1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን አምባሳደር ንግግር፣ የቀድሞ ተዋጊዎች ጉዳይ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምገባ

ዓርብ፣ ግንቦት 16 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት ያስቆጣው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ እቅድ በትግራይ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ተማሪዎችን ለመመገብ አቅም አንሷቸዋል መባሉን በተመለከተ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ከሰጧቸው አስተያየቶች መራርጠናል።

https://p.dw.com/p/4gDHb
 አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ
በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር አርቪን ማሲንጋምስል Abebe Feleke/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ግንቦት 16 ቀን 2016

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሥለ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊና የሰብአዊ መብት ይዞታ የሰጡትን አስተያየት የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር «ሐሰት» እና «ተቀባይነት የሌለዉ» በማለት መንቀፉ ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ነው።   አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ አዲስ አበባ ዉስጥአንድ ታሪካዊ ሕንፃ ሲጎበኙ ባደረጉት ንግግር «መንግሥትን የሚተቹ ወገኖችን ማሰር፣ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት እንደማይጠቅም ገልጸው፤ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሀገሪቱ ወደ ዉጤታማ ምክክር እንድትገባ ይረዳል ብለዉ ነበር። ይህን አስመልክተው አስተያየታቸውን በፌስቡክ ካጋሩት መካከል ወርቅነህ ውባንተ፤ «ምኑ ላይ ነው ስህተቱ ትክክል ነው የተናገረው» ሲሉ፤ ቸኮል ለማም፤ «ምኑ ነው ሐሰቱ» በማለት ይጠይቃሉ።

አዲስ ዘመን አዲስ ዘመን ግን፤ «ሰውየው ምን አገባቸው? በአንድ ሀገር የውስጥ ገዳይ ገብቶ መፈትፈት እና የሁለቱን ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወይም ወዳጅነት ከማጠናከር ይልቅ ጥላቻ እና ልዩነትን ማራገብ ተገቢ አይደለም።» በማለት ተችተዋል። ጂግሳ ኒሞና ግን፤ «ሰላም አውርዱ ማለት ኃጢያቱ ምኑ ላይ ነው?» ሲሉ ይጠይቃሉ።

ሻምበል አገንሳ ሻምቡ በበኩላቸው፣ «አምባሳደሩ ትክክል ብለዋል ብቻ ሳይሆን መሬት ያለ ሀቅ ነው ። እውነት በእውነቱ ምስጋና ይገባቸዋል» ነው የሚሉት።  አቤነዘር ጀምበሩም ፤ «አምባሳደሩ መሬት ላይ ያለውን ነገር በተገቢው መንገድ ነው ያስቀመጡት። ምክረ ሃሳባቸውን ባለድርሻ አካላት በአፋጣኝ ቢተገብሩ ለዚህ ሀገር ችግር መፍትሄ እንደሚያመጣ አልጠራጠርም!!!» ባይ ናቸው። ገሊሞ ጋሞ ግን፤ «እነሱ የሰው ምክር አይመቻቸውም» በማለት መለሱ፤ አብዲ ኤም ሰይድ ደግሞ የሌሎች ሃገራት አምባሳደሮችም የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ ነው የጋበዙት፤ «ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበትን ሀቅ በትክክል ያፀባረቀ ነው መወጣት መግባት ያልተቻለበት ሁኔታ ነው ያለው የሌሎች ሀገር አባሳደሮችም ለኢትዮጵያ ሰላም መታገል አለባቸው።» በማለት።

ኢንድሪስ መሀመድም፤ «የምንኖረውን እውነት ስለተናገሩልን እናመሰግናለን ክቡር የአሜሪካ አምባሳደር» ነው ያሉት። ዋካ ዋካ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «በውስጥ ጉዳይ አያገባቸውም» ይላሉ። ሀሰን ጅቢቾ በበኩላቸው፤ «ኢትዮጵያ ሉኣላዊ አገር ናት። የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በታጠቁት ሐይሎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እያደረጉ ያሉት ጥረት መልካም ነው።» ሲሉ፤ መርሻ ተሰማ በበኩላቸው፤ «የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሩ ያሉ አምባሳደሮች ልክ እንደ ራሱ ዜጎች አስፈራርቶና አፍኖ እውነትን ከመናገር የሚገድብ ይመስለዋል መሰል። በቀደም እኒህን አምባሳደር የብልፅግናው ጉምቱ ምሁር ለምን ተቹን በሚል ከዝንጀሮ ጋር አመሳስለው በብስጭት ሀሳባቸውን ከኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ሲተቹ ነበር... አሁን በደንብ ገቡላቸው።» ነው ያሉት።

ከትግራይ ተዋጊ ኃይሎች
የቀድሞ ተዋጊ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል። ፎቶ ከማኅደር፤ የትግራይ ተዋጊ ኃይሎች ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

የአሜሪካ አምባሳደሩን የፖሊሲ የተባለውን ንግግር ከተቹት አንዱ አላማር ለሌ ደግሞ፣ «በውስጥ ጉዳይ ምንም አይመለከታቸውም። የሚመለከታቻው ከሆነ በዩክሬን እና ፍልስጤም የሚደርሰውን ውድመት ያስቁሙ።» ብለዋል። ፍሰሀ መኮንን በበኩላቸው፤ «ሲያልቅ አያምር አለ የሀገሬ ሰው፤ ከአሜሪካ ጋር መጣላት ሊጀመር ነው?» በማለት ሲጠይቁ፤ ከፈኒ አዱኛም፤ «በድጋሜ "no more" ጨዋታ ልንጀምር እንዳይሆን?» ይላሉ። ፍቃዱ ወልዴ ደግሞ «እኔ በጣም የሚገርመኝ መቼ ነው ከቀድሞው የወደቁ መንግሥታት የምንማረው? በቃ በአፈና ጊዜ ሊገዛ ይችላል በዘላቂነት ግን አይቀጥልም፤ በጊዜ ችግሮቻችንም በመነጋገር እንፍታ።» በማለት ምክራቸውን ሲለግሱ ጌቱ ንጋቱ ታዲያ፤ «ምን አይነት ዘመን ነዉ? እዉነትን መሸከም የከበደበት።» በማለት ትዝብታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል።

 

ኢትዮጵያ ውስጥየቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ካናዳ 14 ሚሊየን ዶላር መመደቧ ተሰምቷል። በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ካስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ይተገበራል የተባለው በትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን በመደገፍ ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለሱ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች የታቀደውን ያህል አለመሳካቱ ነው የሚገለጸው። ይህን አስመልክተው አስተያየት ከሰጡት አንዱ አበበ ታምሩ፤ «ሲሆን የምናየው ከሆነ ጥሩ ዜና ነው» ነው ያሉት። አህመድ ሸሁሴን ግን፤ «ለኔ ግልፅ ያልሆናልኝ  የቀድሞ ታገዮችን ሲሉ ከደርግ እስከ ብልፅግና ያታገሉትን ነው ወይስ የትግራይን ብቻ ነው ግልፅ አርጉልን እስቲ እኔም ታጋይ ስለነበርኩ ነዉ» በማለት ማብራሪያ ጠይቀዋል፤ በዕደ ተክሌ ደግሞ፤ «የትግራይ መከላክያ ሠራዊት እንጂ የቀድሞ ተዋጊዎች የሚባል የለም፤ የአሁን እንጂ የቀድሞ ኣይደሉም።» ነው የሚሉት። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከ200 ሺህ በላይ የትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎች በሚል የተገጸውን ቁጥር የተመለከቱት የፌስቡክ ተጠቃሚ ያሬድ አባተ፤ «274 ሺህ?» ብለው ከጠየቁ በኋላ « የጠቅላላ የኢትዮጵያ ሠራዊትን ሊያክል ምን ቀረው» ብለዋል። መብቱ ወርቁ ደግሞ፣ «እንደ ፖለቲካ ያለ ውሽታም ህዝቦችን ጨፍጨፊ የለም በዚህች ዓለም» በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ሕንጻምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሌላው የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛው መነጋገሪያ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመመገብ አቅም ማነሱን ያመላከተው መረጃ ነው። እንደ ተገለጸው በዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ምግብ በቀን የተመደበው ገንዘብ አሁን በሀገሪቱ ባለው የዋጋ ንረት ለአንድ ጊዜ የምግብ ሰዓት እንኳ የሚሆን አይደለም። በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ለሌሎች ፕሮጀክቶ ያቀዱትን በጀት ለመጠቀም እየተገደዱ መሆኑም ተነግሯል። ታደለ ብርሃኑ፤ «እና አንሶላና ብርድ ልብስ ይዛችሁ ይባል የነበረው የዓመት ቀለባችሁን ይዛችሁ የሚል ሊጨመርበት ነው ማለት ነው?» ብለው ሲጠይቁ፤ ቴዎድሮስ ሀጎስ መለስም፤ «በደርግ ዘመን 36 ብር ነበር ኣሁን ሁሉም በተወደደበት ቁልቁል 22 ብር? ይገርማል» በማለት በጀቱን ያነጻጽራሉ።  

ተፈሪ ደዩ በበኩላቸው፤ «መንግሥት ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ፈጣን መፍትሄ ቢሰጥበት መልካም ነበር» ብለዋል። ካሌብ በየነም፣ «ስለሀገራችን የወዲፊት እጣ ፈንታ ማሰብ እራሱ እጅግ በጣም ያስፈራል» ነው የሚሉት። ደግነቱ ደሴ በበኩላቸው፤ «በምግብ እራስ ሳይቻል ቤተመንግሥት በቢሊዮን ዶላር የሚገነባውስ?» በማለት ይጠይቃሉ።

ጉዳዩ ያሳሰባቸው የሚመስሉት ኢትዮፒያን ብራይት ዴይ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ታዲያ፤ «በዚህ ከቀጠለ ዩኒቨርቲዎቹ በቅርቡ ይዘጋሉ። ይህ ትንቢት ሳይሆን መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነው።» ሲሉ ስቴቪ ጃብ የተባሉት ደግሞ፤ «ዩኒቨርሲቲ መዘጋት አለበት ስንት ፓርክ መሥሪያ ገንዘብ እየባከነ ነው» ብለዋል። የታከታቸው የሚመስሉት ጆን አብ ታዲያ፤ «ባይኖርስ ዩንቨርስቲው መቼም አሁን ካለንበት አይብስ» በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጋሩት።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ