1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መዋለ ሕፃናት ከፋተርሽቴትን ለዓለም ከተማ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2014

ከአዲስ አበባ 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የመረሃ ቤቴ አዉራጃ ዓለም ከተማ እና በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት የምትገኘዉ ፋተርሽቴትን ከተማ የእህትማማችነት ማህበርን መስርተዉ የትምህርት የባህል ልዉዉጥን ማድረግ ከጀመሩ ዛሬ ሃያ ሰባተኛ ዓመት ላይ ደርሰዋል።

https://p.dw.com/p/44jHU
Alexander Bestle | Sponsorenlauf der Karlheinz-Böhm-Schule
ምስል Privat

ጀርመናዉያኑ ሦስተኛ የህጻናት መዋያ ለማስገንባት ገንዘብ እያሰባሰቡ ነዉ

የኢትዮጵያዋ ዓለምከተማ እና የጀርመንዋ ትንሽዋ ከተማ ፋተርሽቴትን የወዳጅነት ማኅበር 27ኛ ዓመቱ ይዞአል። ሰሞኑን በጀርመን የሚገኙት የማኅበሩ አባላት በዓለም ከተማ ሦስተኛ የህጻናት መዋያ ለማስገንባት የርዳታ ገንዘብ እያሰባሰቡ ነዉ።

Alexander Bestle | mit Diakon Jansen
ምስል Privat

 የዓለም ከተማና የጀርመንዋ ፋተርሽቴትን ከተማ የወዳጅነት ግንኙነት ከተመሰረት 27 ዓመታት አስቆጠረ። የሁለቱ እህትማማች ከተሞች የወዳጅነት ማኅበር የተቋቋመዉ የዛሬ 27 ዓመት  ሰዎች ለሰዎች የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅት መስራች በኦስትርያዊዉ በካርልሃይንስ ቦም እና በቅድሞዉ የፋተርሽቴትን ከንቲባ ፒተር ድርሊንገር ነበር። ዛሬ በጀርመንዋ የዓለም ከተማ እህት በሆነችዉ በፋተርሽቴትን ከተማ የሚገኙ ወደ 600 የሚሆኑት የማኅበሩ አባላት ሦስተኛ መዋለ ህጻናት እና የሞያ ስልጠና ማዕከል ለመገንባት በጀርመን እርዳታን እያሰባሰቡ ናቸዉ። በዓለም ከተማ ማኅበሩ እስካሁን  ሁለት የሕጻናት መዋያዎችን አንድ ቤተ-መጽሐፍት እንዲሁም አንድ ቤተ-መዘክርን ከፍቶ ለበርካታ ህጻናት እድልን ከፍቶአል። በዚሁ ህጻናት  መዋያ ለሚሰሩ ቁጥራቸዉ ቀላል ለማይባል ኢትዮጵያዉያንም የስራ እድልን አስገኝቶአል።  ሦስተኛ የሕጻናት መዋያን እንዲሁም የሞያ ስልጠና ማዕከልን ለመክፈት እቅድ ከያዘ አራተኛ ዓመት ያስቆጠረዉ ማኅበሩ እቅዱን እዉን ሊያደርግ እጅግ ጥቂት ጊዜያት ነዉ የቀሩት። በጀርመን የዓለም ከተማ እና የፋተር ሽቴትን ማኅበር የፕሮጀክትና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ቤስትል እንደሚሉት በዓለም ከተማ ሦስተኛ የሕጻናት መዋያ ለመገንባት እቅድ ከያዝን ወደ አራት ዓመት ሊሆነን ነዉ። በገንዘብ ችግር ምክንያት እስካሁን ማሳካት አልቻልንም ነበር። አሁን ግን በጀርመን በጉጉት የሚጠበቀዉን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ አደባባይ መደብ ዘርግተን ኢትዮጵያን እንያስተዋወቅን ስለዓለምከተማ እየተረክን፤ ትንሽ ስጦታም አዘጋጅተን የርዳታ ገንዘብ እያሰባሰብን ነዉ። ህልማችንን እዉን ልናደርግ የቀሩን ጥቂት ወራቶች ነዉ።

Äthiopien | Kindergarten in Aleme Ketema
ምስል Privat

«በእህት ከተማችን በሆነችዉ በዓለም ከተማ ለማሰራት ላቀድነዉ የሕጻናት መዋያ የገና በዓል ከመድረሱ ከሦስት ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የርዳታ ገንዘብ እያሰባሰብን ነዉ። ከ 15 ይሮ በላይ ለሚሰጠን ሰዉ እናመሰግናለን ለማለት እና የመልካም የገና በዓል ምኞት መግለጫ አይነት ካርድ አዘጋጅተናል። ይህ የዓለምከተማና የፋተር ሽቴትን የእህትማማችነት ከተሞችን ገፅታ  የሚያመላክት አይነት ማስታወሻ ነዉ። ትናንት ለምሳሌ የከተማችን የፋተርሽቴትን ማኅበር አራት ሺህ ይሮ ሰጥቶናል። እስካሁን ካለፈዉ መስከረም ጀምሮ ወደ 60 ሺህ ይሮ የርዳታ ገንዘብ አሰባስበናል።»

Alexander Bestle | mit Claas Knoop
ምስል Privat

በጀርመን የዓለም ከተማ እና የፋተር ሽቴትን ማኅበር የፕሮጀክትና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ከጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ቤስትል ጋር ይህን ቃለ ምልልስ ለማድረግ ስልክ ስንደዉልልላቸዉ፤ ከስራቸዉ በኋላ ወደ ከተማ ወጥተዉ በዓለምከተማ ለሚገነባዉ ለሦስተኛዉ የሕጻናት መዋያ ገንዘብ ሲያሰባስቡ ነበር ያገኘናቸዉ። 600 ጀርመናዊ አባላት ያሉበት የሁለቱ ከተሞች ማኅበር አባላት ዓለምከተማን እየረዱ ያሉት በትርፍ ጊዜያቸዉ የተለያዩ ድርጅቶችን፤ ተቋማትን እና ግለሰቦችን በማነጋገር በሚያሰባስቡት የርዳታ ገንዘብ ነዉ። በጀርመን አምስት ስድስት ኢትዮጵያዉያን የሚገኙበት ይህ የርዳታ ማኅበር አባል እና የኮሚቴ አባል የሆኑት ትዉልደ ኢትዮጵያዊትዋ ወይዘሮ ሳራ በቀለ፤ ማኅበሩን ከተቀላቀሉ ከ 17 ዓመት በላይ ሆናቸዉ። አሁን ደግሞ በዩንቨርስቲ የሚማሩት ልጆቻቸዉም ከትምህርታቸዉ በኋላ ሥራቸዉ የዓለምከተማን የሚረዳዉን የርዳታ ድርጅት መርዳት መሆኑን ወ/ሮ ሳራ ይናገራሉ። ወይዘሮ ሳራ በጀርመን ሲኖሩ ወደ 25 ዓመት ሆንዋቸዋል። የሦስት ልጆች እናትና ባለትዳር ናቸዉ።

ጀርመናዉያኑ ለዓለም ከተማ ርዳታ በትምህርት ቤቶች የስፖርት እና የተለያዩ ዉድድሮችን እንዲሁም  መገናኛ መድረኮችን በማዘጋጀት ነዉ ርዳታን የሚያሰባስቡት። የማኅበሩ አባላት ለኑሮአቸዉ በእለት ስራቸዉ ተወጥረዉ ቢዉሉም፤ በዓለም ከተማ የሚገኙትን ህጻናት ለመርዳት እና የነሱን የወደፊት እድል በትምህርት ለማመቻቸት እንደማይደክማቸዉ በአጽኖት ይናገራሉ። በጀርመን የዓለም ከተማ እና ፋተርሽቴትን ማኅበር የፕሮጀክትና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ቤስትል እንደሚሉት በዓለም ከተማ ሦስተኛዉን የሕጻናት መዋያ በቅርቡ መገንባት እንጀምራለን።

Alexander Bestle und Sara Bekele
ምስል Privat

«በዓለምከተማ ሦስተኛዉን የህጻናት መዋያ ግንባታን ለመጀመር 150 ሺህ ይሮ ነዉ የሚያስፈልገን። ማህበራችን ለዚህ ግንባታ የሚሆን 100 ሺህ ይሮ እጁ ላይ ይዞአል። አሁን የሚስፈልገን ተጨማሪ 150 ሺህ ይሮ ነዉ። ህጻናት መዋያዉን ለመገንባት በአጠቃላይ 250 ሺህ ይሮ ያስፈልገናል። ከዚህ ዉስጥ ወደ 50 ሺህ ይሮ የሚሆነዉ በህጻናት መዋያዎቹ ዉስጥ ለሚሰሩ ማሰልጠኛ የሚዉል ነዉ። አሁን በሚገነባዉ እና እየሰሩ ባሉት በሁለቱ ህጻናት መዋያዎች ዉስጥ የአካል ጉዳተኛ ህጻናትን እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰራተኞችን ማሰልጠን እንፈልጋለን»

ከሁለት ሳምንት በፊት የትግራይ ታጣቂዎች ከዓለም ከተማ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ደርሰዋል ተብሎ ሁለቱ የሕጻናት መዋያዎች በከተማዉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዉ እንደነበር አሌክሳንደር ቤስትል አንዴም በደስታ ሌላም ሃገሪቱ ጦርነት ዉስጥ መግባትዋን በሃዘን ድባብ ተዉጠዉ ነግርውናል። ታጣቂዎቹ ከተማዋ መግባት ሳይችሉ ተመልሰዋል፤ ስለዚህም እድለኞች ነን ሲሉም ነዉ የተናገሩት።  አሁን በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፤ ከተማዋም ሰላማዊ ኑሮዋን ቀጥላለችም ብለዋል አሌክሳንደር ቤስትል። በዓለም ከተማ የፋተር ሽቴትን የወዳጅነት ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ ደሳለኝ ወንድሜነህን ወደ ዓለም ከተማ ስልክ ደዉለን ዓለምከተማ እንዴት ሰነበተች ብስንላቸዉም ነበር።  

እንደ አቶ ደሳለኝ ፤ ጦርነቱ የተቀለበሰዉ፤ የህወሓት ታጣቂዎች ዓለም ከተማ ለመድረስ 70 ኪሎሜትር ሲቀራቸዉ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

በዓለም ከተማ የፋተር ሽቴትን የወዳጅነት ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ ደሳለኝ ወንድሜነህን እንደተናገሩት በዓለም ከተማ የህጻናት መዋያዉ መገንባት ለህጻናቱ ብሎም ለከተማዉ ከፍተኛ ጥቅም ስላለዉ ጀርመናዉያን ብቻ ሳይሆን በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ለዚህ መልካም አላማ እጃቸዉን ቢዘረጉ ፤ ሃገርን ለመገንባት ከሚደረገዉ ጥረት ጋር አንዱ አካል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከ 200 በላይ ህጻናት በሕጻናት መዋያዉ የተለያዩ ትምhreቶችን ይቀስማሉ።

Äthiopien | Kindergarten in Aleme Ketema
ምስል Privat

ከአዲስ አበባ 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የመረሃ ቤቴ አዉራጃ ዓለም ከተማ እና በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት የምትገኘዉ ፋተርሽቴትን ከተማ የእህትማማችነት ማህበርን መስርተዉ የትምህርት የባህል ልዉዉጥን ማድረግ ከጀመሩ ዛሬ ሃያ ሰባተኛ ዓመት ላይ ደርሰዋል። ሁለቱ የእህትማማች ከተሞች የ 20 ኛ እና 25ኛ ዓመት ቁርኝታቸዉን መታሰብያ ጀርመን ባቫርያ ግዛት የሚገኙት  አባላት ኢትዮጵያ የሚገኙትን የማኅበሩን አባላት ማለትም የዓለም ከተማ መስተዳድር ከንቲባን ጨምሮ የሕጻናት መዋያ ሰራተኞች እና የከተማዋን ነዋሪዎች ጋብዘዉ በደማቅ ማክበራቸዉ የሚታወስ ነዉ። ማኅበርተኞች የሁለቱን ከተሞች ትስስር አስረኛ ዓመት መታሰብያን ሲያከብሩ ደግሞ ጀርመናዉያኑ ማኅበርተኞች ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ፤ ከአዲስ አበባ ዓለም ከተማ ድረስ በብስክሌት በመጓዝ ከነዋሪዉ ጋር በደማቅ ማክበራቸዉ ይታወሳል። አድማጮች የሁለቱ ከተሞች ወዳጅነት መጠንከር የዓለም ከተማ የዛሬ ሕጻናትን የነገ ሃገር ተረካቢዎችን እድል መደገፍ እና ማሳመር ነዉና  ድጋፋችሁ እንዳይለይ፤ ማኅበሩም በጥንካሪዉ እንዲቀጥል በመመኘት ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ