1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምያንማር የተቃርኖ ሕብር ሐገር

ሰኞ፣ መጋቢት 13 2013

የዓለምን የሠላም ኖቤል፣ የዩናይትድ ስቴትስን ምክር ቤት የሚሰጠዉን ከፍተኛ ሽልማት የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚዋ፣ የነጋንዲ ዉርስ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የዴሞክራሲ ጠበቃ የሚባሉት ፖለቲከኛ በሚሊዮን ከሚቆጠረዉ የሐገራቸዉ ዜጋ ደሕንነት ይልቅ፣ አሳሪ፣ አሳዳጅ፣ አጋች ጄኔራሎቻቸዉን መረጡ።

https://p.dw.com/p/3qyVD
Myanmar Naypyitaw Senior General Min Aung Hlaing und NLD Partei Anführer Aung San Suu Kyi
ምስል Soe Zeya Tun/REUTERS

የምያንማር ፖለቲካዊ ቀዉስ


የምያንማር ወታደራዊ ሁንታ ለረጅም ጊዜ ያሰራቸዉን ዕዉቅ ፖለቲከኛ ኦንግ ሳን ሱ ቹን ከለቀቀ በተለይም በ2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃ ምርጫ እንዲደረግ ከፈቀደ ወዲሕ ዓለም ያደነቀ-ያወደሰ የደገፈዉ ለዉጥ እንዳጀማመሩ መቀጠሉ ማጠያየቅ የጀመረዉ በሮሒጂያ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰዉ ግፍ ይፋ እንደወጣ ነበር።2016።እኚያ ከስር እንዲለቀቁ እስያ፣ አዉሮጳ አሜሪካ የታገለላቸዉ ሳን ሱ ቺ በሮሒንጂያዎች ላይ የደረሰዉን ግፍ መካዳቸዉ የመብት ተሟጋቾችን አስደንግጦ፣ አስገርሞ፣ አነጋግሮ ሳያበቃ ዘንድሮ የካቲት እሳቸዉ ወሕኒ፣የደቡብ ምስራቅ እስያዊቱ ሐገር ጅምር ዲሞክራሲም መቀመቅ ገባ።ምክንያት፣ ዉጤት እንድምታዉ ያፍታ ቅኝታችን ሰበብ ነዉ።
                   
ስልታዊ፣ ለም ግን ሞቃት፣የጦረኞች ግን የቡድሐ መንፈሳዉያን ሐገርም ናት።በርማ ወይም ምያንማር።የተቃርኖ ጥምረት ዉጤት።የዘመናዊቱ በርማ መስራች አባት ኦዉግ ሳን እንደ ሐገራቸዉ ሁሉ ተቃራኒ ሙያ-ስብዕናን ያጣመሩ ነበሩ።
ቆራጥ አዋጊ የጦር ጄኔራል ነበሩ።ጎበዝ ተደራዳሪ-ዲፕሎማት፣ ሕዝብ አስተባባሪ ፖለቲከኝም።በ1940ዎቹ ከብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ጋር አብረዉ ጃፓኖችን ወጉ፣ ደግሞ በተቃራኒዉ የሮሒንጂያ ሙስሊሞችን ጨምሮ ሕዝባቸዉን በብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ላይ አሳመፁ።እንደገና ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተደራደሩ ግን ነፃነቱ ሊታወጅ ወራት ሲቀሩት በተቀናቃኞቻቸዉ ተገደሉ።1947።
እሳቸዉም በርግጥ ያባታቸዉ ልጅ ናቸዉ።የአባታቸዉን፣ የአባታቸዉ እናት እና የእናታቸዉን ስም ቀይጠዉ መጠሪያቸዉ አደረጉት።ኦዉንግ ሳን ሱ ቺ ብለዉ።ነሐሴ 1988 የሐገሪቱን ወታደራዊ አገዛዝ በመቃወም የበርማን ሕዝብ ከጠረፍ-እስከ ጠረፍ ሲያነቃንቁት ሴትዮዋ ከጦር አዛዥነቱ በመለስ፣ ከስጋ ስም ወራሽነቱ ባሻገር በመንፈስ፣ በዓላማ ፅናት፣ በአስተባባሪነትን በርግጥ ያባታቸዉ ልጅ መሆናቸዉን አስመሰከሩ።

Myanmar | Proteste gegen Militärputsch
ምስል AP/picture alliance

                           
ሕዝባዊ አመፁ የተጀመረዉ በጎርጎሪያኑ 8ኛ ወር-ኦገስት፣ በ8ኛዉ ቀን፣ በ1988ኛዉ ዓመት በመሆኑ ታሪካዊ መጠሪያም አለዉ።አራት 8 ቶች-8888 የሚል።ወይዘሮ ሳን ሱ ቺ በእንግሊዛዊ ባለቤታቸዉ አደፋፋሪነት፣ የበርማ ብሔራዊ ሊግ ለዴሞክራሲ (NLD በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የተባለዉን የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረቱትም ያኔ ነበር።
ወታደራዊ አገዛዝን የሚቃወመዉን ፓርቲ የመሠረቱት ከዉትድርናዉ በጡረታ የተገለሉ ጄኔራሎችን አሰባስበዉ መሆኑ ሴትዮዋ ወታደርነቱ ቢያመልጣቸዉ ባባታቸዉ ግርፎች ለማካካስ መሞከራቸዉን መስካሪ ነዉ-ብለዉ ነበር ታዛቢ ነን ባዮች። 

በ1990 በተደረገዉ ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ በ59 ከመቶ ድምፅ አሸነፈ።ይሁንና ዲሞክራሲያዉ ሥርዓትን ብልጭ ሲል-ድርግም፣ ሲቢላዊ መሪን ብቅ ሲል-እንቅ የሚያደርጉት የጦር ጄኔራሎች ለሳን ሱ ቺና ለፓርቲያቸዉም ምሕረት አልነበራቸዉም።አገዷቸዉ።አሰሯቸዉም።
ከ1988 ጀምሮ ሳን ሱ ቺን እናዳበታቸዉ ፅኑ፣ እንደ ጋንዲ የሠላማዊ ትግል አራማጅ፣ የዴሞክራሲ ጠበቃ እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸዉ የምዕራቡ ዓለም ሙሉ ድጋፉን አልነፈጋቸዉም።በ1991 ታላቁን የሰላም ኖቤል ሸለሟቸዋልም።በ1999 የታተመዉ ታይም መፅሔት ከጋንዲ ልጆች አንዷ በማለት አወድሷቸዉም ነበር።ሴትዮዋ ግን እስከ 2010 ድረስ የቁም እስረኛ ነበሩ።
በ2015 በተደረገዉ ምርጫ NLD በሁለቱም የሐገሪቱ ምርክር ቤቶች አብላጫ መቀመጫ በማግኘቱ መንግስት መሠረተ።ይሁንና በምያንማር ሕግ መሰረት የዉጪ ዜጋ ያገባ የሐገሪቱን የመሪነት ስልጣን መያዝ ስለማይችል ሳን ሱ ቺ የመንግስት አማካሪ የተባለዉን የጠቅላይ ሚንስትርነትና  የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ደርበዉ ይዘዉ መንግስቱን ከጀርባ ይመሩ ያዙ።
ከ1970ዎቹ ጀምሮ አርካይን ወይም አርካን በተባለዉ ግዛት የሚኖሩ የሮሒንጂያ ሙስሊሞችን የዜግነት መብት የገፈፉት የምያንማር ጄኔራሎች ሮሒንጂያዎችን መግደል፣ የተረፉትን ማባረር፣ ሴቶቹን መድፈር፣ ሐብት ንብረታቸዉን ማዉደሙን ያጠናከሩት ሳን ሱ ቺ ስልጣን በያዙ ባመቱ ነበር።2016።በወራት ዕድሜ ብዙ መቶዎች ተገደሉ፣ ተደፈሩ፣ 800 ሺሕ ያሕል ሕዝብ ተሰደደ።ርምጃዉን በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት ወንጀል በማለት አዉግዘዉታል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ ባንግላዴሽና ማሌዢያ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ብለዉታል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ በማስተማሪያ መፅሐፍት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል የዘር ማፅዳት (ወንጀል) አለዉ።
ይሁንና ወንጀለኞች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ አቤቱታ ያቀረበዉ ልዕለ ኃያሊቱ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጠንካራዎቹ አዉሮጳች፣ ቻይኖች፣ ሩሲያዎችም አልነበሩም።ራሳቸዉን የሙስሊሞች ተጠሪ የሚሉት ሐብታሞቹ የአረብ ገዢዎችም ስለ እልቂቱ መስማታቸዉ ጭራሽ አጠራጣሪ ነዉ።ትንሺቱ፣ሙስሊማይቱ፣ አፍሪቃዊቱ ጋምቢያ እንጂ።
ታሕሳስ 2019 ዘ ሔግ ኔዘርላንድስ ላስቻለዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ወይዘሮ ኦዉንግ ሳን ሱ ቺ መለሱ ጋሚቢያን እየወቀሱ።«በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ጋምቢያ በርካይን ግዛት፣ ምያንማር ዉስጥ ስላለዉ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበችዉ መረጃ ያልተሟላና የተሳሰተ ምስል የሚፈጥር ነዉ።ፍርድ ቤቱ ርካይን ግዛት ዉስጥ ያለዉን ተጨባጭ እዉነታ በትክክልና ባልተዛበ መንገድ መገንዘብ አለበት።የርካይን ሁኔታ በጣም የተወሳሰበና በቀላሉ መረዳት አስቸጋሪ ነዉ።» 
የዓለምን የሠላም ኖቤል፣ የዩናይትድ ስቴትስን ምክር ቤት የሚሰጠዉን ከፍተኛ ሽልማት የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚዋ፣ የነጋንዲ ዉርስ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የዴሞክራሲ ጠበቃ የሚባሉት ፖለቲከኛ በሚሊዮን ከሚቆጠረዉ የሐገራቸዉ ዜጋ ደሕንነት ይልቅ፣ አሳሪ፣ አሳዳጅ፣ አጋች ጄኔራሎቻቸዉን መረጡ።
በሮሒንጂያ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመዉ በደል በጭራሽ የዘር ማጥፋት አይደለም አሉ።ጠየቁም ጥፋቶችን እየቀጣን እንዴት እንከሰሳለን?
«ያጠፉ ወታደሮችንና መኮንኖችን የሚመረምር፣ የሚከስና የሚቀጣ መንግስት እንዴት ዘር-የማጥፋት ዓላማ አለዉ ሊባል ይችላል።» 
ወይዘሮ ሳን ሱ ቺ ክሕደት ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አስደንጋጭ፣አስተዛዛቢ፣ አነጋገሪም ነበር።የ2008ቱን ኖቤል የሰላም ሽልማትን የተሸለሙት ባንግላዴሺያዊዉ የድሆች ተቆርቋሪ መሐመድ ዩኑስ በሳን ሱ ቺ ክሕደት ከደነገጡ፣ ከተናደዱትም አንዱ ናቸዉ።
                               
«እዚያ የተፈፀመዉ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝ ነገር ነዉ።ስሜቱን በየቀኑ እረዳዋለሁ።እኔ የሮሒንጂያ ስደተኞች የሰፈሩበት አካባቢ ተወላጅ ነኝ።እሳቸዉ ይሕን የኖቤል ሽልማት ሲያገኙ ዓለም አድናቆትና ድጋፉን ሲያዘንብላቸዉ ነበር።አሁን ግን ፍፁም ተቃራኒ አቋም ይዘዋል።ሌላ ገፅታ አላቸዉ።የገዛ ዜጋቸዉን የመግደልና የማሰቃየት ፊት።»
ሳን ሱ ቺ የሐገራቸዉ ጦር ያደረሰዉን ግፍ የካዱት፣ የማያንማርን ተዘዋዋሪ የመሪነት ሥልጣን  ቢይዙም የሐገሪቱ የጦር ጄኔራሎችን የመቆጣጠር ስልጣን ስለሌላቸዉ ነዉ በማለት የሚከራከሩ አሉ።በርግጥም የምያንማር የጦር ጄኔራሎች የጦርና ፀጥታ የማስከበሩን ስልጣን እንደተቆጣጠሩት ነበር። 
ዶክተር መሐመድ ዮንስ ግን  መልስ አላቸዉ።ግድያ፣ ግፍ፣ ወንጀሉን ባደባባይ ማዉገዝ አያቅታቸዉም የሚል።ካቃታቸዉ ደግሞ ታዲያ ምን ይሰራሉ?
                                       
«ሁሉንም ነገር፣ የተፈፀ ወንጀል የለም፣ መንደሮች አልተቃጠሉም ሁሉንም የዉሸት መግለጫ ሰጥተዋል።ጦሩ አላሰራ አለኝ ማለት ይችሉ ነበር።ይሁንና ጥፋቱን በሙሉ እራሳቸዉ በራሳቸዉ ተቀብለዉታል።በወታደሩ ወይም በሌላ ወገን ላይ ማላከክ አይችሉም።ሁሉንም ጥፋት ተቀብለዋል።ማስተካከል ያለባቸዉም ራሳቸዉ ናቸዉ።»
ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች የተስማሙበት የወይዘሮ ሳን ሱ ቺ የክሕደት ስሌት አብዛኛዉን የምያንማር የቡድሐ ማሕበረሰብ ላለማስቀየም፣ ባመቱ ሕዳር በሚደረገዉ ምርጫ ከፍ ያለ ድምፅ ለማግኘት፣ ከሁሉም በላይ የጦር ኃይሉን ቁጣና ግልምጫ ለማለዘብ ነዉ-የሚለዉ ትንታኔ ነዉ።ዕቅድ ስልታቸዉ በርግጥ ያዘ።ሕዳር 2020 በተደረገዉ ምርጫ ፓርቲያቸዉ በከፍተኛ ድምፅ አሸነፈ።ግን ለወራት።
ከ1949 ጀምሮ እስከ 2011 ከጄኔራል ኔ ዊ እስከ ጄኔራል ማዉንግ ኢዬ የተፈራረቁት የምያንማር የጦር አዛዦች ሲሻቸዉ ራሳቸዉ በቀጥታ፣ ሲላቸዉ አሸንጉሊት ሲቢል መሪ እየሾሙ የቀድሞዋ በርማ-የኃላዋን ምያንማርን ሁለንተናዊ ጉዞ ዘዉረዋል።ጄኔራሎቹ የፖለቲካ ስልጣኑን ሲይዙ፣ ከጦር መሳሪያ ሽያጭና ግዢ እስከ ማዕድን ኢንዱስትሪ፣ ከእርሻ ምርት እስከ አሳና ደን ያለዉን ሐብት ይቆጣጠራሉ።
ሚያዚያ 2011 የጦር መሪነቱን ስልጣን የያዙት ጄኔራል ሶ ዊን -የምዕራባዉያን ማዕቀብ ቢያይልባቸዉ ሳን ሱ ቺን ለቀዉ ግን ሐብት ዉሳኔዉን እንደያዙ ለመቀጠል ነበር-ሥልታቸዉ።በሕዳሩ ምርጫ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ ሕገ-መንግሥት መቀየር የሚያስችል ድምፅ ማግኘቱን ሲረዱ ግን አዲስ የተመረጠዉ መንግስት እስኪመሰረት ሲያደቡ ቆዩ።
የካቲት 1።መንግስት ተመሰረተ።ጄኔራል ሶ ዊንም ጦራቸዉን «ቀጥል» አሉት።ታሕሳስ 2019 በዓለም ሕዝብ ፊት የተከራከሩ፣ የተሟገቱ፣ ከሕዝባቸዉ ያስበለጧቸዉን ሳን ሱ ቺን ጨምሮ የፓርቲያቸዉን ከፍተኛ መሪዎች፣ የምክር ቤት እንደራሴዎችን ለቃቅመዉ ገሚሱን በቁም ሌላዉን በየወሕኒ ቤቱ አጎሯቸዉ።
ምያንማር። ሌላ ስም፣ ሌላ ምርጫ፣ ሌላ ዓመት፣ ሌላ ጄኔራል ግን ያዉ መፈንቅለ መንግስት።የተሰጠዉ ምክንያት  የሳ ሱ ቺ ፓርቲ የምርጫዉን ሒደትና ዉጤት አጭበርብሯል የሚል ነዉ።የተለመደዉ መፈንቅለ መንግስት፣ የተለመደዉ ተቃዉሞ ሰልፍ፣ ግጭትና ግድያ አልተለየዉም።
 የምያንማር ፀጥታ አስከባሪዎች እስካሁን 200 ተቃዉሞ ሰልፈኛ ገድለዋል።የቆሰለዉን በቅጡ የቆጠረዉ የለም።ከአንድ ሺሕ በላይ አስረዋል።ዓለም አቀፍ የሚባለዉ ማሕበረሰብ በጣሙን ምዕራቡ ዓለም የመፍንቅለ መንግስት መሪዎቹን ማዉገዝ፣ ማስጠንቀቅ፣ በማዕቀብ መቅጣቱን ቀጥሏል።የመጨረሻዉ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዛሬ የጣሉት ማዕቀብ ነዉ።
የሕብረቱ ዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦርየል እንዳሉት ሕብረታቸዉ 11 የምያንማር ወታደራዊ ሁንታ መሪዎችንና ተባባሪዎቻቸዉን በማዕቀብ ቀጥቷል።
                                  
«ምያንማርን በተመለከተ መፍንቀለ መንግሥቱን የመሩ፣ ያቀነባበሩና ተቃዉሞ ሰልፈኞችን ያስገደሉ 11 ሰዎች በማዕቀብ እንቀጣለን።»
የምያንማር የጦር ጄኔራሎች ወዳጅ የምትባለዉ ቻይና ሳትቀር በተለይ የተቃዉሞ ሰልፈኞች መገደል፣መቁሰላቸዉን ተቃዉማለች።ሰሞኑን ከዩናይትድ ስቴትስ አቻዎቻቸዉ ጋር የተነጋገሩት የቤጂግ  ባለስልጣናት የምያንማርን ፖለቲካዊ ቀዉስ ለማስወገድ ከዋሽግተኖች ጋር በጋራ ለመጣር ቃል ገብተዋልም።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሕንድ፣ ጃፓንና አዉትሬሊንያን የሚያስተናብረዉ አዲስ ቡድንም አዲስ ጥረት መጀመሩን አስታዉቋል።ምያንማርን በአባልነት የሚያስተናብረዉ የደቡባዊ ምሥራቅ እስያ ሐገራት ማሕበር (አዝያንም) አሳሪ-ታሳሪዎችን ለማደራደር  አንድ ሁለት እያለ ነዉ።ዉግዘት፣ ቅጣት፣ የማደራደር ሙከራ፣ ጥረቱ፣ በሙሉ  እስከ 2010 ከነበረዉ የተለየ አይደለም።የተቃራኒ ቅይጧን ሐገር የተቃርኖ ታሪክ ለመለወጥ መፈይዱም አይታወቅም።

Myanmar Demonstration gegen den Militärputsch in Yangon
ምስል STR/AFP
06 Weltspiegel | Myanmar | 22.03.2021
ምስል Uncredited/AP/picture alliance
05 Weltspiegel | Myanmar | 22.03.2021
ምስል Stringer/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ