1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግስት ለሕዝብ ዋይታ ጀሮ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ዓርብ፣ ሰኔ 17 2014

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕዝብን ያላማከለ አጀንዳ ያነገቡ ያላቸው ኃይሎች በንፁኃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ እያደረጉ ይገኛሉ፣ መንግሥትም ለሕዝቡ ዋይታና ሰቆቃ ጆሮ አለመስጠቱ አሳስቦኛል በማለት ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/4DCaE
 Ethiopian political parties joint council
ምስል Solomon Much/DW

መንግስት ለሕዝብ ዋይታ ጀሮ እንዲሰጥ መጠየቁን

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በተለያዩ ክልሎች "በግፍ ለተገደሉ ዜጎች መታሰቢያ የሚሆን ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ " ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አቀረበ።

የጋራ ምክር ቤቱ "ሕዝብን ያላማከለ አጀንዳ ያነገቡ እና የተለያየ አላማ እና ግብ ያላቸው " ያላቸው ኃይሎች "የመንግሥትን ዝምተኛና ቸልተኛነት ደጀን በማድረግና ማንም ሊገታቸው የሚችል ኃይል አለመኖሩን ሲገነዘቡ በንፁኃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ እያደረጉ ይገኛሉ፣ መንግሥትም ለሕዝቡ ዋይታና ሰቆቃ ጆሮ አለመስጠቱ አሳስቦኛል" በማለት ተናግሯል።
የጋራ ምክር ቤቱ የማንኛውም መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የሀገሩን ሠላም እና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እንደሆነ ቢታወቅም መንግሥት በዳተኝነቱ ምክንያት ግዴታውን በተሟላ መልኩ ሊወጣ አልቻለም ብሏል።
በሌላ በኩል በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት ለዓንድ አመት ከምንፈቅ ጋብ ቢልም ዳግም የመመለስ ሥጋት እያንዣበበ በመሆኑ ሀገሪቱን ዳግም ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች በድርድር እንዲፈቱ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ትናንት ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አዲስ የምክር ቤቱ የአመራር አባላት ምርጫ ዶክተር መብራቱ አለሙ ሰንበታን ከቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ ፣ ዶክተር አብዱልቃድር አደምን ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ም/ሰብሳቢ እና እስካሁን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው ያገለገሉትን ዶክተር ራሄል ባፌን ስከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፀሐፊ አድርጎ መርጣል።

ሰሎሞን ሙጨ
ዮሐንስ ገብረእግዚአባሔር
ነጋሽ መሐመድ