1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ቀን ወደፊት ይገለጣል

ረቡዕ፣ ጥር 13 2012

ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10ን ጊያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበር።

https://p.dw.com/p/3Weza
Äthiopien Wahlen 2015
ምስል DW/E. Bekele

«ጊዚያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም»

ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10ን ጊያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበር። የቦርዱ ቃል አቀባይ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ እንዳስታወቁት ግን የመጨረሻዉ የምርጫ ቀን ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና «የሕብረሰብ ክፍል» ካሏቸዉ ወገኖች ጋር ቦርዱ ከተወያየ በኋላ ይወሰናል። ቦርዱ ያስወመጠዉ ጊዚያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሳይጀመር የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በመመርመር ላይ እንደኾነም የቦርዱ ቃል አቃባይ ሶሊያና ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የዘንድሮዉ ምርጫና ዝግጅቱ የሚደግበት ጊዚያዊ የጊዜ ሰለዴ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።።በጊዜ ሰሌዳዉ መሠረት ካለዉ ታሕሳስ 22 ጀምሮ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን እያደራጀ ነዉ። የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜን ነሐሴ 20/2012 ለማድረግ ጊዚያዊ ቀጠሮ መያዙንም ነው ይፋ የተደረገው የጊዜ ሰሌዳ የሚያለክተው።

የምርጫ ቦርዱ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳን ሕጋዊ እና ትክክለኛ በማለት ስምምነታቸውን የገለጹ የመኖራቸውን ያህል ምርጫዉ በከባዱ የክረምት ወቅት ይደረጋል መባሉ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና የወንዞች ሙላት ምርጫው ያለ ችግር ስለመከናወኑ ጥርጣሬ የገባቸው እንዳሉም ታይቷል።

የምርጫ ቦርድ በበኩሉ የመጨረሻ በሚለው የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ቀደም ሲል ለመነሻነት ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየት እያሰባሰበበት ስለመሆኑም ነው የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት ።

በኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ ሀገራዊ ምርጫ መካሔድ እንዳለበት በህገ መንግሥቱ ተደንግጓል። በዚሁ በስራ ላይ ያለው ህገ- መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ለስድስተኛ ጊዜ ሊካሄድ በጊዜያዊነት የተያዘለት ቀነ-ቀጠሮ ውዝግብ ማስነሳቱ ከህግ አንጻር እንዴት ይታይ ይሆን።

Nationales Wahlgremium Äthiopiens
ምስል DW/S. Muchie

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ እንደሚሉት የምርጫ ቦርዱ በህግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ ከአሰራሩ ጋር በሚያመቸው መልኩ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ይችላል በማለት ይናገራሉ ። ቦርዱ ህግን የሚተላለፍ ተግባር እስካልፈጸመ ድረስ በየትኛውም የአየር ጠባይ ውስጥ ቀጠሮውን የመያዝ ስልጣን ቢኖረውም ሁሉን ሊያስማማ ወደ ሚችል የውይይት መድረክ ቢያመራ የተሻለ ውጤት ሊገንበት እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በጊዜያዊነት ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ተግባራዊ መደረግ ባልጀመረበት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረጉ መኾናቸው ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም የሚል ወቀሳ እና ትችት ሲሰነዘር ይሰማል።

የምርጫ ቦርድ ቃል አቃባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ እንደሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰጣቸው ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ መንገድ ወጥተው በሚገኙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቅድሚያ ተፈጸሙ የተባሉ የህግ ጥሰቶች መመርመር አለበት ይላሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተዘጋጀላቸው የህግ ማዕቀፍ ወጥተው ሲገኙ ይኽንኑ ለማስተዳደር በወጣው ህግ ሊዳኙ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ደግሞ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ናቸው። ከሰሞኑ ጀምሮ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጌቸው ጊዜያቸውን ያልጠበቁ የምርጫ ቅስቀሳዎች ወይም የቅስቀሳ ይዘት ያላቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ሕጋዊ መንገድን ሊከተሉ እንደሚገባም ነው የሚያሳስቡት።

የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫ 2012 ቀነ ቀጠሮን ቁርጥ ባያደርግም የአዳዲስ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ግን መመዝገቡን ቀጥሏል። ቦርዱ ዛሬ እንዳስታወቀው ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጥቷል።የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የተሰጣቸው አራቱ ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው።

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሀመድ