1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ሜሴንጀር  አር ኤን ኤ» ቴክኖሎጅና የወባ መከላከያ ክትባት ምርምር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 21 2013

የበሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ዋና ዋና ክፍሎችን የያዙ ሰው ሰራሽ ዘረመሎችን ወደ ሰዎች ህዋሳት በመላክ የሰውነት የተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅም ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርገው ይህ  ቴክኖሎጂ፤  በአሁኑ ወቅት ለበርካታ በሽታዎች የመከላከያ ክትባትን ለማግኘት ይረዳል የሚል እምነት እያሳደረ መጥቷል።

https://p.dw.com/p/3yCbs
Weltspiegel 11.02.2021 | Corona | Deutschland Marburg | Biontech-Werk
ምስል BionTech/REUTERS

«ሜሴንጀር አር ኤን ኤ»ቴክኖሎጅ የህክምናው ሳይንስ አብዮት



የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት ሜሴንጀር  አር ኤን ኤ ተብሎ የሚጠራው ቴክኖሎጅ የኮቪድ-19  ክትባቶችን በስኬት ማምረት  አስችሏል።  ከዚህ ስኬት  በመነሳትም ሊቃውንቱ ሌሎች ክትባቶችን ለመስራት በመሞከር ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ በዚህ ቴክኖሎጅ የካንሰር ክትባትን ለማግኘት ሰፊ ምርምር እየተደረገ መሆኑን ተመራማሪዎቹ የገለፁ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ  የጀርመኑ ባዮንቴክ ኩባንያ በዚሁ ቴክኖሎጅ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባትን ለማግኘት ሰፊ ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልጿል። በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም «ሜሴንጀር  አር ኤን ኤ» ተብሎ በሚጠራው ቴክኖሎጅ እና በወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ምርምር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የተሳካ የኮሮና ተዋህሲ ክትባት ያመረተው የጀርመኑ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ባዮንቴክ   በሚቀጥለው ዓመት የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በሰዎች ላይ ሙከራ ማድረግ እንደሚጀምር ገልጿል። ክትባቱን የሚያበለፅገው የኮሮና ተዋህሲ ክትባትን ለመስራት የተጠቀመበትን  ተመሳሳይ ዘዴ ማለትም «ኤም አር ኤን ኤ » ቴክኖሎጂን በመጠቀም  መሆኑንም የመድኃኒት አምራች ኩባንያው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ፡፡የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኡጋር ሻሂን  ያለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ የሞት መጠንን መቀነስ የሚያስችል፣ ዘላቂ መፍትሄን የሚያረጋግጥ እና ደህንነቱ የተጠበቀ  ውጤታማ የወባ መከላከያ ክትባት  ለማዘጋጀት በዚህ ቴክኖሎጅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
ለመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ በሽታዎችን  መከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን ለማምረት ጥቅም ላይ እየዋለ  ያለውና ባለሙያዎቹ «ሜሴንጀር  አር ኤን ኤ» ብለው የሚጠሩት ቴክኖሎጅ ምንድነው? ስንል  የጠየቅናቸው በኦሃዮ ስቴት ዩንቨርሲቲ ዋን ሄልዝ ግሎባል ኢንሸቲቭ የምስራቅ አፍሪቃ ሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ጌትነት ይመር ማብራሪያ አላቸው።
«ኤም አር ኤን ኤ » ቴክኖሎጂ ሰው ሰራሽ በሆነ መልኩ በሽታ አምጭ የሆነውን ተዋህስ ወሳኝ የሆነውን አካል ፕሮቲን ፤በሽታ የሚያመጣውን አካል በሙሉ አይደለም።በሙሉ «ቫይረሱ»ን በሙሉ «ፓራሳይቱ»ን ሳይሆን ወሳኝ የሆነውን የምትጠቅመውን አካል በመውሰድ ፤ሜሴንጀር « አር ኤን ኤ» ማለት ከስሙ እንደምንረዳው መልዕክት ማስተላለፍ ነው።ሰውነታችንን ማዘዝ ነው።ምን እንዲያደርግ ሰውነታችን ፕሮቲን እንዲያመርት።ስለዚህ በ«ቫይረሱ» ወይ በ«ፓራሳይቱ» ያለን አካል «ኮድ» የተደረገ ነገር።ይሰጣል። ሰውነታችን ውስጥ ይገባል።ሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ ክትባቱ ይህንን ፕሮቲን  አምርት ብሎ ለሰውነታችን ህዋስ ይነግረዋል ማለት ነው።ልክ ያንን ሲያመርት ሰውነታችን ምንድነው የሚያስበው የሆነ ነገር ሊያጠቃ እየመጣ ነውና መከላከያ  አምርት የሚል መልዕክት ነው።ስለዚህ በአጠቃላይ የ«ሜሴንጀርኤም አር ኤን ኤ » ቴክኖሎጂ  የ«ቫይረሱ» ወይም በወባ ጊዜ የ«ፓራሳይቱ» ወይም የባክቴሪያው  ቅንጣት ሰውነታችን ውስጥ ገብቶ የሰውነታችንን የማምረቻ  «ሜካኒዝም»ተጠቅሞ ፕሮቲን ያመርታል። ያ ፕሮቲን ለሰውነታችን የሆነ ወራሪ እንደመጣ እንዲሰማው ያደርጋል ያኔ የሰውነታችን የበሽታ መከላከያ ይነቃቃል።»በማለት ነው ያብራሩት።

Deutschland | Coronavirus | Moderna Impfstoff
ምስል Frank Hoermann/SVEN SIMON/picture alliance
Biontech
ምስል Boris Roessler/dpa/picture alliance

ባለሙያው እንደሚሉት በዚህ ቴክኖሎጅ የሚመረት ክትባት ወደ ማዕከላዊ የህዋስ ክፍል ወይም «ኒዩክለስ» ውስጥ ዘልቆ ሳይገባ «ሳይቶፕላዝም» በተባለው ፈሳሽ የህዋስ ክፍል ላይ ፀረ-ባዕድ አካላት የሆኑ ፕሮቲኖች እንዲመረት  ትዕዛዝ የሚሰጥ  ነው።ዓላማዉም  የሰውነትን የመከላከያ አቅም በማነቃቃት በሽታውን ቀድሞ መከላከል ነው።
የመከላከያ ክትባቱን በቀላሉ በማምረት በብዛት ለማዳረስ የሚመች መሆኑ ደግሞ ቴክኖሎጅውን  ለየት ያደርገዋል ይላሉ።
«ሜሰንጀር ሪቦ ኒዩክሊክ አሲድ»  በምህፃሩ« ኤም አር ኤን ኤ» በጎርጎሪያኑ 1990 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአይጦች ላይ  የተሞከረ ቴክኖሎጅ ሲሆን፤በዚህ ሙከራ  ህይወት ባለው ህዋስ ውስጥ ዘረ-መላዊ መረጃ በማስተላለፍ  ተከላካይ ፕሮቲን እንዲመረት ማድረግ እንደሚቻል ፍንጭ ተገኝቷል።ሙከራው በዘጠናዎቹ የቀጠለ ሲሆን፤በ2005 ዓ/ም  የተሻለ ሙከራና ውጤት በማሳየቴ የሲካ ተዋህሲን፣የዕብድ ውሻ በሽታና እንፍሉዌንዛን በመሳሰሉት በሽታዎች ላይ ሲሞከር ቆይቷል።የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ደግሞ በታህሳስ 2020 ዓ/ም የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለማበልፀለግ ውሏል። በዚህም ውጤታማ ክትባት ማምረት ተችሏል።
መቀመጫውን ጀርመን ያደረገዉ የባዮንቴክ የምርምር ቡድንም በዚሁ ቴክኖሎጅ ላይ ተመስርቶ በጎርጎሪያኑ 2022 መጨረሻ የወባ መከላከያ ክትባትን  በሰዎች ላይ ለመሞከር  ማቀዱንም ይፋ አድርጓል። 
ይህንን  ተከትሎ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየን  በ«ሜሴንጀር አር ኤን ኤ»ቴክኖሎጅ የህክምና ሳይንስ አብዮትን እየተመለከትን ነው። ሲሉ ነበር የገለፁት። 
የወባ በሽታን ማጥፋት ተጨባጭ ግብ ሲሆን ይህም በዚህ ትውልድ ሊሳካ  ስለመቻሉ  ቀድመን ማወቅ ችለናል  በማለትም በክትባቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
ባለሙያው ዶክተር ጌትነትም ቴክኖሎጅው በሁለት መንገድ ፈጣንና ለማንኛውም አይነት በሽታ መጠቀም የሚያስችል ነው ሲሉ ተስፋ ሰጭነቱን ያጠናክራሉ። 
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ውጤታማነቱ የተረጋገጠ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ለማግኘት ተመራማሪዎች ለበርካታ ዓመታት  ሙከራዎችን አካሂደዋል። ያምሆኖ እስካሁን ድውጤታማነቱ የተረጋገጠ  ክትባት ገና  አልተገኘም። ነገር ግን  በቅርቡ አስትራዜኒካን ባመረተው ኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ይህንኑ ቴክኖሎጅ በመጠቀም « R21 ማትሪክስ ኤም» የተባለ የወባ መከላከያ ክትባት በአፍሪቃዊቷ ሀገር  ቡርኪናፋሶ  በሰዎች ላይ ሙከራ ያደረገ ሲሆን የመከላከል አቅሙ ከ70 በመቶ በላይ መሆኑ ታውቋል።ከዚህ አንፃር  የአሁኑ የባዮንቴክ  የሙከራ ዕቅድ ታላቅ  ተስፋ የተጣለበት  ሁለተኛው ክትባት ነው። ይህ መሰሉ መፍትሄ  በድሃ ሀገራት ጤና  ላይ አስተጾው ከፍተኛ  ነው ይላሉ ዶክተር ጌትነት። 
የበሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ዋና ዋና ክፍሎችን የያዙ ሰው ሰራሽ ዘረመሎችን ወደ ሰዎች ህዋሳት በመላክ የሰውነት የተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅም ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርገው ይህ  ቴክኖሎጂ፤  በአሁኑ ወቅት ለበርካታ በሽታዎች የመከላከያ ክትባትን ለማግኘት ይረዳል የሚል እምነት እያሳደረ መጥቷል።
ይህንን ቴክኖሎጂ መጠቀም ከነባሮቹ  ዘዴዎች በበለጠ ክትባትን ለማበልፀግ ፈጣን መንገድ በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ፍለጋ ሊያቆም ይችላል ተብሏል፡፡
 በዓለም የጤና ድርጅት ፣ በአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ ማዕከላት እና በአውሮፓ ህብረት የሚደገፈው ይህ የክትባት ምርምር  እንደታሰበው ከተሳካ በዓመት ከ 400 ሺህ በላይ ሰዎችን  በተለይም በአፍሪካ  ሕፃናትን ለህልፈት የሚዳረገውን  የወባ በሽታ በመዋጋት ረገድ ትልቅ ርምጃ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው።

Culiseta annulata,Ringelschnake,Banded Mosquito
ምስል Hippocampus Bildarchiv/picture alliance

 

ሙሉ ቅንብሩን  የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ አንጋብዛለን።


ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ