱን አስተዳዳሪዎች መሰየም ይችላል። እንደሚታወቀው፣ እስከዛሬ ድረስ በሞዛምቢክ የግዛት አስተዳዳሪዎችን የሚሾሙት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ናቸው።
Auto-Konvoi Mosambik
ምስል DW/B. Jequete
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያስረዱት፣ ፍሬሊሞ እና ሬናሞ በ1992 ዓም የሰላም ውል ከተፈራረሙበት ጊዜ አንስቶ የሬናሞ ታጋዮች አድልዎ እንደተደረገባቸው ነው የሚሰማቸው፣ ከዚህ ባለፈም፣ በምርጫ ወቅት ሆን ተብሎ ተካሂዶዋል በሚሉት የማጭበርበር ተግባር ሰለባ እንደሆኑ በቅሬታ ይናገራሉ። ይሁንና፣ ከ25 ዓመት በፊት የርስበርሱን ጦርነት ባበቃው የ1992 የሰላም ውል እንዲሟሉ የቀረቡት ሀሳቦች ፣ ለምሳሌ፣ የሬናሞን ታጋዮች ትጥቅ አስፈትቶ በሀገሪቱ ጦር፣ ፖሊስ እና የፀጥታ ኃይላት ውስጥ የማዋሀዱ ስራ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። ይህም አሁንም በድርድሩ ላይ ትልቅ እክል የደቀነ ጉዳይ እንደደቀነ ይገኛል። እጎአ ጥቅምት 2014 ዓም በተካሄደው በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ እንደገና በኅቡዕ መንቀሳቀስ ጀምረው የነበሩት የሬናሞ መሪ አፎንሶ ድላካማ፣ በስድስት የሀገሪቱ ግዛቶች አብላጫው የመራጭ ድምፅ በማግኘታቸው ራሳቸውን የነዚህ ግዛቶች መሪ ማለታቸው የሚታወስ ነው።
Flüchtlingslager in Kapise, Malawi
ምስል HRW
በሰላሙ ድርድር ላይ ኾዜ ማንቲየጋስ ውዝግቡ ሊያበቃ የሚችልበትን መንገድ የጠቆሙ ውሳኔዎች መደረሳቸው አበረታቺ መሆኑን ቢገልጹም፣ ገና መሰራት ያለበት ብዙ ስራ መኖሩን አልካዱም።
« ሬናሞ በስድስቱ የሀገሪቱ ግዛቶች አስተዳዳሪዎችን ይሰይሙ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ይህን እቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስቸለውን ሕጋዊ ዘዴ ባፋጣኝ ማግኘት ይኖርባቸዋል። »
እጎአ ጥቅምት 2014 ዓም በተካሄደው በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ እንደገና በኅቡዕ መንቀሳቀስ ጀምረው የነበሩት የሬናሞ መሪ አፎንሶ ድላካማ፣ በስድስት የሀገሪቱ ግዛቶች አብላጫውን የመራጭ ድምፅ በማግኘታቸው ራሳቸውን የነዚህ ግዛቶች መሪ ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይሁንና፣ ማንትየጋስ በፍሬሊሞ እና በሬናሞ መካከል ስር የሰደደውን ውዝግብ የሚያበቃው የሰላም ድርድር ውጤታማ ነው ባሉበት አነጋገራቸው ተፈንጥቆ የነበረው የተስፋ ጭላንጭል የሞዛምቢክ መንግሥት ዋነኛ ተደራዳሪ ኾዜ ቬሎዜ ወዲያውኑ ውል መደረሱን ባስተባበሉበት ጊዜ መና ቀርቶዋል።
የሞዛምቢክ መንግሥት እና ሬናሞ የሰላም ድርድራቸውን በቀድሞ የቦትስዋና ፕሬዚደንት ክዌት ማሪዜ፣ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ተወካዮች፣ የአውሮጳ ህብረት እና የጎረቤት ደቡብ አፍሪቃ ዲፕሎማቶች ሸምጋይነት እንደገና የጀመሩት እጎአ ነሀሴ፣ 2015 ዓም ነው። ድርድሩ ሞዛምቢክን ካለፉት አርባ ዓመታት በላይ ወዲህ በመምራት ላይ በሚገኘው የፍሬሊሞ ፓርቲ መሪ እና በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፊሊፔ ኒዩዚ እና እጎአ እስከ1992 ዓም ድረስ ከፍሬሊሞ ጋር የርስበርስ ጦርነት ባካሄደው እና እንደገና በ2015 ዓም ወደ ትጥቁ ትግል ባመራው በተቃዋሚው የሬናሞ ፓርቲ መሪ አፎንሶ ድላካማ መካከል አንድ ጉባዔ የሚደረግበትን መንገድ እንዲያመቻች የታሰበ ነበር። ይሁንና፣ በድርድሩ ወቅት የተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት መፍትሔ ይህን ዓላማ እና መፍትሔ የመሻቱን ጥረት አሰናክሎታል። በነዚህ ግጭቶች ሲቭሎች ተገድለዋል፣ የመንግሥት ሕንፃዎች እና ተሽከርካሪዎች በእሳት ጋይተዋል፣ ዋና መንገዶች ተዘግተዋል። በዛቫራ የሚገኘው የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ማርቼሊኖ ሙዬያ እንደታዘበው፣ የሞዛምቢክ ውዝግብ ሁሌ በፕሮፓጋንዳ የታጀበ ነው።
« ፖሊስ ግጭት በሚነሳበት ጊዜ ጥቃት የጣሉት የሬናሞ ደጋፊዎች እንደሆኑ ነው ሁሌ የሚነግሩን። ግን ከጥቃቱ በስተጀርባ የመንግሥት ጦር ኃይላት መሆናቸውን ከሕዝቡ የምንሰማው ። የየትኛው ወገን ቃል ትክክለኛ መሆኑን ማወቅ አዳጋች ነው። »
Mosambik Anschlag gegen Oppositionsführer Afonso Dhlakama
ምስል DW/A. Sebastião
የፖለቲካ ታዛቢዎች ሞዛምቢክ ተመልሳ ወደርስበርሱ ጦርነት እየገባች መሆንዋን አስታውቀው ይህ ለገጠሩ ሕዝብ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ግጭቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የሞዛምቢክ ዜጎች ወደ ጎረቤት ማላዊ ሸሽተዋል። መንግሥታ ያወጣቸው መዘርዝሮች እንደሚያሳዩትም፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያው በሞዛምቢክ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖራሉ። ግጭቱ በሀገሪቱ ኤኮኖሚም ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አልቀረም። ምክንያቱም በውጊያው ዋነኛ መተላለፊያ የሆኑ መንገዶች በመዘጋታቸው የሸቀጦች ዋጋ ንሮዋል። በሞዛምቢክ የአንድ የወጣቶች የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅት ባልደረባ ሳዉ ማዎ ሙቻንጎ ውዝግቡ ማብቃት አለበት ይላሉ።
« ግፊታችንን ማጠናከራችንን እንቀጥልበት። በሚቀጥለው ሳምንት ነሀሴ 27፣ 2016 ዓም በመዲናይቱ ማፑቶ ሰላም እንዲወርድ የሚጠይቅ ግዙፍ የአደባባይ ሰልፍ ይደረጋል። የሰልፉ ዓላማም ሰላም የጠማው የሞዛምቢክ ሕዝብ ለተቀናቃኞቹ ፓርቲዎች ጦርነት እንደማይፈልግ እና ውዝግብ እንደበቃው በግልፅ መልዕክት እንዲያስተላልፍ ለማድረግ ነው። »
ሲቭሉ ማህበረሰብ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ሀገሪቱን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ለማውጣት ሲቻል ባንድነት ስላጣኑን በመጋራት እንዲሰሩ ይፈልጋል። ይሁንና ፣ ይህ ሊሆን የሚችልበት ድርጊት ፣ የዶይቸቬለ ለአፍሪቃ የፖርቱጋል ክፍል ባልደረባ እንደምትለው፣ ከውጭ የሚገኝ ድጋፍ ወሳኝ ሊሆን ይችላል።
« ውዝግቡ የሚመለከታቸውን ተቀናቃኝ ወገኖች በማደራደር ላይ የሚገኘው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚያሳርፈው ግፊት ላይ ጥገኛ ይሆናል ብየ አስባለሁ። ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ስምምነት ለመድረስ በወቅቱ ከሁለቱም በኩል ፈቃደኝነቱ ተጓድሎ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም፣ የሰላሙ ድርድር ይሳካ ዘንድ ፣ ፖለቲከኞች፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከገመቱት በላይ፣ በሞዛምቢክ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ተፅዕኖው እየተጠናከረ የመጣው ሲቭል ማህበረሰብ በሚጫወተው በቀላሉ የማይገመት ሚናም ላይ ጥገኛ ይሆናል። »
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ