1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥር የታቀፉ ፓርቲዎች "መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ እና ተጨባጭ ሁኔታው" በሚለው ሀሳብ ላይ ተወያየ። ዉይይቱ በዋናነት ገዢው ፓርቲ በተወዳዳሪዎቹ ላይ የሚያደርሰው ጫና ማየል፣ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት አለመከበር፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳያድግ ምክንያት ናችው ተብለው ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/4SDH5
Äthiopien |  Interparteilicher Dialog
ምስል Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዐውድ አለመኖሩ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥር የታቀፉ ፓርቲዎች "መድብለ ፓርቲ  በኢትዮጵያ እና ተጨባጭ ሁኔታው" በሚለው ሀሳብ ላይ ዛሬ ተወያይተዋል። ለውይይት መነሻ እንዲሆን ካለው ነባራዊ ሀቅ ይልቅ በመርህ ደረጃ የሚታወቁ ሳይንሳዊ ሀሳቦች የቀረቡበት ይህ ውይይት ላይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋናነት ገዢው ፓርቲ በተወዳዳሪዎቹ ላይ የሚያደርሰው ጫና ማየል ፣ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት አለመከበር፣ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ አለመለያየት፣ በገዢው እና ሌሎች ፓርቲዎች ምካክል  ፍትሕዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳያድግ ምክንያት ናችው ተብለው ቀርበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት በራሱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንዳይጠናከር አድርጓል የሚሉ ሀሳቦችም በዚሁ ውይይት ላይ ተንፀባርቀዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፖለቲካ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዐውድ አለመኖሩን ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫዎች አለመደረጋቸውን ፣ የሕግ የበላይነት መደፍጠጥን ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለመጠናከር ጠቅሶ በዋናነት መንግሥት ይህ እንዲስተካከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።

መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ እና ተዋረድ ሕግጋት መስፈራቸውን የጠቀሱት የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅራቢው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህር ጽሁፋቸው ንድፈ ሀሳባዊ እና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ የዳሰሰ አልነበረም። በሕግ የሰፈሩት ድንጋጌዎች በተቋም የተደገፉ አለመሆናቸውን ግን አምነው ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደ ሁል ጊዜው በተለይ መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ያሳድርብናል ያሉትን ጫና በመዘርዘር ፣ ለእውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለመዳበር ምክንያት ያሏቸውን በርከት ያሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል። "ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ገንዘብ እንዳይደግፉና እንዳይደጉሙ ይፈራሉ። የገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ አለባቸው።"

"ወደ ወረዳ እና ቀበሌ መዋቅር ስንወርድ የአንድን የፓርቲ አባል ወይም አመራር አድማ የማስደረግ ፣ ስትሞት የሚቀብርህ የለም ፣ ቤትህ ሲቃጠል አንደርስልህም፣ ከማህበራዊ ነገሮች ገልልተኛ ትሆናለህ እየተባለ መብቱን መለማመድ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው።"

Äthiopien |  Interparteilicher Dialog
"መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ እና ተጨባጭ ሁኔታው"ምስል Solomon Muchie/DW

"ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕግ፣ ፖሊስ ፣ መከላከያ ፣ የፀጥታ እና የመረጃ አገልግሎቶች የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባል መሆን አይችሉም ተብሎ ተደንግጓል። ዛሬ ፍርድ ባት ነፃ አይደለም። ፖሊስና መከላከያ በቀጥታ የፖለቲካ ፓርቲን እየደገፉና  የሌሎች ተቃዋሚ  ፓርቲዎችን ሥራ እያደናቀፉ እንዳለ በግልጽ የሚትልወቅ ነው።"

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ኢትዮጵያ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አፈፃፀም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኗን በማሳያዎች ጭምር ገልፀዋል። "የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዐውድ መፈጠር መቻል አለበት። በዚህ ረገድ ብዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ። ምርጫ ይወዳደራሉ ነገር ግን የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ከመሆኑ አንፃር በአብዛኛው የገዢው ፓርቲ የበላይነት አለ።"

የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጉባኤ ለማድረግ አዳራሾችን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሲከለከሉ ፣ ምርጫ ሲቃረብ የፓርቲዎች አባላትና አመራሮች ከእስር እስከ ግድያ ጥቃት ሲደርስባቸው ይልውቃል። ከዚያም አልፎ ገዢው የፖለቲካ ማህበር የመንግሥትን ንብረት እንዳሻው ሲገለገል ፣ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ሲያስገባ ምነው ለተቃዋሚዎችስ ይህንን አያስፈጽምም በሚል በፓርቲዎች  ይተቻል።

ለመሆኑ የመድብለ ፓርቲ መኖር አለመኖር መለኪያ ሚዛናችሁ ምንድን ስንል የቦርዱን ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለን ጠይቀናቸዋል። "አንዱ መለኪያ በምርጫ ጊዜ ፓርቲዎች ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ ማመቻቸት ነው" ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ነጋu መሐመድ