1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መተማመን የጎደለው፤ ጥላቻና ፕሮፓጋንዳ ያጠላበት የኢትዮጵያው ድርድር

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 30 2014

"እኛ እንደተገነዘብነው መንግሥት እስካሁን ለድርድሩ ያስቀመጠው ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የለም፤ሆኖም ከመቀሌው ጉብኝታችን እንደተረዳሁት ከሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ በኩል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ የቀረበ ቅድመ ሁኔታ አለ።" :ዶ/ር አኔተ ቬበር

https://p.dw.com/p/4FDIt
Dr. Annette Weber
ምስል SWP

መተማመን የጎደለው፤ ጥላቻና ፕሮፓጋንዳ ያጠላበት የኢትዮጵያው ድርድር

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና በሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ መካከል የሰፈነው አለመተማመን ለሰላም ድርድሩ ዋናው እንቅፋት እንደነበር በአፍሪቃ ቀንድ የአውሮጳ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ገለጹ:: ልዩ መልዕክተኛዋ አኔተ ቬበር ከዶይቼ ቨለ "DW" የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ፤ በሁለቱም ወገኖች ይንጸባረቁ የነበሩ የጥላቻና በብሄሮች መካከል ውጥረትን የሚያሰፍኑ ንግግሮችና መግለጫዎችም ትልቅ መሰናክል ፈጥረው መቆየታቸውን በማውሳት እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንዲያረግቡና በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መርህና ጥላ ስር ለሚካሄደው ቀጣይ ድርድር ፍሬያማ ውጤት ሊያመጡ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ውይይት ለማካሄድ እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል::
ሁለት ዓመታትን ሊደፍን የጥቂት ወራት ዕድሜ ብቻ የቀሩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ውይይት ለመቋጨት ከሰሞኑ የአሜሪካ እና የአውሮጳ ህብረት ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም የምዕራባውያን አምባሳደሮች ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ሕወሃት/ አመራሮች ጋር የተናጥል ውይይት አካሂደዋል:: በጉዞዋቸው ያከናወኗቸውን ዓበይት ተግባራት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡት የዶይቼ ቨለ "DW" የአማርኛው ፕሮግራም ክፍል በአፍሪቃ ቀንድ የአውሮጳ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ዶ/ር አኔተ ቬበር አነጋግሯቸዋል:: "አስካሁን በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሰላም ድርድሩ ዋና እንቅፋት ሆኖ የቆየው በመሃላቸው የሰፈነው የመተማመን እጦት ነው" ይመስለኛል የሚሉት ቬበር አሁንም ሁለቱም ኃይላት በየፊናቸው ወደ ዋናው ድርድር ለመምጣት ያላቸውን ፍላጎት ከማሳወቅ ባሻገር የመተማመን ስሜትን ለፈጥሩና ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት:: በዚህ ረገድ የአፍሪቃ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ተደራዳሪዎቹ በመተማመን ተቀራርበው የሰላም ውይይቱን እንዲጀምሩ ለማስቻል አስፈላጊውን ጥረት ማድረጋቸውንም ቬበር ጠቅሰዋል::
"በሁለቱም ወገኖች መካከል መተማመን አለመኖሩ በሰላም ውይይቱ ሂደት ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ተደራዳሪ ኃይላቱ እርስ በእርሳቸው የመተማመን ስሜትን እንዲያጎለብቱና ተቀራርበው ቀውሱን በሰላም እንዲፈቱ ለማስቻል አስፈላጊውን ጥረ ሁሉ አድርገዋል:: እኛ እንደተገነዘብነው መንግሥት እስካሁን ለድርድሩ ያስቀመጠው ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የለም፤ሆኖም ከመቀሌው ጉብኝታችን እንደተረዳሁት ከሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ በኩል በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ የቀረበ ቅድመ ሁኔታ አለ:: እነዚህ አገልግሎቶች የሚቀጥሉ እስከሆነ ከመንግሥት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል"
ዶክተር ቬበር ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር ከመምጣታቸው አስቀድሞ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ግልጽ የሆነ መተማመንን በመሃላቸው ሊፈጥሩ ይገባል ሲሉም በተደጋጋሚ አጽንዖት ሰጥተው አስገንዝበዋል:: አንዱ በሌላው ላይ የሚሰነዝረው የጥላቻ ንግግርና ቀስቃሽ መግለጫ እንዲሁም ቅራኔውን የሚያሰፋ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻም ሊገታ ይገባዋል ነው ያሉት::
"ከሰላም ውይይቱ በፊት በመሃላቸው መከባበር የሰፈነበት የመተማመን ስሜትን ማጎልበት እጅግ ጠቃሚ ነው፤በብሄሮች መካከል ውጥረትን ከሚያሰፍን ከጥላቻ ቀስቃሽ ንግግርና መግለጫም መቆጠብ ይገባል፤አንዱ በሌላው ላይ የሚያካሂደውን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማርገብም ለሰላም ውይይቱ ስኬት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፤ ምክንያቱም የጥላቻ ንግግር በመሃላቸው ያለውን ዕምነት የሚሸረሽር በመሆኑ ነው:: በመሰረቱ ከእንዲህ ዓይነቱ ቅራኔን ከሚያባብስ ተግባር መቆጠብ የሰላም ውይይቱ እንዲሰምር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንም እርስ በራሳቸው እንደ አንድ ሃገር ዜጋ እንዲተያዩና በጋራ እንዲቆሙ የሚረዳ ነው"
የትግራይም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም በእጅጉ ናፍቆታል ያሉት በአፍሪቃ ቀንድ የአውሮጳ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ዶ/ር አኔተ ቬበር፤የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የትግራይ ኃይላት ወደ ሌላ ወደ ሌላ ዙር ግጭት እንዳያመሩ በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት ማዕቀፍና ጥላ ስር የተጀመረው ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል::
"በእኛ በኩል አሁን ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረገው የሰላም ውይይት በጣም አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን፤አቋምችን ለሁለቱም ወገኖች ግልጽ ነው፤ በአፍሪቃ ህብረት ጥላና ማዕቀፍ ስር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው ውይይት የሚቀጥልበትን መንገድ መደገፍ ሁነኛው አማራጭ ነው፤በአሁኑ ወቅት የትግራይም ሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋሉ፤ በተለይም የትግራይ ሕዝብ ወደ መደበኛ ሰላማዊ ሕይወቱ መመለስን ሌላው የሃገሪቱ ምህበረሰብም የቀደመው የለውጡ ጅማሮ ሂደት እንዲቀጥል ፍላጎታቸው ነው:: ከግጭትና ጦርነት የትኛውም ወገን አትራፊ ባለመሆኑ ሁለቱም በጠረጴዛ ዙሪያ ወደ ስምምነት በሚያደርሷቸው አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል"
እንዳልካቸው ፈቃደ
እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር