1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ሰላም ንግግር እንዲመለሱ ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 22 2015

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የጀመረውን የሰላም ንግግር እንዲቀጥል የሲቪክ ማኅበራት ጥሪ አስተላለፉ። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ጀመሩት የሰላም ንግግር እንዲመለሱ በሰሜን አሜሪካ በኦሮሞ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ የሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት በጋራ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4RydF
OLLAA meeting in North America
ምስል Private

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኦሮሞ ሲቪክ ማህበራት ለመንግስት እና ኦነሰ ያቀረቡት ጥሪ

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የጀመረውን የሰላም ንግግር እንዲቀጥል የሲቪክ ማኅበራት ጥሪ አስተላለፉ። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ጀመሩት የሰላም ንግግር እንዲመለሱ በሰሜን አሜሪካ በኦሮሞ ባህል ፣ ቋንቋ ፣  የሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ የማማከር ስራ የሚሰሩ የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት በጋራ ጥሪ አቅርበዋል። 

በሰሜን አሜሪካ በኦሮሞ የባህል፣ የቋንቋ የሰብአዊ መብት እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ የአማካሪነት ሥራ የሚሰራው እና በእንግሊዝኛ (Oromo Legacy leadership advocacy association) ወይም በምኅጻሩ (OLLAA) ለሰላም ንግግር ጥሪ መተላለፉን ገለጸ። ማኅበሩ በመላው ዓለም ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የሲቪክ ማሕበራት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ መንግስት እና ለኦሮሞ ነጻነት ጦር ግልጽ ደብዳቤ መጻፉንም (የተጻፈው ደብዳቤው በኢንተርኔት ነው የተለቀቀው ወይንስ ለሚመለከታቸው በአካል ቀርቧል?) የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሴና ጂምጂሞ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር አስቀድመው ጀምረው ወደ ነበረው የሰላም ንግግር እንዲመለሱ አሜሪካ ግፊት እንድታደርግ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል። 
«የኦሮሞ ማህበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሊፎርኒያ ውስጥ ለ1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ያህል ተቀምጦ ተነጋግሯል። በርካታ ነጥቦች ተነስተዋል። ከእነዚህ ዋስጥ ትልቁ በሰላም ጉዳይ ላይ በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም እንዲመጣ አሜሪካ ሊኖራት ስለሚገባ ተሳትፎ እና ማሳደር ስላለባት ተጽዕኖ በስፋት ተወያይተናል። ነገር ግን ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ችግር አስቸኳይ ውይይት ይፈልጋል ፤ እነዚህ የተለያዩ  ወገኖች እንደገና ተገናኝተው ሰላም እንዲሰፍን ከ20 በላይ የኦሮሞ ማህበራት በጋራ ደብዳቤ ጽፈናል።  »
በመንግስት እና ታጣቂ ቡድኑ መካከል አስቀድሞ የተደረገውን የሰላም ንግግር ተፈጻሚ እንዲሆን አበክረው ሲሰሩ እንደነበር የሚናገሩት ሌላዋ የማህበሩ የቦርድ  አባል ዶ/ር ናርዶስ ጣሰው ናቸው ። እርሳቸው እንደሚሉት በመጀመሪያው የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች ቢያንስ የተኩስ አቁም ላይ ይደርሳሉ የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ያ ሳይሳካ መቅረቱ እንዳሳዘናቸው ነው የሚናገሩት ። ነገር ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጥንም ይላሉ ።
« እና ተስፋ ያደረግነው ቢያንስ የተኩስ አቁም ይኖራል ብለን ነበር። ኦሮሚያ ውስጥ ምንም አይነት ጦርነት መኖር የለበትም ፤ መጀመሪያው ጦርነት ማቆም ነው። እና እሱን ነበር ቢያንስ ተስፋ ያደረግነው ። ነገር ግን አሁንም አበረታች ነው። »
አማካሪዋ ሴና ጂምጂሞም  ይህንኑ ሃሳብ ያጸናሉ ። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለው ሁኔታ ለይደር የሚቆይ አልነበረም ይላሉ።  ማንም ለኦሮሞ ህዝብ ሰላም እና ጥቅም እታገላለሁ እስካለ ድረስ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ለማስቆም ጊዜ መስጠት አልነበረባቸውም በማለት መንግስትም ሆነ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ሰላም እንዲመጡ የግድ ነው ይላሉ።
«የኦሮሞ ነጻነት ጦር ለኦሮሞ ህዝብ ነው የምታገለው ይላል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ኦሮሞ ነው የመረጠኝ ይላል። ኦሮሞ እስከ መረጠው ድረስ ይኼኛውም ለኦሮሞ እየታገለ እስከሆነ ድረስ ኦሮሞ በመሃል መሞት የለበትም ፤ ይህ ከሆነ ሁለታችሁም ኦሮሞን በመግደል ፤ ሀገር ጥሎ ሸሽቶ ስደተኛ እንዲሆን ከማድረግ ፤ በረሃብ እንዲያልቅ ከማድረግ ከጦርነቱ ታቅባችሁ ለቀጣዩ ውይይት ቀን ቢቆርጡ እንላለን ያ ሳይሆን ቢቀር ግን ፤ እንዳመለጠን ዕድል እንቆርጣለን።»
ኢትዮጵያ ውስጥ ምስቅልቅሎሽ ያስከተሉ ቅሬታዎች በርካታ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ናርዶስ ጣሰው በበኩላቸው ፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ለመንግስት እና ለኦሮሞ ነጻነት ጦር ደግሞ በድጋሚ ወደ ሰላም ንግግሩ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። 
« ጥሪያችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎች በጣም በርካታ ናቸው ። እና ተደራሽ መደረግ አለባቸው ። ይህ ደግሞ በውይይት ነው የሚሆነው ። በጦርነት አይሆንም ።  ስለዚህ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ተመልሰው መጥተው በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንዲችሉ እና መጀመሪያ ደግሞ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፤ ጦርነት እንዲቆም ። » 
የሆነ ሆኖ ጥሪው የቀረበላቸው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ምላሽ ስለመስጠታቸው አልታወቀም።
የሲቪክ ማኅበራቸው ቀደም ሲል ሁለቱ ተፋላሚዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን የገለጹልን የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ሴና ጂምጂሞ የሰላም ንግግሩ እንዲቀጥል  በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርን ጨምሮ ፤ ከአውሮጳ ህብረት ልዩ ልዑክ ፤ የአፍሪቃ ሕብረት ፤ ኢጋድ እና ከተለያዩ መንግስታት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸውልናል።  የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቃባይ ኦዳ ተርቢ አሁን አመሻሹን በትዊተር ባጋሩት መረጃ ደግሞ በመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለም ሆነ በዕቅድ የተያዘ ንግግር አለመኖሩን አስታውቀዋል። ኦዳ በዚሁ አጭር መረጃቸው እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው ብለዋል። ለሰላማዊ መፍትሔ መስራታችንን እንቀጥላለን ፤ ወደ ፊት የሚደረግ ድርድር ካለም እንሳውቃለን ብለዋል። ኦዳ እየተሰራጨ ነው ያሉት አሉባልታ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር ያሉት ነገር የለም ።

OLLAA meeting in North America
ማህበሩ ከዩናይትድስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዑክ ጋር ከመከረ በኋላ ምስል Private
OLLAA meeting in North America
ሴና ጂምጂሞ የኦሮሞ ሌጋሲ አድቮኬሲ ማህበር ዳይሬክተር ምስል Private

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ