1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫን የምታልመዉ ሶማሌላንድ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8 2015

በሶማሌላንድ በእዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄድ ነበረባት። መስከረም ወር ላይ ግን ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለዉ የሽማግሌዎች ምክር ቤት፣ የፕሬዝዳንት ሙዝ ቢሂ አብዲን የስልጣን ዘመን ለሁለት ዓመታት አራዝሟል። በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይሁንና ስለመካሄድ አለመካሄዱ ገና በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

https://p.dw.com/p/4L5u9
Somaliland Hauptstadt Hargeisa
ምስል Katrin Gänsler/DW

ሶማሌላንድ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ነጻነቷን ያወጀች ቢሆንም እውቅናን ያገኘች ሀገር አይደለችም

ሶማሌላንድ ህዳር ወር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። በሶማሌላንድ የምርጫ ጊዜን ማራዘም እንደ ልማድ ተደርጎ የሚታይ ሆንዋል። ይሁንና በሃገሪቱ በቀጠለዉ ቀዉስ ምክንያት የማራዘሙ ዉሳኔ ተቀባይነት አላገኘም። ጊዜዉ ከቀትር በኃላ፤ ቦታዉ የሶማሊላንድ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው በቡራኦ ዉስጥ ነው። በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ መስጊዶች ምዕመናን ለፀሎት ሲጠሩ ይሰማል። አብዲራክሲም ያማ ያሲን ግን ከሱቁ ፊት ለፊት ተክዞ ተቀምጧል። የ38 ዓመቱ ጎልማሳ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ነጋዴ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምንም ዓይነት ገበያ አልነበረዉም።

Somaliland Abdiraxiim Yama Yasin will Somaliland verlassen, falls nicht zügig gewählt wird
አብዲራክሲም ያማ ያሲን-የ38 ዓመቱ ጎልማሳ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ነጋዴምስል Katrin Gänsler/DW

«ለመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን እሸጣለሁ ። ከሦስት ዓመታት ጀምሮ ንግዱ ሞቷል ። እቃ ለመግዛት ወደ ሱቅ የሚመጣ ሰው ስለሌለ አብዛኛውን ጊዜ ሱቄን ሙሉ በሙሉ እዘጋነበር ነበር።  የመለዋወጫ እቃዎችን በ45 የአሜሪካ ዶላር የሸጥኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ ። ዛሬ ይህ የመለዋወጫ እቃ 65,000 የሶማሌላንድ ሺሊንግ ያወጣል። ይህ በዶላር ሲሰላ አስር የአሜሪካ ዶላር እንኳ አይሞላም።»

ይላል አብዲራክሲም። በአፍሪቃ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ በሶማሌላንድ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ)ባወጣው ግምት መሰረት በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በኬንያ ከ36 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የአስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል። በሰሜን ሶማሌ ክልል የምትገኘዉ ሶማሌላንድ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ነጻነቷን ያወጀች ቢሆንም እውቅናን ያገኘች ሀገር አይደለችም። ሶማሌላንድ  ከዚህ ቀደም ድርቅ ካስከተለባት ከፍተኛ ጉዳት ሙሉ በሙሉ ገና አላገገመችም። ከዚህ ሌላ በሶማሌላንድ የሚታየዉ ፖለቲካዊ ለውጦች ሁኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪ እያደርጉት ነዉ። 

በሶማሌላንድ በእዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄድ ነበረባት። መስከረም ወር ላይ ግን ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለዉ የሽማግሌዎች ምክር ቤት፣ የፕሬዝዳንት ሙዝ ቢሂ አብዲን የስልጣን ዘመን ለሁለት ዓመታት አራዝሟል። በሶማሌላንድ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይሁንና አሁንም ስለመካሄድ አለመካሄዱ ገና በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። የሶማሌላንድ የገንዘብ ሚንስትር ሰአድ አሊ ሺርን ነገሩ እንብዛም አላሳሰባቸዉም። 

«በስልጣን ለመቆየት ጊዜ የማራዘም ልማድ አለብን። ይህ አሁኑ ብቻ ሳይሆን የነበረ ልማድ ነዉ። ከዚህ በፊት ሁለቱም የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት እያንዳንዳቸው የስልጣን ጊዜያቸዉ ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል።  እናም ይህ ስልጣን ማራዘም ልማዳችን ሆኗል።»

ተቃዋሚዎች በሶማሌላንድ የሽማግሌዎች ምክር ቤት ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑን ይነቅፋሉ። መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። አብዲራህማን ሞሃመድ አብዱላሂ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ «ዋዳኒ» እጩ መሪ ናቸዉ። የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ በሶማሌላንድ ስልጣን በዘመድ መሆኑን ይናገራሉ።

Somaliland Saad Ali Shire Finanzminister
የሶማሌላንድ የገንዘብ ሚንስትር ሰአድ አሊ ሺርንምስል Katrin Gänsler/DW

«የሶማሌላንድ ላዕላይ ምክር ቤት ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ተመርጦ አያውቅም። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ሰዎች በባሕላዊ እውቀታቸዉ የተከበሩ ሽማግሌዎችና ጠቢባን ነበሩ ። ልጆቻቸው መመዘኛውን ባያሟሉም እንኳ አሁን ስልጣኑን ተቆጣጥረዉታል።»

የሶማሌላንድ ህገ መንግስት በአይነቱ ልዩ፤ በሁኔታው ይበልጥ የተወሳሰበ መሆኑ ይነገራል። ምንም እንኳ የሶማሌላንድ መንግሥት፣ የራሱ ፓስፖርትና የራሱ የመገበያያ ገንዘብ ቢኖረዉም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እዉቅናን ያገኘዉ በታይዋን ብቻ ነው። ሶማሌላንድ የአፍሪቃ ህብረት እዉቅናን አግኝታ የህብረቱ አባል ለመሆን ለአስርት ዓመታት ስትታገል ቆይታለች። ይህ አንድ ቀን ቢሳካ ግን ሶማሌላንድ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር የማግኘት መብትን ታገኛለች። በአሁኑ ወቅት የሶማሌላንድ ኢኮኖሚ የሚደገፈዉ እና የተመካው፤ በዉጪ ከሚኖረዉ ዜጋ ከዳያስፖራውና ከከብት ኢንዱስትሪ በሚገኘዉ ገቢ ላይ ነው። ባለሃብቶች በሃገሪቱ መዋለንዋይ እንዳያፈሱ በሃገሪቱ በየቦታዉ የሚታየዉ ግጭት አግደዋቸዋል፤ ሲሉ የሶማሌላንድ የንግድ ሚንስትር ሳድ አሊ ሽሬ ይናገራሉ።

«ግጭትና ዉዝግቦች ምንጊዜም ቢሆን ልማት ላይ መዋለንዋይ እንእንዳይፈስ ያግዳሉ። በተለይ ሁኔታዉን በአይናቸዉ ያላዩ ዉጭ የሚኖሩ ዜጎቻችን ስለ ደህንነት ሁኔታዉ ያላቸዉ አመለካከት የተለየ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰው በልማት ላይ ገንዘባቸዉን እንዳያዉሉ አያበረታታቸውም። ሁኔታዉ የዚህን ሃገር ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የዉጭ ሃገር ባለሃብቶችም ጭምር እንዲመጡ የሚጋብዝ አይደለም።»

ሶማሌላንድ ከሶማሊያ በተለየ መልኩ ደህንነቷ የተጠበቀና ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲያዊ መሆንዋን አጽንኦት ትሰጣለች። ይሁን እና በሃገሪቱ የሰዎች መሠረታዊ መብቶች መገደባቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ በመሆኑ ነቀፊታ አስከትሏል። ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ተከትሎ ነሐሴ ወር ዉስጥ በተጠራ የተቃወሞ ሰልፍ አምስት ሰልፎች ህይወታቸዉን አጥተዋል። የሶማሌላንድ የሰብአዊ መብት ማዕከል (HRC) ፕሮግራም አስተባባሪ ካዲጃ ሙሳ እንደሚሉት ሰዎች ያልምንም ምክንያት ይታሰራሉ።

Somaliland Viehwirtschaft
ሶማሌላንድ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ነጻነቷን አወጀችምስል Katrin Gänsler/DW

«ባለፉት ሁለት ዓመታት በፖለቲካዉ ሁኔታ ምክንያት በግብታዊነት የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ለምሳሌ ምንም ምክንያት ወይም ማስረጃ ሳይኖር ጋዜጠኞች ይታሰራሉ።»

ካዲጃ ሙሳ  ከጎርጎረሳዉያኑ 2021 ዓ.ም ምርጫ ወዲህ አንድም ሴት ያልገባበት የሶማሌላንድ ፓርላማን ይነቅፋሉ። በቡራኦ የመኪና መለዋወጫ ዕቃ ነጋዴዉ አብዲራክሲም ያማ ያሲን ዛሬ ከቀትር በኋላ አንድም ነገር አልሸጠም። አብዲራክሲም ያማ ያሲን  በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ እንዲሻሻል በተቻለ ፍጥነት ምርጫ ይካሄዳል ብሎ ተስፋም ያደርጋል።

«ምርጫዉ ይካሄዳል ብዬ በጣም ተስፋ አደርጋለሁ። ምርጫ ከሌለ ከእንግዲህ እዚህ መቆየት አልፈልግም፤ ከዚህም ለቅቄ እወጣለሁ።»

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ