መድኃኒቱን በጥንቃቄ መከታተል የሚያሻው የTB ህክምና
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2013TB ሳንባን ብቻ የሚጎዳ የሚመስላቸው፤ አጠራሩም የሳንባ ነቀርሳ ነው፤ የሚሉ ጥቂት አይደሉም። በፌስቡክ ገጻችን ላይም ይኽንኑ አስተያየት የጻፉ መኖራቸንም አስተውለናል። ባለፈው ሳምንት በፌደራል ጤና ሚኒስቴር መድኃኒት የተላመደ TB ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር አንዳርጋቸው ኩምሳ፤ TB ሳንባን ብቻ የሚያጠቃ ሳይሆን በርካታ የሰውነት ክፍሎችን የሚጎዳ የጤና ችግር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ሀኪም ቤቶችና የጤና ተቋማት የግሎችን ጨምሮ በቂ ስልጠና በወሰዱ ባለሙያዎች አማካኝነት ለመደበኛው የTB በሽታ ህክምና እየሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል። መድኃኒት የተላመደውን TB የሚያክሙ ወደ 67 የሚሆኑ የህክምና ተቋማት መኖራቸውንም ገልጸዋል። የTB መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው ያመለከቱት ዶክተር አንዳርጋቸው ታማሚዎች ተገቢውን የሀኪም ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። መድኃኒት በመውሰዱ ሂደት በሚያጋጥሙ የተለያዩ የጤና ቀውሶች ምክንያትም የTB መድኃኒት ሊቋረጥ እንደማይገባ፤ ይልቁንም ወደ ሀኪም በመሄድ ተገቢውን ምክርና ርዳታ ማግኘት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት የሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ ትኩረት ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮና ተሐዋሲ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ኮቪድ 19 ኢትዮጵያም ውስጥ የታማሚዎች እና በዚህ መዘዝም ሕይወታቸው የሚያልፈው ቁጥር እየተበራከቱ መሄዱ ይነገራል። TBም ሆነ ኮቪድ 19 ሳንባን የሚያጠቁ በሽታዎች መሆናቸውን ያመለከቱት ዶክተር አንዳርጋቸው የሚኖረው ሳል እና ይዞታው እንደሚለያይ፤ ሆኖም በምርመራ መጣራት እንዳለበትም አሳስበዋል። በፌደራል ጤና ሚኒስቴር መድኃኒት የተላመደ TB ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር አንዳርጋቸው ኩምሳ ህክምናውን የጀመሩ ታማሚዎች ያለመታከት ለ ስድስት ወራት የሚሰጣቸውን መድኃኒት ተከታትለው በመውሰድ በሽታውን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙም ምክራቸውን ለግሰዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ