1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት እንዲያስቆም የሚጠይቅ ሰልፍ በፍራንክፈርት ተካሄደ

እሑድ፣ ጥቅምት 23 2012

በፍራንክፈርት ኢትዮጵያውያኑ ያካሄዱትን ሰላማዊ ሰልፍ በማስመልከት የጀርመን ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሮት ባስተላለፉት መልዕክት «በአሁኑ ወቅት ከወደ ኢትዮጵያ የሚሰሙ ዜናዎች አሳሳቢ» መሆናቸውን በመግለፅ «የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አያሌ ፈታኝ ችግሮች ከፊታቸው ተደቅነዋል» ብለዋል

https://p.dw.com/p/3SOyX
Frankfurt am Main | In  Frankfurt lebende Äthiopier demonstrieren
ምስል DW/E. Fekakde

መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ብሄር እና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ግድያ ጥቃት እና ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀል እንዲሁም የዕምነት ተቋማትን ጭምር የማቃጠል አስከፊ ወንጀል ያለማቋረጥ ቢቀጥልም መንግሥት እስካሁን ችግሩን ለመቅረፍ የወሰደው ህጋዊ እርምጃ አጥጋቢ ባለመሆኑን ችግሩ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ።

ሰሞኑን በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግድያና ጥቃት ለማውገዝ ፤እንዲሁም መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት እንዲከላከል ለመጠየቅ ዛሬ በፍራንክፈርት ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱ ኢትዮጵያውያን ወንጀል ፈጻሚዎቹ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል።

"ድርጊቱን ለማስቆም የአገሪቱ የመከላከያ እና የፖሊስ ኃይል ፈጣን እርምጃ አልወሰደም" ያሉት የሰልፉ አስተባባሪ በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ሃላፊ አቶ ስዩም ኃብተማሪያም «መንግሥት ዋና አጥፊ ወንጀለኞችን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ወገንተኝነት የያዘ እስኪያስመስለው ሌሎች አካላት ችግሩን አባብሰውታል በሚል ተደጋጋሚ መግለጫ እና ውንጀላ ላይ መጠመዱ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽር መጪውን ጊዜ የበለጠ አስጊ የሚያደርገው እና ወንጀለኞችንም ለበለጠ ጥፋት የሚያበረታታ ተግባር ነው» ሲሉ ወቅሰዋል።

በፍራንክፈርት ኢትዮጵያውያኑ ያካሄዱትን ሰላማዊ ሰልፍ በማስመልከት የጀርመን ፓርላማ (ቡንደስታግ) ምክትል ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሮት በፅሁፍ ባስተላለፉት መልዕክት «በአሁኑ ወቅት ከወደ ኢትዮጵያ የሚሰሙ አብዛኛዎቹ ዜናዎች አሳሳቢ»  መሆናቸውን በመግለፅ «የዘንድሮው የዓለማችን የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አያሌ ፈታኝ ችግሮች ከፊታቸው ተደቅነዋል ፤ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት የጥቃት ሰለባ ከሆኑ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ጎን መቆማችንን በማስታወስ ለሟች ቤተሰቦች የተሰማንን ሃዘን ለመግለፅ እንወዳለን» ብለዋል።

«በኢትዮጵያ ማናቸውንም ግጭቶች እና ሁከቶች ጨምሮ ሃይማኖት እና ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን አጥብቀን የምንቃወም ሲሆን ፤ የአዲስ አበባም ሆነ የክልል ባለስልጣናት የኃይል ጥቃት ፈጻሚዎችን ለፍርድ እንዲያቀርቡ፤ የማዕከላዊ መንግስቱም ለአናሳ ማህበረሰቦችም ሆነ በአጠቃላይ ለዜጎቹ ህጋዊ ጥበቃ እንዲያደርግ እንጠይቃለን» ሲሉ የጀርመን ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሮት መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ