መዝናኛ፦ የአባይ ዳር ሙዚቃ
እሑድ፣ ጥቅምት 16 2012ጢስ ኣባይ ከባሕር ዳር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ አነስተኛ የገጠር ከተማ ናት። ከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተጠቃልላለች። በዓለም ቅርስነት ተመዘገበው የጢስ አባይ ፏፏቴ የሚገኘውም በዚችው ከተማ አቅራቢያ ነው። የፏፏቴው የውሀ መጠን ክረምቱን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። በመስከረምና ጥቅምት ወራት የፏፏቴው መጠን የጎላ ቅናሽ ባያሳይም የውሀው ጥራት ግን እየጨመረ ስለሚሄድ ለፏፏቴው ልዩ ትዕይንት ይፈጥርለታል።
አብዛኛውን ጊዜ በሰማይ የሚታየው ቀስተ ዳመና በፏፏቴው የታችኛው ክፍል ተሰርቶ ማየትም ለአባይ ፏፏቴ ሌለኛው ትዕይንቱ ነው፡፡
የአገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች በብዛት ከሚጎበኙት የአማራ ክልል የተፈጥሮ መስህብ ቦታዎች በመጀመሪያ ረድፍ ከሚጠቀሱት ወስጥ አንዱም ነው። ፏፏቴው ከሚማርከው ትዕይንቱ ባሻገር ድምፁም ልዩ ቦታ ሚሰጠው ነው።
ታዲያ ወደዚህ ፏፏቴ የሚጓዙ ጎብኝዎች በፏፏቴው ትዕይንትና ድምፅ እየተደመሙ ተፈጥሮን ሲደንቁ የአካባቢው ወጣቶች ደግሞ በባሕላዊ ዋሽንትና ማሲንቆ ጨዋታ ያጅቧቸዋል።
ከወጣቶች መካከል አበበ ዓለሙ አንዱ ሲሆን በዋሽንት ቱሪስቶችን ማዝናናት ከጀመረ 10 ኣመታትን አሳልፏል፡፡ እንደየ ወቅቱ ሁኔታ ከአገር ጎብኚዎች በቀን እስከ 100 ብር ድረስ ገቢ እንደሚያገኝ ወደ ቦታው ሄዶ ለነበረው የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ተናግሯል።
ማሲንቆ የሚጫወተው ገብረሕየወት ማረውም ሙያውን ከአባቱ አንደወረሰና በዚሁ ቱሪስት በማዝናናት ስራ ከ10 ኣመታት በላይ እንደቆየበት ተናግሯል።
አሁን በቱሪስት አስጎብኝነት ስራ ላይ የተሰማራው ውብሸት አሳዬ ቀደም ባሉት ዓመታት በዋሽንት ጨዋታ ቱሪስቶችን ያዝናና አንደነበርና የ3 ዓመት የቱሪዝም ትምህርተ ስልጠና ወስዶ በማስጎብኘት ስራ ላይ መሰማራቱን ናገራል።
ፏፏቴውን ሲጎበኙ ካገኘኋቸው ቱሪስቶች መካከል ስፔናዊው ካርሎስ ፏፏቴውን ከ20 ጊዜ በላይ መጎብኘታቸውን ጠቅሰው አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የተፈጥሮ መስህቦች ጢስ አባይ ፏፏቴ ምርጥና ድንቅ ነው በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
ዓለምነው መኮንን
ተስፋለም ወልደየስ