1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምሥራቅ ወለጋ፤ ተፈናቃዮች እርቅና ርዳታው

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2016

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በተለይም ኪረሙ ከሚባል ወረዳ ከ1 ዓመት በፊት ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬያቸው እየተመለሱ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ይሁንና ተፈናቃዮችን ወደቀዬያቸው የመመለሱ ሥራ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችንም በድጋፍ በማቅረብ ሊታገዝ እንደሚገባ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4XeMT
ኦሮሚያ ክልል ፤ ኢትዮጵያ ፎቶ፦ ከማኅደር
ኦሮሚያ ክልል ፤ ኢትዮጵያ ጎጆ ቤቶች አቅራቢያ ሰዎች ሲጓዙ ይታያል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ተፈናቃዮች የቁሳቁስና መጠለያ ድጋፍ ተማጽነዋል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በተለይም ኪረሙ ከሚባል ወረዳ ከአንድ ዓመት በፊት ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ይሁንና በህዝብ መሃል እርቀሳልም እንዲወርድ በማድረግ የተጀመረው ተፈናቃዮችን ወደቀዬያቸው የመመለሱ ሥራ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችንም በድጋፍ በማቅረብ ሊታገዝ እንደሚገባ ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው፡፡

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች የሰላም መረጋጋት አንጻራዊ እምርታ እያሳዬ በመሆኑ ነዋሪዎችን ወደ ቀዬያቸው የመመለሱ ስራ በአዎንታዊነት ቢነሳም፤ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ሲመለሱ ያለ በቂ እርዳታ ነው ብለዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በከፋው ግጭት ተፈናቅለው በተለያዩ አከባቢዎች ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW)የሰጡ አንድ የአከባቢው ተፈናቃይ በሕዝብ መካከል መልካም የሚባል መተማመን ተፈጥሮ ተፈናቃዮችን የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

«አሁን ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ላይ አማራውም ወደ ቀዬው እየተመለሰ ኦሮሞውም ወደ ሀሮ ቀበሌ እየገባ ነው፡፡ መልሶ እየሰፈረ ነው፤ በመንግሥት ማለት ነው ። አሁን የሰላሙ ጉዳይ መልካም ነው፡፡ ከፊቱ የተሸለ ነው፡፡ በጣም ሰላም ነው ። በህዝቡ መካከልም በጣም መተማመንን አለ ። እርቁም ጥሩ ነው ።»

ባለፈው ዓመት ኪረሙ ውስጥ በተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት በርካታ የአማራ ተወላጆች ሀሮ ወደ ተባለች ቀበሌ ሲሸሹ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ በብዛት የኪረሙ ወረዳ ከተማ ውስጥ መጠለላቸውን ተፈናቃዩ አክለው ተናግረዋል፡፡ በዚህን ወቅት ቤትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች ተቃጥለው እንደነበርም ተብራርቷል፡፡ ይህ ደግሞ ተፈናቃዮች አሁን ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከአንገብጋቢ ድጋፍ ጋር መሆን እንደሚገባው ነው ተፈናቃዩ በሰጡን አስተያየታቸው የጠየቁት፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች፤ በአብዛኛው ህጻናት እና ሴቶች ። ፎቶ፦ ከማኅደር
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጥቃት ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች፤ በአብዛኛው ህጻናት እና ሴቶች ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

«ግን ችግሩ ምን መሰለህ፤ ቦታው ላይ ስንሄድ ብያንስ ቤቱ የተቃጠለ፤ የቤት እቃና የሚባላ የሚጠጣ የሌለበት ስለሆነ እነዚህ ነገሮች ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡ ለመኖሪያ ቆርቆሮ እንኳ መተካት ባይቻል ሸራ እንኳ ቢዘጋጅልን መልካም ነው፡፡ እና መንግሥት አሁን ሰላሙን አስፍኖ ህዝቡን ወደ ቀዬው መመለሱ ጥሩ ሆኖ እያለ የሚበላ እና አልባሳት ነገር ቢኖር  ጥሩ ነበር ። ግን ምግብ የርዳታ እጥረት በጣም ነው ያለው ። በጣም የተቸገረ ህብረተሰብ ነው እዚህ ያለው፡፡ ያን ታሳቢ አድርጎ ቢያሰፍር ጥሩ ነበር ።ቢያንስ ሰዉ ሲመለስ ዝም ብሎ አመዱ ላይ ከሚቀመጥ ሸራ እንኳን ቢኖር ።»

በአከባቢው አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መሆኑን ያልሸሸጉትና አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የኪረሙ ነዋሪ ግን አሁንም ወደ ቀዬያቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች ውስን ናቸው ይላሉ፡፡ «አሁን ወደቀዬያቸው የተመለሱት ውስን ሰዎች ናቸው፡፡ በተለይምበኪረሙ ግጭት ወቅት የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ናቸው እንጂ የተመለሱት ከገጠር የተፈናቀሉ አርሶአደሮች አሁንም ገና አልተመለሱም፡፡ አሁን ሁሉም ወደ ቀዬው ይመለሳል እየተባለ ነው፡፡ ግን ደግሞ አሁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ትንሽ ጥርጣሬ የሚያጭርብኝ ያኔ ወንጀል የፈጸሙ በዚሁ ማህበረሰብ ውስጥ በመሆናቸው ከልብ የሆነ እርቅ እና የካሳ ስነስርዓት መካሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ማህበረሰቡ መካከል የተጀመረው ውይይት በጥልቅ የእርቅ ስነስርዓት ብደገፍ መልካም ነው፡፡ ህዝቡ የተዘረፈው ከብት ሁሉ ሊመለስለት ይገባል፡፡ በዚህ ወረዳ ብቻ ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው ባለፉት ሶስት የግጭት ዓመታት ውስጥ የሞቱት፡፡ እናም ይህ ጥልቅ የእርቅ ስነስርዓት የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡”

 የመንዲ ከተማ በከፊል ። ፎቶ፦ ከማኅደር
ምዕራብ ወለጋ፤ ኦሮሚያ ክልል፤ ኢትዮጵያ የመንዲ ከተማ በከፊል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Negassa Deslagen/DW

እኚህ ነዋሪም የርዳታ ምግብ እጥረት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው የምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ነዋሪም በአንጻራዊት ሰፍኗል ያሉትን የሰላሙን ሁኔታ አሞካሽተው የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጉዳይ ግን ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ያወሳሉ፡፡ «የሰላሙ ሁኔታ እንኳ አሁን ደህና ተረጋግቷል፡፡ ግን ደግሞ መብራ እና ኔትዎርክ ዘግተው ህዝቡ ቅር ተሰኝቷል፡፡ አሁን እራሱ ተራራ ላይ ወጥቼ ነው የማወራህ፡፡ አሁን መብራ ከጊዳ አያና በተጨማሪ በአንገር ጉቲን እና ኪረሙ አይሰራም፡፡»

ነዋሪዎቹ ስላነሱት አንገብጋቢ የርዳታ እና መሰረተ ልማቶች ጥያቄ ከአከባቢው በተለይምከምስራቅ ወለጋ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት የኃላፊዎቹ ስልክ ባለመነሳቱ ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ከርዳታ ጋር በተያያዘ ለኦሮሚያ ቡሳጎኖፋ ቢሮ ኃላፊዎች ደውለን ምላሽ አላገኘንም፡፡

ባለፈው ሳምንት ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ አታለል አቦሃይ ግን ዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት በኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ ማቆማቸው ጫና መፍጠሩን ገልፀው፤ ያም ሆኖ ግን መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ተፈናቃዮችን የርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየጣረ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ