1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

መፈናቀል ኤኮኖሚያዊ ኪሳራው ስንት ነው?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2015

መፈናቀል በኢትዮጵያ በዜጎች መብቶች እና ደህንነት ላይ ካሳደረው ጫና በተጨማሪ ክልሎች እና የፌድራል መንግሥቱን እየተፈታተነ ይገኛል። ኢትዮጵያ በ2021 በተፈናቃዮች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚ ሆና ነበር። ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር በተባለ ተቋም ስሌት በ2020 የመፈናቀል ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 1% ገደማ ይገመታል

https://p.dw.com/p/4Iin8
Äthiopien | Bürgerkrieg | Tigray | Debre Berhan
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ መፈናቀል ኤኮኖሚያዊ ኪሳራው ስንት ነው?

ከእርሻ ማሳቸው እና ከቀያቸው ርቀው መኖሪያቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምትገኘው ባምባሲ ከተማ ያደረጉት የ65 ዓመቱ ገበሬ ኑሯቸው "ምስቅልቅል" ውስጥ ገብቷል። ለደሕንነታቸው በመሥጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የሚሹት ገበሬ የገቡበትን ቀውስ ባሳለፉት ዕድሜ አጋጥሟቸው የማያውቅ እንደሆነ ይናገራሉ። "በተለይ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ራስ ምታት" ሆኖባቸዋል።

እጃቸው ከእርፍ የራቀው ገበሬ ከነስድስት ቤተሰቦቻቸው የተፈናቀሉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከምትገኘው ባቦ ገምበል ወረዳ ነው። ትውልዳቸው ወሎ አምባሳል ተሑለደሬ ወረዳ ቢሆንም ወደ ወለጋ ያቀኑት በ1977 ከተከሰተው ድርቅ በኋላ በቀድሞው የደርግ መንግሥት የሰፈራ መርሐ-ግብር ነበር። ድርቅ እና ረሐብ ሸሽተው በወጣትነታቸው በተጠጉበት አገር ብርቱ ገበሬ ሆነው ቤተሰብ መስርተዋል። "በትንሽ መሬት ላይ" ቡና፣ ጫት፣ ባህር ዛፍ፣ ማንጎ፣ ሙዝ እያመረቱ "ጥሩ ኑሮ" እንደነበራቸው ተናግረዋል።

"የዘለቄታው ዕድላችንእጣ ፋንታችን ምንድነው?" የተፈናቀሉ ገበሬ

እኚህ ገበሬ ኑሯቸውን "በነበር" ለማስታወስ ያስገደዳቸው በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል የሚደረግ ውጊያ ከቀያቸው ካፈናቀላቸው በኋላ ነው። ገበሬው እንደሚሉት አንዲት ልጃቸው በተማረችበት የሙያ መስክ የመቀጠር ዕድል ብታገኝም የቀሩት የቀን ሠራተኛ ሆነዋል።  የተጠለሉበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና የፌድራሉ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርጉላቸውም ኑሮ ግን "በጣም አስቸጋሪ እና ውስብስብ" ሆኖባቸዋል። የረድዔት ድርጅቶች የቤት ቁሳቁስ፣ ማብሰያ፣ የተለያዩ መመገቢያ ዕቃዎች ለተፈናቃዮች ማከፋፈላቸውን የገለጹት ገበሬው "የእኛ መሠረታዊ ችግራችን የቀለብ ነው" ሲሉ አሳሳቢው "የምግብ ጉዳይ" እንደሆነ ይገልጻሉ። "የውኃ ላይ ኩበት ሆነናል። መሬት እና ቤት አልባ ሆነን ተቀምጠናል" የሚሉት ገበሬ "የዘለቄታው ዕድላችን፤ እጣ ፋንታችን ምንድነው?" የሚለው የሚያብሰለስላቸው ነው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። የክልሉ ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በግጭት የወደሙ ጥሪቶችን መልሶ በመገንባት ተፈናቃዮችን ለመመለስ "ወደ 38 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል።"ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

እንዲህ አይነት ልብ ሰባሪ የሰቆቃ ታሪኮች ከትግራይከአማራከኦሮሚያከአፋርከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚደመጡ ናቸው። ኢትዮጵያን በሚያብጠው የፖለቲካ ቀውስ፣ ግጭት፣ ጦርነት እና በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ አደጋዎች ሳቢያ በጎርጎሮሳዊው 2021 የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አገሪቱን ከዓለም ቀዳሚ አድርጓት ነበር።

መቀመጫውን በስዊትዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር (IDMC) የተባለ ተቋም ባወጣው ሪፖርት በ2021 በኢትዮጵያ ከ5.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል። የኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የፕሮግራሞች ኃላፊ ክሪስቴል ካዛባት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት መፈናቀል በዜጎች እና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ የበለጠ ጫና አለው። 

"መፈናቀል በሰዎች ሕይወት በተለይም በጸጥታ፣ በጤና እና ደሕንነታቸው ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በመላው ዓለም በተለይም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከታየበት ከእንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ሲደርስ ኤኮኖሚው ላይ ጭምር ጫና እንደሚኖረው ማስታወስ እጅግ ጠቃሚ ነው" የሚሉት ክሪስቴል ካዛባት "ተቀብለው የሚያስተናግዷቸው ማኅበረሰቦች አንዳንድ ጊዜም የትውልድ ማኅበረሰባቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው" የኤኮኖሚ ተግዳሮት እንደሚገጥማቸው ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ ማሳያ

ይኸ ተጽዕኖ ክሪስቴል ካዛባት እንደሚሉት የአንድ ማኅበረሰብ፣ ክልል ግፋ ሲልም የአገርን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት የመገዳደር አቅም አለው። ለዚህ ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል። የ65 ዓመቱን ገበሬ ከነ ቤተሰቦቻቸው ያስጠለለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት በገጠሙት ተከታታይ ግጭት ሳቢያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉበት ነው።

አስከፊ እና ተደጋጋሚ ግጭቶች ባስተናገደው የመተከል ዞን ብቻ ወደ 250 ሺሕ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። በአጠቃላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር 475 ሺህ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ያረጋገጡት የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ በተሰራ ጥናት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ "ወደ 38 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል። የገንዘቡ መጠን ብዙ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው "የወደሙ ነገሮች ብዙ ስለሆኑ ከዚያ አንጻር ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ባሉ ጊዜያት ለመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋም የሚያስፈልግ ነው" ብለዋል።

ተፈናቃዮች
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን አፈናቅሏል። ነጋዴዎች መደብሮቻቸውን፣ ገበሬዎች ማሳቸውን የመንግሥት ተቀጣሪዎችም ሥራቸውን ጥለው ለደሕንነታቸው ለመሸሽ ተገደዋል። ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ይኸ የገንዘብ መጠን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2015 ከኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ከተመደበለት 3.7 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ እጅጉን የላቀ ነው። ይኸ ጉዳይ የክልሉ መንግሥት ጥብቅ የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ መመሪያ ገቢራዊ እንዲያደርግ ካስገደዱ ምክንያቶችም አንዱ ነው። በግጭት የወደሙ ንብረቶችን በመገንባት ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም የክልሉን በጀት የተፈታተነ መሆኑን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሒ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን "ከዚህ በፊት በክልሉ በጀት ውስጥ ያልነበረ" መሆኑን የገለጹት አቶ ዚያድ አብዱላሒ "ከፍተኛ ወጪ ያስወጣናል። ከተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው" ብለዋል።

ይኸ ጫና ግን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት በ2015 በጀቱ ከመደበው 345.12 ቢሊዮን ብር መደበኛ ወጪ አብዛኛውን ከሚወስዱት መካከል "በጦርነቱ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ለሚያስፈልግ የዕለት ዕርዳታ" ይገኝበታል።

የትግራይ ተፈናቃዮች በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሽሬ ካምፓስ ተጠልለው
ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ በትምህርት ቤቶች እና በዩኒቨርሲቲዎች ተጠልለዋል። በኢትዮጵያ ፌድራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሰላም ንግግር ቢጀመርም ውጊያ አልቆመም። ምስል Baz Ratner/REUTERS

ምግብ፣ ጊዚያዊ መጠለያ፣ ጸጥታ፣ የጤና እና ትምህርት  የመሳሰሉ የተፈናቀሉ ዜጎች መሠረዊ ፍላጎቶች ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ። ይኸ ወጪ በራሳቸው በተፈናቃዮቹ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ ባስጠጓቸው ማኅበረሰቦች፣ በመንግሥት እና በዕርዳታ ድርጅቶች ትከሻ ላይ የሚወድቅ ነው። ለኢትዮጵያ ተፈናቃዮች መሠረታዊ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን እና በመንግሥት ላይ ያሳደረውን ጫና ለመረዳት ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዶይቼ ቬለ መረጃ ቢጠይቅም የተቋሙ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር በሰራው ስሌት መሠረት ግን በጎርጎሮሳዊው 2020 ለአንድ ተፈናቃይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በአማካይ 250 ዶላር ገደማ እንደ ነበር ክሪስቴል ካዛባት ገልጸዋል። ካዛባት "ይኸ ወጪ በ2020 በኢትዮጵያ በተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ሲባዛ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የድርጅቱ የፕሮግራሞች ዳይሬክተር እንደሚሉት ግን ይኸ የገንዘብ መጠን ትክክለኛውን ሁኔታ የሚያሳይ አይደለም። "የመፈናቀልን አጠቃላይ ኤኮኖሚያዊ ዳፋ መለካት አልቻልንም። ለምሳሌ ያክል ባስጠጓቸው ማኅበረሰቦች ላይ የሚከተለውን ጫና ወይም ተፈናቃዮች እንደ ቀደመው ጊዜ ሸቀጦች መሸመት፣ መስራት እና ማምረት ባለመቻላቸው የሚፈጠረውን የረዥም ጊዜ ዳፋ አያካትትም" ሲሉ ተናግረዋል።

ጉዳዩን ውስብስብ የሚያደርገው ለተፈናቃዮች መሠረታዊ አገልግሎቶች ማቅረብ ወይም መልሶ ማቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥትን ትኩረት በሚሹ ሌሎች ውስብስብ እና በርካታ ችግሮች ላይ የሚታከል በመሆኑ ነው። ከመኖሪያ ቀያቸው ባይፈናቀሉም ግጭት፣ ኹከት፣ የከባቢ አየር ለውጥ፣ ጎርፍ እና ድርቅን በመሳሰሉ ኩነቶች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ማገዝ እንደ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያሏቸውን አገሮች በእጅጉ እንደሚፈታተን በኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የፕሮግራሞች ኃላፊ ክሪስቴል ካዛባት ያስረዳሉ። ይሁንና የዛኑ ያክል ሚሊዮኖችን ከቀያቸው ለመሸሽ የሚያስገድዱ መሠረታዊ ጉዳዮች መፍትሔ ማበጀት ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ ሚናው ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመቀበል እየተጠባበቁ
ከመኖሪያ ቀያቸው ባይፈናቀሉም ግጭት፣ ኹከት፣ የከባቢ አየር ለውጥ፣ ጎርፍ እና ድርቅን በመሳሰሉ ኩነቶች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ማገዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ያሏት የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚፈታተን ነው። በሶማሌ ክልል የሚገኘውን የሽንሌ ዞን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በድርቅ ምክንያት በርካቶች ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋሉ። ምስል Mulugeta Ayene/AP/picture alliance

"በ2020 የውስጥ መፈናቀል ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 1 በመቶ ያህል እንደነበረ እንገምታለን። አንድ በመቶ ብዙ ላይመስል ይችላል። ነገር ግን ከአጠቃላይ አገሪቱ አኳይ ይኸ ብዙ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል" የሚሉት ክሪስቴል ካዛባት "ይኸ ገንዘብ ለማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ልማት ወይም ወደ ፊት መፈናቀል እንዳይከሰት ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች ገቢራዊ ለማድረግ ሊውል ይችል የነበረ ነው። ስለዚህ አገሪቱ የምትወስዳቸው ማኅበረሰቦችን የሚጠቅሙ እርምጃዎች  መፈናቀል ባሳደረው ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ምክንያት ተግባራዊ አይሆኑም" በማለት ተጽዕኖውን ገልጸውታል።

"መፈናቀል በኢትዮጵያም ሆነ በበርካታ የዓለም አገራት ከደረሰበት መጠን አኳያ ለጉዳዩ መፍትሔ ማበጀት ለተፈናቀሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ እጅጉን ጠቃሚ ነው" በማለት የኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የፕሮግራሞች ኃላፊ ክሪስቴል ካዛባት አክለዋል።

ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከኑሮ መሠረታቸው እየነቀለ ለሽሽት ለሚዳርጋቸው ፖለቲካዊ እና የጸጥታ ቀውስ መፍትሔ ፍለጋው በፖለቲከኞቿ ጫንቃ ላይ የወደቀ ቢሆንም ተፈናቃዮችን ለማገዝ እና ለማቋቋም ግን አጋሮች ያሿታል። በኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የፕሮግራሞች ኃላፊ ክሪስቴል ካዛባት እንደሚሉት በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና የልማት ባንኮች ኢትዮጵያን እና ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸውን አገራት ሊያግዙ ይችላሉ። ተፈናቃዮችን እና ያስጠጓቸውን ማኅበረሰቦች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማቅረብ አፋጣኝ እገዛ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ክሪስቴል ካዛባት ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ የሚፈጥር የረዥም ጊዜ መዋዕለ ንዋይ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል። ይኸ ደግሞ በሰብዓዊ እርዳታ ዕቅድ ውስጥ የማይካተቱ የሙያ ሥልጠናዎች ማቅረብ እና አዳዲስ የገቢ ማግኛ ዕድሎች መፍጠርን የሚጨምር ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ